1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ ችግር ያስከተለው የሰብዓዊ ቀዉስ በኢትዮጵያ

ሰኞ፣ ጥቅምት 13 2010

በኢትዮጵያ በተፈጥሮና በሰዉ ሰራሽ ችግሮች ሳቢያ የሰብዓዊ ቀዉስ እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፎች ማስተባበሪ ጽ/ቤት በምህጻሩ OCHA አስታወቀ። በመሆኑም መንግስትና የሰብዓዊ እርዳታ አጋሮች ትኩረት ሰጥተዉ ሊሰሩበት ይገባል ብሏል።

https://p.dw.com/p/2mMe7
Äthiopien Hunger Hungerhilfe
ምስል picture-alliance/dpa/M. Ayene

Humaniterian Crisis in Ethiopia - MP3-Stereo

 

 የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ  እርዳታ የሚያስፈልጋቸዉን  ሰዎች ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን አመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪ ጽ/ቤት በምህጻሩ ኦቻ ሰሞኑን ባወጣዉ ወቅታዊ ዘገባ እንደገለጸዉ የሀገሪቱ ሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ ነው።
በድርቅ፣ በጎርፍና በእርስበርስ ግጭቶች ሳቢያ በሀገሪቱ   እርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ ሰወች ቁጥርም እየጨመረ በመሆኑ ጽ/ቤቱ በጎርጎሮሳዊዉ 2017  ክለሳ ያካሄደበትን የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ሰነድ  ሳይቀር እንደገና ለመመልከት መዘጋጀቱን አስታውቋል።
በሀገሪቱ ሰብል አምራች በሆኑ የኦሮሚያ ፣የደቡብና የምስራቅ አማራ አካባቢወች  በቂ የክረምት ዝናብ ባለመጣሉ ሊያስከትለው የሚችለው የምርት መጠን መቀነስም ሌላዉ ተጨማሪ ችግር መሆኑ ተመልክቷል። በዚህም የተነሳ በወቅቱ ርዳታ የሚያስፈልገው 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰው ቁጥር መሻሻል ሳይታይበት ወደ 2018ዓ/ም  ሊሸጋገር ይችላል የሚል ስጋት እንዳለዉ ኦቻ  ገልጿል።
የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ግጭትን ተከትሎ በቅርቡ የተከሰተዉ የዜጎች መፈናቀልም እየጨመረ ለመጣዉ ሰብዓዊ ቀዉስ ምክንያትት መሆኑ ተገልጿል።  ለእነዚህ ተፈናቃዮች የሚደረገዉን ድጋፍ በተመለከተ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጽ/ቤቱ ጠቁሞ አሁን ባለዉ ሁኔታ ችግረኞቹን ለመደገፍ ከ 103 ሚሊዮን ዶላር  በላይ  በጀት ያስልጋል። የድርቅ ተጎጅወችን  ለመደገፍ ደግሞ እስከ መጭዉ ጥር ወር ብቻ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር  ያስልጋል ሲል ጽ/ቤቱ አመልክቷል።
እንደ ኦቻ ዘገባ በምግብ እርዳታ ረገድ ቀደም ሲል በሴፍትኔት ተጠቃሚ የነበሩ  4 ሚሊዮን ሰዎች ሲሆኑ የተፈናቀሉ ዜጎች መጨመርና የተምች ዘር በሰብል ላይ በሚያደርሰዉ ጉዳት የተነሳ በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ እያሻቀበ መጥቷል።  በመሆኑም  መንግስትና የሰብዓዊ እርዳታ አጋሮች ትኩረት ሰጥተዉ ሊሰሩበት ይገባል ነዉ የተባለዉ።
የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ በድርቅ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከሚደረገዉ ድጋፍ ዉጭ በአሁኑ ወቅት በመፈናቀልና በጎርፍ አደጋ ለደረሰባቸዉም ዜጎች እርዳታና ድጋፍ መቀጠሉን ገልጿል። የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴ ማብራሪያ አላቸዉ።«ይህ ቁጥር 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሆነዉን አስቀድሞ የተቀመጠ ነገር ስለሆነ እነዚህ ሶስት አካላት ማለትም  መንግስት፣መንግስታዊ ያልሆነዉ ህብረትና  የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድጋፍ እያደረጉ ናቸዉ ። ከዚያ ዉጭ ለተከሰተዉም መንግስት አስፈላጊዉን ድጋፍ እያደረገ ነዉ ።» ሲሉ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴ አብራርተዋል።  
እንደ  አቶ ደበበ ገለጻ ድርቅን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የእለት ደራሽ እርዳታ  የሚያስፈልጋቸዉን  ሰወች ወቅታዊ ቁጥር  በመጭዉ ህዳር ይፋ ይሆናል።
እንደ ተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪ ጽ/ቤት በተመጣጠነ ምግብ እጥረትና  በጤና  ረገድ ያለዉ ፍላጎት በተለይ በሶማሌ ክልል እሳሳቢ እየሆነ  መጥቷል። የአጣዳፊ ተቅማጥና ትዉከት በሽታ በተፈናቃዮች ዘንድ ሊከሰት ይችላል የሚለዉም ሌላዉ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ፤የጤና ባለሙያወች ጉዳዩን በቅርብ እንዲከታተሉትና የእርዳታ ድርጅቶችም ከወቅታዊዉ  የሰብዓዊ ሁኔታ  ጋር እቅዶቻቸዉን በማስተካከል እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎችን ህይወት እንዲታደጉ ጽ/ቤቱ  አሳስቧል።

Äthiopien Gode - Dürre-Krise
ምስል DW/J. Jeffrey

 

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ