1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቱርክና የአውሮፓው ኅብረት፣

ሐሙስ፣ ሐምሌ 22 2002

አየርላንድ የኅብረቱ አባል እንዳትሆን ያገዳት የአገሯ ህዝብ ውሳኔ እንደነበረ የሚታወስ ነው። ቱርክ ግን አባል እንዳትሆን ከኅብረቱ አባል መንግሥታት ነው ሰፊ ተቃውሞ የገጠማት።

https://p.dw.com/p/OXZo
ቱርክና የአውሮፓው ኅብረት፣
ምስል AP

አንዳንድ የኅብረቱ አባል መንግሥታት የሆነው ሆኖ፣ የተለየ አመለካከት እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል። ለምሳሌ ያህል ብሪታንያ፤ ካትሪን ብራንድ፤ ከብራሰልስ ወደ ቦን የላከችውን ዘገባ ፤ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

አብዛኞቹ የአውሮፓው ኅብረት አባል አገሮች ስለቱርክ ሲናገሩ ፣ ሦስት ቃላት ይሠነዝራሉ፤ ትልቅ፤ ድሃ እና ግራ-አጋቢ የሚሉ ናቸው። በቆዳ ስፋት እርግጥ ነው ቱርክ ከፈረንሳይ በለጥ ትላለች። የህዝቧ ብዛት ደግሞ ከሞላ ጎደል ከጀርመን ህዝብ ብዛት ጋር የሚስተካከል ነው። የህዝቧ የነፍስ ወከፍ ገቢ ሲታይ ከሩማንያ ህዝብ ያነሰ ወይም ይበልጥ የደኸየ ነው። በሦስተኛ ደረጃ ግራ አጋቢ፤ ውስብስብ የሚባለው አገላለጽ፤ ለአውሮፓ ባእድ፤ የተለየ ባህል ያላት ለማለት ሲሆን ብዙዎቹ ያን ያህል በግልጽ አያወሱትም። አንጌላ ሜርክል ግን በግልጽ ነው የሚናገሩት--።

«እንደሚመስለኝ፤ ሙስሊሙን ዓለም፣ በተለይ ቱርክን ይበልጥ ማቅረብ ለሁላችን ጠቀሜታ አለው። በምን ዓይነት ግንኙነት እንዴትስ ሆኖ ይፈጸማል? ከአውሮፓው ኅብረት ጋር የተለየ አስተያየት የሚደረግለት ተጓዳኝነት ወይስ ሙሉ አባልነት --በዚህ ላይ ነው የምነካረከረው።»

የጀርመን መራኂተ-መንግሥት ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል ይህን የተናገሩት፤ ባለፈው ዓመት ፕራግ ውስጥ ተደርጎ በነበረው ጉባዔ፤ያኔ አዲስ የነበሩት የዩናይትድ እስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ የአውሮፓው ኅብረት አባል አገሮች፤ ቱርክን እንዲቀበሏት አባል ትሆን ካሳሰቡ በኋላ ነበረ። የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ግን ይበልጥ ግልጽ ሆነው የተናገሩት።

«ቱርክ በአውሮፓው ኅብረት ቦታ የምታገኝ አይመስለኝም። ይህን ጥያቄ በተመለከተ አመላካከቴን አልለውጥኩም።»

አንጌላ ሜርክልና ኒኮላ ሳርኮዚ የሆነው ሆኖ፤ ቱርክ የአውሮፓው ኅብረት አባል ልትሆን በምትችልባቸው ቅድመ-ግዴታዎች ዙሪያ፤ ኅብረቱ በይፋ የሚያደርገውን ውይይትም ሆነ ድርድር ሊገቱት አይችሉም። የመንግሥታቱ መሪዎች እ ጎ አ በ 2004 ዓ ም፤ ድርድር እንዲጀመር በሙሉ ድምፅ መስማማታቸውም የሚዘነጋ አይደለም። ድርድሩ ከተጀመረ ከ 10 እና 15 ዓመታት ወዲህ ፣ የሆነው ሆኖ፣ ቱርክ የተጠየቀችውን የቱን ያህል እንዳሟላች፤ ኅብረቱም ለመቀበል ያለው ዝግጁነት በአርግጥ እስከምን ድረስ አንደሆነ መመርመር ይኖርበታል። ኅብረቱ፤ ባለፉት 5 ዓመታት 12 አዳዲስ አባላት ተቀብሎ ብዛቱን ከጨመረ ወዲህ አሁን የተሰላቸ ነው የሚመስለው። 27 ቱ አባል አገሮች ተስማምቶ ለመሥራት ሰፊ ኃይልና ገንዘብ እያስወጣቸው ነው። ከአዲሱ የብሪታንያው ጠ/ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን በስተቀር፤ አዲስና ትልቅ ሀገር ከእንግዲህ በአባልነት ለመቀበል የሚሻ፤ ያለም አይመስልም።

«ቱርክ፣ በኔቶ ተጓዳኝነቷ፤ አውሮፓን ለመጠበቅ ያደረገችውን፣ አሁንም በአፍጋኒስታን ያለትን ድርሻ ሳስብና የአውሮፓው ኅብረት አባል እንዳትሆን የተደቀነባትን ሳንክ ስመለከት ያናድደኛል። »

ባለፈው ሰኞ ነበረ ካሜሩን አንካራ ውስጥ ከቱርክ የንግድ ሰዎች ጋር ሲነጋገሩ ይህን ያሉት። አያይዘውም ቱርክ የአውሮፓው ኅብረት አባል ትሆን ዘንድ ፤ በተቻላቸው ሁሉ እንደሚሟገቱ ም ነው ቃል የገቡት። አንዳንድ የአውሮፓውን ኅብረት በጥርጣሬ የሚመለከቱ የብሪታንያ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ከሆነ፣ የብሪታንያው ጠ/ሚንስትር፤ይህን የሚሉት ለቱርክ ተቆርቁረው ሳይሆን፤ የአውሮፓውን ኅብረት እንደ አንድ የፖለቲካ ተቋም ለማዳከም ነው። ኅብረቱ ከሰፋ ፤ አባላቱ የተለያየ አመላካከት ስላላቸው አንድነታቸው መጠናከሩ ቀርቶ ይላላል። በአሁኑ ጊዜ የሆነው ሆኖ፣ ጊዜው ለቱርክ ተቃዋሚዎች ነው ያመቸው። ይሁንና የቱርክ አቋም፣ ከአውሮፓው ኅብረት ህጎችና እሴቶች የቱን ያህል የሚጣጣም ሆኖ እንደተገኘ ማመሣከር የግድ ማለቱ አልቀረም። ሂደቱ እጅግ አዝጋሚ በመሆኑ ክሮኤሺያና አይስላንድ እርሷን ቀድመው 28ኛ ና 29ኛ አባላት ሳይሆኑ እንደማይቀሩም እየተነገረ ነው። ማመልከቻ ያስገቡት አገሮች ሁሉ የሆነው ሆኖ፣ ገና ረጅም ጊዜ መጠበቃቸው አይቀሬ ነው። ከመቄዶንያ ጋር የሚካሄደው ውይይት ከግሪክ ጋር ባላት ጭቅጭቅ ሳቢያ ፈቀቅ ሊል አልቻለም። አልባንያ፣ ሞንቴኔግሮና ሰርቢያ ደግሞ በቅርቡ ነው ማመልከቻ ያስገቡት።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ