1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቱኒዚያ-የዘመናቱ ሥርዓት ተገነደሰ

ሰኞ፣ ጥር 9 2003

ይቺዉ ኑሮ በዛች ብሎ ሥርዓታቸዉ ሲጨክንበት-በራሱ ላይ ጨከነ።ታሕሳስ 17 2010-እራሱ ላይ የጫራት ክብሪት መላ ቱኒዚያን ታነድ-ጢስ ጠለሷ የሜድትራንያ ባሕር ተሻግሮ ፈረንሳይ የሚኖሩ ቱኒዚያዎችን ያዉድ ገባ።

https://p.dw.com/p/Qsxx
መሐመድ ቡዛዚምስል picture alliance/dpa

17 01 11

አመፅ-ጩኸት፥ግጭት-ሞት እና የዘመናት ሥርዓት መደርመስ።የቱኒዚያ ክራሞት።የሰሜን አፍሪቃዊቱ ዉብ-አረባዊት ሐገር ሰሞናዊ እዉነት መነሻ፥ ምክንያቱ ማጣቃሻ፥ እንድምታ አስተምሕሮቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።እንደ ሁለት ዓመት ሕፃን በሁለት እግሩ ለመቆም ሲዉተረተር እሳቸዉ እንደ ታማኝ ጠቅላይ ሚንስትር «የቱኒዚያ የነፃ አባት» እያሉ-እያቆለጳጰሱ ያገለገሏቸዉን ፕሬዝዳት ሐቢብ ቡርጊባን ለአዲሲቱ ቱኒዚያ የማይበጁ፥ ያረጁ ያፈጁ ብለዋል አስወገዷቸዉ።እንደ ተራማጅ መሪ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን ጠቅልለዉ ያዙ።ዚን አል አብዲን ቤን ዓሊ።ሕዳር 1987 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)

እሱ እያደገ-የኑሮ መከራን ሲጋፈጥ እሳቸዉ እንደተቀማጠሉ የሜድትራኒያን ባሕር ዳርቻዋን፥ አረባዊት ሐገር ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩ።መሐመድ ቡዛዚ እንደ መሪ በርግጥ ከሳቸዉ ሌላ-ሌላ አያዉቅም።እንደ ብዙ የእድሜ አቻዎቹ ሌላ የማወቅ ምኞት፥ ፍላጎት ቢኖረዉ እንኳን ለእናቱ መጦሪያ፥ለራሱ መኖሪያ ከመቃረም ባለፍ እሳቸዉን የመዳፈር ዝንባሌ፥ ድፍረት፥ አቅምም አልነበረዉም።

Zine El Abidine Ben Ali
ቤን ዓሊምስል picture alliance / dpa

ይቺዉ ኑሮ በዛች ብሎ ሥርዓታቸዉ ሲጨክንበት-በራሱ ላይ ጨከነ።ታሕሳስ 17 2010-እራሱ ላይ የጫራት ክብሪት መላ ቱኒዚያን ታነድ-ጢስ ጠለሷ የሜድትራንያ ባሕር ተሻግሮ ፈረንሳይ የሚኖሩ ቱኒዚያዎችን ያዉድ ገባ።

ያን ጀግና ዛሬ እንደ ጀግና ያስታወሰዉ ብዙ የለም።መልዕክት አስተምሕሮቱ ግን በርግጥ ብዙ ነበር።በ1984 ሳዲ ቡዚዲ ከተማ የተወለደዉ መሐመድ ቡዛዚ እንደ እድሜ አቻዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን አጠናቅቋል።ሥራ ቀጣሪ ማግኘት ግን አልቻለም።ተወልዶ ባደገባት ከተማ አትክልት ፍራ-ፍራፍሬ ይቸረችር ያዘ።

ከገቢዉ ማነስ በተጨማሪ ሰበብ አስባብ እየፈጠሩ ጉቦ የሚጠይቁት ፖሊሶች ሲደርሱበት፥ካለዉ የቃረማትን ማጋራት ከሌላዉ ሸቀጡን ጠቅልሎ መሮጥ ለመሐመድ-ለብጤዎቹም አድካሚ አሰልቺም ግን ግድ ነበር።አልደከመዉም።ቢደክም-ቢታክተዉም አሮጌት እናቱን ለመጦር፥ እራሱን ለማኖር ሌላ ምርጫ አልነበረዉም።የዚያን ቀን ግን -ፖሊሶች ያዙት።ፍቃድ የለሕም ብለዉ አትክልቱን ወረሱበት።ደበደቡት።

Mohammed Bouazizi Tunesien Unruhen Krankenhaus Ben Ali
እሳት-ሞት መሐመድ ቡዛዚምስል AP Photo/Tunisian Presidency

እንደ ዜጋ በደዮቹን ለመክሰስ አቤት ማለቱ አልቀረም።የሰማዉ ግን የለም።ከንቱ ጩኸት።በቃ መረረዉ።ከኪሱ በነበረች ሳንቲም ቤንዚን ገዛ።ለእናቱ «ፌስ ቡክ» ላይ በለጠፈዉ ደብዳቤ ይቅርታ ጠየቀ።ተንደርድሮ አቤቱታ ካቀረበበት መሥሪያ ቤት አጠገብ ደረሰ።ቤንዚኑን ሰዉነቱ ላይ ቸለሰዉ።ቀጠለ-እሳት።አልሞተም ግን ክፉኛ ነደደ።የሃያ-ዘጠኝ አመቱ ወጣት ሲያጣጥር አካሉን ያነደችዉ እሳት ሥራ አጥነት፥ የኑሮ ዉድነት፥ ሙስና ሆድ ያባሰዉን የቱኒዚያ ወጣት ለአደባባይ ሠልፍ-ተቃዉሞ አሳደመች።

እሳቸዉ ግን የደዉሉን ድምፅ መስማት፥ መልዕክቱን መቀበል አልፈለጉም ነበር።መሐመድ በሞተ በሳምንቱ እራሱን ማቃጠል-መግደሉ የቀሰቀሰዉን አመፅ-የወንጀለኞች ምግባር በማለት አወገዙት። ፕሬዝዳት ቤን ዓሊ ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ።

«እነዚሕ ሰዎች የመንግሥት ሕንፃዎችን ሰባብረዋል።የመንግሥት ተቋማትና መስሪያ ቤቶችን፥ የዋሕ ዜጎችን አጥቅተዋል።ይሕ ወንጀል ነዉ።እና ልንታገሰዉ አንችልም።ከዚሕ አመፅ ጀርባ ልጆቻችንን መሳሪያ የሚያደርጉ ሐይላት አሉ።ተማሪዎችና ሥራ አጦችን የሚያነሳሱ እና በመንግሥት ላይ የሐሰት ወሬ የሚነዙ ሰዎች አሉ።»

የቤርቤሮችን ብልጠት፥ የካርቴዦችን ሥልጣኔ፥ የፎኔዥያዎችን ወይም ፊንቃዉያንን (ያሁኖቹ ሊባኖሶች)፥ የከነአኖችን እዉቀት፥ የግሪኮችን ጥበብ፥ የአረቦችን ብልሐት፥ የአዉሮጳ-በጣሙን የፈረንሳዮችን ሥርዓት ለዘመነ-ዘመናት ያስተናገደችዉ ሐገር ስሟን ከርዕሠ-ከተማዋ ስም ነዉ የወረሰችዉ።ከቱኒዝ።የተለያዩ ወገኖች የተለያየ ጥበብ፥ እዉቀት፥ ሥልጣኔ ሐይማኖት፥ ብልሐት ሥርዓት የተፈራረቀባት ቱኒዝ የሜድትራኒያ ባሕርን መንተራሷን እንጂ የመጠሪያዋን ትክክለኛ ምንጭ መለየቱ አዳጋች ነዉ።

ብዙ ተመራማሪዎች ግን ከርዕሠ-ከተማይቱ አልፎ የፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች ድንበር ለከለሉላት ለዛሬዋ ቱኒዚያ መጠሪያ የዋለዉ ሥም ከፎኔዥያዉያኑ (ፊንቃዉያኑ) ቱኒት ፈልቆ፥ ከቤርቦሮቹ ኤንስ ጋር ተዳቅሎ-የአረብኛዉን ትርጉም በያዘዉ ቃል- መርጋቱን ይገልፃሉ።ቱኒዝ-«እጅ መስጠት ወይም መማረክ እንደማለት ነዉ-ፍቺዉ።

ቤርቤሮች፥ ካርቴዦች፥ ግሪኮች፥ ሮሞች፥ አረቦች፥ ስጳኞች፥ ቱርኮች በየዘመናቸዉ እየፈረጠሙ ሲጓዟት ዘመን ላፈረጠመዉ ሲንበረከኩባት ዘመነ-ዘመናት ያስቆጠረችዉ ሐገር ታሪኳም እንደ ስሟ እጅ-ከመስጠት መንበረክክ ብዙ ያለፈ አልነበረም።በ1881 ፈረንሳይ ያዘመተችዉ ሰላሳ-ስድት ሺሕ ጦር ያቺን ሐገር ሲያስገብር በያኔዉ ፖለቲካዊ አዋቂ ዘንድ የጠንካራዋን አዉሮጳዊት ሐገር ጠንካራ አገዛዝ የሚነቀንቅ አይኖርም ተብሎለት ነበር።

በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ጦር ያደከመዉን የፈረንሳይ ቅኝ ገዢ ሐይል እነ ቡርጊባ የመሯቸዉ የነፃነት አርበኞች አዋክበዉ-ሐይለኛይቱ አዉሮጳዊት ቅኝ ገዢን አንበረከኳት።1956።ነፃነት። በነፃነት ትግሉ ወቅት ሥም-ዝና አርበኝነታቸዉ በመላዉ ቱኒዚያ የናኘዉ ቡርጊባ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ያዙ።

ቡርጊባ በአመቱ የንጉስ ቤይ ላሚንን ልማዳዊ ዘዉዳዊ አገዛዝ አስወግደዉ የጠቅላይ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን ሲይዙ አበጀሕ ያላላቸዉ ቱኒዚያዊ ጥቂት ነበር።ፈረንሳዮችን በነፍጥ፥ ልማዳዊዉን ዘዉዳዊ አገዛዝ በፖለቲካዊ መፈንቅለ መንግሥት አንበርክከዉ የዚያችን ሐገር የመሪነት ሥልጣን ለእድሜ ልክ የጠቀለሉት ቡርጊባ ከመወደደድ መፈቀራቸዉ ባለፍ ያደራጁት ጦር-ሐይል ጥንካሬ መንበርከክ ቀርቶ ይንገዳገዳሉ ብሎ ለማሰብ ሲበዛ ከባድ ነበር።

እድሜም ጤናም-ሲጫጫናቸዉ ግን የረጅም ጊዜ ጠቅላይ ሚንስትራቸዉ ዚን ቤን አሊ አንበረከኳቸዉ።1987።በሃያ-ሰወስት አመቱ ዘንድሮ ቱኒዚያ ላይ የሆነዉን ቤን ዓሊ ከሐገራቸዉ ያለፈ ታሪክ፥ ከራሳቸዉ የድሕረ-ሃያ ሰወስት ዓመት ምግባር ለማሰላሰል የሃያ-ሰወስት አመቱ አገዛዝ የፈቀደላቸዉ አል-መሰለም።«የወንጀለኞች ምግባርና ሴራ» በማለት ያወገዙት አመፅ፥ ተቃዉሞዉን ለማርገብ የፀጥታ ሐይሎቻቸዉ እርምጃ እንዳልበቃ ቢያዉቁም አልተንበረከኩም።

ሌላ ፖለቲካዊ ያሉትን «ብልጠት» አንድ ሁለት ይሉ ገቡ።የወጣትና የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትሮቻቸዉን አሰናበቱ።አመፁን ለማርገብ አልቻሉም።እንደ ቆጠቆጣቸዉ ግን አልካዱም።ግን አልተንበረከኩም።እንዲያዉም እስከ ማክሰኞ ድረስ ለወደፊቱ ያቅዱ ነበር።ሌላ አዋጅ።

«ፖለቲከኞች፥ የምጣኔ ሐብት አዋቂዎች፥ዩኒቨርስቲዎች፥ የከተማ ከንቲቦች የሚካፈሉበት ዉይይት ማድረግ አለብን።ሰዎቹ የሚሉትን መስማት አለብን።ለሚቀጥሉት አመታት ችግሮቻቸዉን ለማስወገድ እንችል ዘንድ በትክክል የሚሰማቸዉን ማወቅ አለብን።»

የኑሮ ዉድነት፥ ሥራ አጥነት፥ የመሐመድ መስዋዕትነት የመሐመድን ብሶት-በጩኸት የገለጡ የሌሎች ወጣቶች መስዋዕትነት ያስቆጣዉ ሕዝብ ግን የሃያ-ሰወስት አመት መሪዉን «በቁን በቃንዎት» እንዳለ ነበር።ሰዉዬዉ አልተበገሩም ወይም የተበገሩ አልመሰሉም።የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልስ የመሰለ ሌላ መልክት አወጁ።

«ፖለቲካዊ ጥያቄችሁን ተቀበይዋለሁ።በዚሕም ምክንያት በፕረስ ነፃነት ላይ ምንም ገደብ እንዳይጣል ደንግጌያለሁ።አምደ መረቦችም ከእንግዲሕ አይታገዱም።በመገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚደረገዉ ቅድመ-ምርመራም ተነስቷል።»

Tunesien Unruhen Trümmer Ruinen
አመፅ-እሳት- እሳት አመድምስል AP

ከሰወስት አመት በሕዋላ በ2014 በሚደረገዉ ምርጫ እንደማይወዳደሩም ፕሬዝዳንቱ አስታወቁ።እስከ አርብ ድረስ የፖለቲካ አዋቂዎች፥ የመገናኛ ዘዴ ባለሙያዎች፥ የፕረስ ነፃነት ተሟጋቾች አስተያየት ክርክር የፕሬዝዳንት ቤን አሊ እርምጃን ተገቢነት አመልካች ነበር።ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አንዳዶቹም የፕሬዝዳንቱን ንግግር አወድሰዉ ነበር።ነጂብ ቻቢ አንዱ ናቸዉ።

«እንደሚመስለኝ ትናንት የሰማነዉ ጥሩ ንግግር ነዉ።ፕሬዝዳንቱ የፕረስ ነፃነትን፥ የኢንተርኔት ነፃነትን ጨምሮ ለማክበር፥ በሰላማዊ መንገድ በአደባባይ የመሰብሰብን መብት ለማክበር ወስነዋል።ነፃ ምርጫ ለማድረግ ተስማምተዋል።በ2014 በሚደረገዉ ምርጫ እንደማይወዳደሩም አስታዉቀዋል።እነዚሕ በሙሉ ግን ቃላት ናቸዉ።እኛ የምንሻዉ ቃል-መግባት ሳይሆን ገቢራዊ የሚሆኑበትን ሥልት መቀየሱን ነዉ።»

የፕሬዝዳንቱ ንግግር ሲያወያይ ሲያነጋግር-አርብ እሳቸዉ ምናልባት አስቀድመዉ የነደፉትን ስልታቸዉን ገቢር-አደረጉ።እብስ ወደ ጂዳ።በርግጥ ተንበረከኩ።የሃያ-ሰወስት ዘመን ሥርዓታቸዉ ተንኮታኮተ።ሕዝቡ በተለይ ከሜድትራኒያን ባሕር ማዶ ፈረንሳይ የሚኖረዉ ስደተኛ ፈነጠዘ።

«ቤን ዓሊ ወንጀለኛዉ፥-አምባገነኑ ተወገደ።» ይላል መፈክሩ

«ላለፉት ሃያ አመታት ወደ ሐገሬ መግባት አልቻልኩም ነበር።አሁን ግን ዛሬ እዚሕ ከኔ ጋር የተሰለፉትን ልጆቼን ይዤ ሐገሬ መግባት እችላለሁ።» አለ እሱ።ሌላዉ ቀጠለ፣-

«ሐምሳ ሰባት አመቴ ነዉ።ከልጅነቴ ጀምሮ የምሰማዉ አንድ ስም ነበር።የቱኒዚያ መንግሥትን ሁል ጊዜም የሚቆጣጠረዉ አንድ ነገድ ነዉ።አንገሽግሾናል።የቤን ዓሊ አገዛዝ መፈፀሙ ተገቢ ነዉ።ሕዝቡን እንደ ዉሻ ነበር የሚገዙት።»

ቱኒዚያ የሰቀዘዉ ፖለቲካዊ ጉንፋን አልጄሪያ፥ ግብፅ፥ ዮርዳኖስ ሌሎችን እያስነጠሰ ነዉ።ቱኒዚያ በርግጥ አልተረጋጋችም። ቤን ዓሊ ግን ተንበረከኩ።ሥርዓታቸዉ ተንገዳግዶ-ተገረሰሰ።ማነሕ ባለ-ተራ ነዉ የከንግዲሁ ጥያቄ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ