1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቲለርሰን እና ላቭሮቭ በአፍሪቃ ምን ያደርጋሉ?

ቅዳሜ፣ መጋቢት 1 2010

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን እና የሩሲያ አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትን ጎብኝተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በተመሳሳይ ወቅት በአፍሪካ መገኘት ከፍተኛ መነጋጋሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ በሁለቱ ሀገራት መካከል “መቀናቀኑ ቢኖርም በአፍሪካ ቀጥታ ፉክክር አልገጠሙም” ይላሉ።

https://p.dw.com/p/2u60O
Bildkombo Rex Tillerson Sergei Lawrow

ሚኒስትሮቹ የደህንነት እና የንግድ ጥቅሞችን ማስጠበቅ ላይ አተኩረዋል

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የአፍሪካ ሀገራትን በዚህ ሳምንት እንደሚጎበኙ በመጀመሪያ ይፋ ሲደረግ ዓለም አቀፍ ትኩረት የሳቡት ሁለት ነገሮች ከጉብኝታቸው ዋና ዓላማ ውጭ የሆኑ ናቸው፡፡ አንደኛው የሀገራቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዛሬ ሁለት ወር ግድም የአፍሪካ ሀገራትን ለመግለጽ ለተጠቀሙበት ጸያፍ ቋንቋ ይፋዊ ይቅርታ ይጠይቃሉን? የሚለው ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እንደ እርሳቸው ሁሉ አፍሪካን በተመሳሳይ ወቅት ከሚጎበኙት የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ ወይ? የሚለው ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱም ጥያቄዎች ይመለሱባታል ተብላ የታሰበችው ከተማ ደግሞ አዲስ አበባ ነበረች፡፡ 

ቲለርሰን ትራምፕን ወክለው ለአፍሪካውያን ይቅርታ ከጠየቁ ይህንኑ የሚያደርጉት በኢትዮጵያ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽህፈት ቤት ነውና ነው አዲስ አበባ መነሳቷ፡፡ ቲለርሰን እና ላቭሮቭ በየፊናቸው ከሚጎበኟቸው አስር የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በሁለቱም አጀንዳ ውስጥ የነበረችው ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗ ለሁለቱ ንግግር ማካሄጃነት ተመራጭ አድርጓት ነበር፡፡ ይቅርታውም ሆነ የሁለቱ ሚኒስትሮች መገናኘት ግን እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ 

Äthiopien Rex Tillerson und Moussa Faki Kommissionsvorsitzender Afrikanische Union (AU)
ምስል Getty Images/AFP/S. Maina

ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ቲለርሰን እና ላቭሮቭ በተመሳሳይ በሸራተን አዲስ ሆቴል አርፈው ለመነጋገር ፍቃደኝነታቸውን አላሳዩም የሚል ዘገባዎች ቢያወጡም ዘገባው በተሰራጨበት ወቅት ላቭሮቭ ገና አዲስ አበባ እንኳ አልገቡም ነበር፡፡ በይቅርታው ጉዳይም ቢሆን መገናኛ ብዙሃኑ እንደተመኙት የቲለርሰንን ምላሽ ማግኘት አልቻሉም፡፡ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐሙስ የካቲት 29 ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ የጋራ መግለጫ ለመስጠት ጋዜጠኞች ፊት ሲቀርቡ የይቅርታው ጉዳይ ከአንድም ሁለቴ ተነስቶባቸው ነበር፡፡ ቲለርሰን ጥያቄውን ቢሸሹም በትራምፕ አገላለጽ በመበሳጨት መግለጫ ጭምር ያወጣው የአፍሪካ ህብረትን በሊቀመንበርነት የሚመሩት ሙሳ ፋኪ ግን ጉዳዩን “የውሾን ነገር ያነሳ” አይነት አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡ 

የቲለርሰን የአፍሪካ ጉብኝት የትራምፕ ጸያፍ ንግግር ጥላ ያጥላበት እንጂ ጉዞው ከታቀደ ቆየት እንዳለ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ “ለአፍሪካ የሰጠው ትኩረት አናሳ ነው?” በሚል የሚተቸው የትራምፕ አስተዳደር ይህንኑ ለመቀየር ተከታታይ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው መስከረም በኒውዮርክ ከተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ዘጠኝ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችን ምሳ ጋብዘው አነጋግረዋቸዋል፡፡ 

በቀጣዩ ጥቅምት ወር ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኬ ሄሊ ወደ አፍሪካ በመምጣት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት ሀገራትን ጎብኝተው ተመልሰዋል፡፡ በህዳር ወር ቲለርሰን ቦታውን ተረከቡና የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርን ጨምሮ 37 አፍሪካ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ወደ ዋሽንግተን በመጋበዝ ውይይት አድርገዋል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ በአምስት የአፍሪካ ሀገራት እያደረጉ ያሉትን ጉብኝት ከኢትዮጵያ ጀምረዋል፡፡ ለመሆኑ ቲለርሰን ኢትዮጵያን የጎበኙት በሀገሪቱ ባለው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ነው ወይስ ሌላ? የዓለም አቀፍ ጉዳዮች የጥናት ተቋም በሆነው ቻታም ሀውስ የአፍሪካ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት አሌክስ ቫይንስ ምላሽ አላቸው፡፡ 

“የቲለርሰን የኢትዮጵያ ጉዞ በዋናነት ለአፍሪካ ህብረት የተደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ጠቃሚ የመልህቅ ሀገር ተደርጋ በአሜሪካውያኑ የምትታይ ናት፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ተግባራዊ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአሜሪካውያኑ አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው” ብለዋል ቫይንስ።      
በእርግጥም አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንደሚያሳስባት ቲለርሰን ከኢትዮጵያ አቻቸው ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ቀውስ እና አመጽ ማስወገድ የሚቻለው ለሀገሪቱ ህዝብ ሰፊ ነጻነት ሲሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

Äthiopien Besuch russischer Außenminister Sergei Lawrow mit Workneh Gebeyehu
ምስል picture-alliance/dpa/A. Shcherbak

የቲለርሰን ንግግር በተከታዩ ቀን በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር ከተገናኙት የሩሲያው ላቭሮቭ ጋር የአካሄድ ልዩነት የተንጸባረቀበት ነበር፡፡ ላቭሮቭ ትላንት አርብ ከዶ/ር ወርቅነህ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ስለ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተጠይቀው ሲመልሱ “በኢትዮጵያ ያለው የወቅቱ ፖለቲካ ሁኔታ የሀገሪቱ ህዝቦች ጉዳይ ነው” ሲሉ ሀገራቸው በዚህ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባ ተናግረዋል፡፡ ላቭሮቭ የሀገራቸውን “ጣልቃ ያለመግባት መርህ” የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በጀመሩባት የአንጎላዋ መዲና ሉዋንዳ ላይም አጽንኦት ሰጥተውበት ነበር፡፡ 

የቻታም ሀውሱ አሌክስ ቫይንስ የላቭሮቭ የኢትዮጵያ ጉዞ ከቲለርሰን የተለየ አጀንዳ ያነገበ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከቲለርሰን ጋር የሚጋሩት በኢትዮጵያ መቀመጫውን ያደረገውን የአፍሪካ ህብረት በሀገሪቱ በነበራቸው ጉብኝት ታሳቢ ማድረጋቸው እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ 

“ላቭሮቭ ወደ ኢትዮጵያ የሄዱበት ዋነኛው ምክንያት የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተበት 120ኛ ዓመት መታሰቢያ በመሆኑ የሁለትዩሽ ግንኙነቱን ለማክበር ነው፡፡ ሰፋ ባለ መልኩ ደግሞ ይበልጥ ስለ ሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮች፣ ቀጠናዊ ጉዳዮች እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር መነጋገር ስለፈለጉ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት 60 በመቶው ስራ በአፍሪካ ውስጥ መሆኑ ታሳቢ ሲደረግ ይህ ሊገርም አይገባም፡፡ እናም ላቭሮቭ በአፍሪካ ህብረት ባሰሙት ንግግር በጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ላይ እና አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት መቀመጫ እንዲኖራት ሩሲያ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል” ይላሉ ቫይንስ።

ላቭሮቭ በአፍሪካ ህብረት ቆይታቸው ሀገራቸው ለመላው አፍሪካ ስለምታደርገው ድጋፍ ቢገልጹም የአሁኑ ጉብኝታቸው ትኩረት የሰጠው ግን በደቡባዊ አፍሪካ ላሉ ሀገራት ሆኗል፡፡ ሰኞ አንጎላን እና ናሚቢያን፣ ረቡዕ ሞዛምቢክን፣ ሐሙስ ዚምባቡዌን አዳርሰዋል፡፡ ላቭሮቭ ለምን እነዚህን ሀገራት መረጡ? የቻታም ሀውሱ ቫይንስ ትንታኔ አላቸው፡፡ 

Angola | russischer Außenminister Lawrow mit Angolas Präsident Joao Lourenco
ምስል imago/ITAR-TASS/A. Shcherbak

“የላቭሮቭ  የደቡባዊ አፍሪካ ጉብኝት ከዚህ ቀደም ከሩሲያ ጋር ግንኙነቶች ካላቸው ሀገራት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የአንጎላ ግንኙነት ጥልቅ እና ትርጉም ያለው ነው፡፡ የወቅቱ የአንጎላ ፕሬዝዳንት ዡኣ ሎሬንሱ የከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሩሲያ ነው፡፡ ሩሲያ የሶቭየት ህብረት በነበረች ጊዜ በሌኒን ከፍተኛ አካዳሚ እስከ 1982 ነበሩ፡፡ ሩሲያውያን በአንጎላ መከላከያ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ አፍስሰዋል፡፡ የማዕድን ጥቅምም አላቸው፡፡ አልሮሳ ማዕድን የተባለው በአንጎላ ካሉ ትልልቅ የአልማዝ የማዕድን አውጪዎች አንዱ ነው፡፡ አንጎላ ባለፈው ዓመት የቴሌኮሚዩኑኬሽን ሳተላይት እንደታመጥቅ ጭምር ሩሲያ ረድታታለች፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ የናሚቢያ እና ሞዛምቢክም ስለ ነዳጅ ዲፕሎማሲ እና ስለ ማዕድን ሀብቶች ነው፡፡ ሩሲያውያኑ ዩራኒየም የሚያገኙባቸውን ምንጮች ማስፋት ይፈልጋሉ፡፡ ናሚቢያ ደግሞ ለዚያ ፍላጎት አላት፡፡ ሮስኔፍት [የሩሲያ ኩባንያ] አሁን በሞዛምቢክ ሁለት የነዳጅ ቦታዎች አሉት” ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ።

የላቭሮቭ የአሁኑ ጉብኝት ሩሲያ በሶቭየት ህብረት ጊዜ ጠንካራ ግንኙነት ከነበሯት ሀገራት ጋር ወዳጅነቷን ለማጠናከር እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የሩሲያ አካሄድ ከአሜሪካ የወቅቱ እንቅስቃሴ ጋር ሲዳመር ሁለቱ ሀገራት ቀዝቃዛው ጦርነት ተብሎ በሚታወቀው ወቅት በአፍሪካ የነበራቸውን እሽቅድምድም አስታውሷል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተመሳሳይ ወቅት በአህጉሪቱ መገኘት የሀገራቱ ፉክክር ነጸብራቅ ይሆን የሚል ጥያቄም ወልዷል፡፡ የቻታም ሀውሱ ቫይንስ “መቀናቀኑ ቢኖርም በቀጥታ ፉክክር አልገጠሙም” ባይ ናቸው፡፡ 

“ምናልባትም የተወሰነ የመቀናቀን ስሜት ይኖራል፡፡ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በተለያዩ የአመለካከት ነጥቦች ምክንያት በሩሲያ ፌዴሬሽን እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ጸቦች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁለት ጉዞዎች በትንሹም ቢሆን በትኩረታቸው ይለያያሉ፡፡ የሩሲያውያኑ ጉዞ ንግድ ያስቀደመ ነው፤ በትንሹ የመከላከያ ጉዳዮችም አሉበት፡፡ የአሜሪካውያኑ በአብዛኛው ስለ ሰላም እና ደህንነት ነው፡፡ አሜሪካ በጅቡቲ ትልቅ ወታደራዊ ሰፈር አላት፡፡ ቲለርሰን ወደ ሳህልም ይጓዛሉ፤ እንደ ቻድ ወዳሉ ሀገራት፡፡ ለአሜሪካውያኑ የደህንነት ጉዳይ ከሌሎች ነገሮችም በላቀ የሚያስበልጡት ነው፡፡ ያ ደግሞ ጽንፈኝነትን በተለይም እስላማዊ ጽንፈኝነትን መከላከል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ እንደማስበው ሁለቱን ጉዞዎች በተለያየ አመክንዮ መመልከት ትችላለህ፡፡ ጊዜያቸው የተገጣጠመ ቢሆንም ነገር ግን በቀጥታ እየተፎካከሩ አልነበረም” ሲሉ ቫይንስ ያጠቃልላሉ።

ተስፋለም ወልደየስ