1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መቼ ይጠናቀቃል?

ማክሰኞ፣ መጋቢት 19 2009

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚያዚያ ወር የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት 6ተኛ ዓመቱን ይደፍኗል። ከመነሻዉ ሲታቀድ በ 5 ዓመታት ይጠናቀቃል የሚል ቢሆንም ግድቡ በአሁኑ ወቅት 56 በመቶ ብቻ መጠናቀቁን መንግስት ገልጿል።

https://p.dw.com/p/2aA47
Nil Dammbau in Äthiopien Archiv 28.05.2013
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

Why is GERD delayed? - MP3-Stereo

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁን የያዘዉን ስያሜ ከማግኘቱ በፊት  «የሚሊኒየም ግድብ» በሚል በመጋቢት ወር 2003 ዓ,ም በቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የመሠረት ድንጋዩ ከተቀመጠ ስድስተኛ ዓመቱን ዘንድሮ ያዘ። የግድቡ ግንባታ በአብዛኛዉ  ኢትዮጵያዊ  ዘንድ ድጋፍ ቢቸረዉም፤ እቅዱ ይፋ የሆነዉ የፀደዩ  የአረብ አብዮት በተቀጣጠለበት ወቅት በመሆኑ በአንዳንዶች ዘንድ የሕዝቡን ትኩረት ወደ ሌላ አቅጣጫ ለማዞር የታሰበ ተደርጎ ተወስዶ ነበር።

የግንባታዉ ወጭ  4 ,5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም  80 ቢሊዮን  የኢትዮጵያ ብር መሆኑና ይሄዉ ወጭ  የሚሸፈነዉ  ደግሞ  በሀገሪቱ  ሕዝብና መንግሥት ነዉ መባሉ ብዙዎችን ጥርጣሬ  ዉስጥ እንዲገቡ አድርጓል። በሌላ በኩል  ለዘመናት የአባይ  ዉኃ ዋነኛ ተጠቃሚ በሆነችዉ ግብፅ ዘንድም የዚህ ፕሮጀክት እቅድ በስጋትና በጥርጣሬ የሚታይ በመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ግድቡ በተፋሰሱ ሃገራት ላይ የሚያመጣዉ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነዉ በሚል ሁለቱ ሃገራት  በገለልተኛ ወገን እንዲጠና ስምምነት እስከደረሱበት ያለፈዉ ዓመት ድረስ፤ አቤቱታ ስታሰማ ቆይታለች። ያም ሆነ ይህ ግን የግንባታዉ ሥራ ለአፍታም እንዳልተቋረጠ እየተነገረ  6ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል።

የግድቡ ግንባታ ቀደም ብሎ  ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት እየተገባደደ እንደሚሄድ ነበር የተነገረዉ። የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ተግባርም በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት እንደሚጀምርም እንዲሁ። ከሰሞኑ የተሰማዉ ደግሞ የተጠናቀቀዉ 56 በመቶዉ ብቻ መሆኑን ያሳያል። እቅዱ ከመነሻዉ በጎርጎሮሳዊዉ 2017 ዓ,ም ይጠናቀቃል የሚል ቢሆንም። ለመሆኑ በእቅዱ መሰረት ለምን አልተጠናቀቀም? የኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሞሀመድ ሰኢድ እንደገለጹት ግድቡ ሲጀመር በ 5 አመታት ዉስጥ ይጠናቀቃል የሚል እቅድ የተያዘዉ  5500 ሜጋዋት ያመነጫል በሚል ሲሆን፤ በሂደት ግን እያደገ መጥቶ ከ6000 በላይ ሜጋዋት ላይ በመድረሱ በወረቀት ሰፍሮ የነበረዉ እቅድ በተግባር የተለዬ ሊሆን ችሏል ብለዋል።መቼ ይጠናቀቃል? ለሚለዉ ጥያቄ ግን «በቅርቡ» ከማለት ዉጭ ቁርጥ ያለ ቀነ ገደብ ሀላፊዉ አላስቀመጡም።

Äthiopien Grand Renaissance Staudamm al-Sisi al-Bashir Desalegn
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ 6000 በላይ ሜጋ ዋት የኤለክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ነዉ የሚጠበቀዉ። ሥራዉ ሲያልቅም ፤ 1,800 ሜትር ሥፋት እና፤ 155 ሜትር ከፍታ ያለዉ፤ 74 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ዉኃ የመያዝ አቅም ያለዉ ከአፍሪቃም ተወዳዳሪ የሌለዉ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ እንደሚሆን ግንባታዉን የሚያከናዉነዉ ሳሊኒ የተሰኘዉ ኩባንያ በድረገጹ ያሰፈረዉ መረጃ ያመለክታል። ግድቡ የኃይል ማመንጨት ሥራዉን ሲጀምር ለኢትዮጵያ የሚሰጠዉ ጥቅም ጥያቄ ባያስነሳም ሳሊኒ የተባለዉ የጣሊያን ኩባንያ  ያለ ጨረታ ግንባታዉን እንዲያካሂድ መደረጉ አግባብ አይደለም በሚል በዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ አሁንም ድረስ ይተቻል።የህዝብ ግንኙነት ሃፊዉ አቶ መሀመድ ሰኢድ ግን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ እንድትለማ የማይፈልጉና ጥቅማችን ይነካል የሚሉ ሀይሎች  ትችት ነዉ ብለዋል።

በቤንሻንጉል ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጉባ ወረዳ ሲርባ በተባለ ቦታ እየተገነባ ያለዉ ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ተሰርቶ ሲጨናቀቅ 187 ሺህ 400 ሄክታር መሬት የሚሸፍን 246 ኪሜ  ሰዉ ሰራሽ ዉኃ የሚፈጥር ሲሆን፤ ግድቡ በትልቅነቱም ከአፍሪካ 1ኛ ሲሆን ከዓለም 8ኛ ይሆናል።

 

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ