1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታቸር ጠንካራዋ የብሪታኒያ ጠ/ሚኒስትር

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 1 2005

በብሪታኒያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ፥ በዚሁ ሥልጣን ረዥም ጊዜ በመቆየትም እንዲሁ የመጀመሪያዋ የብሪታኒያ መሪ ነበሩ ፣ ትናንት በ87 አመታቸው ያረፉት የቀድሞዋ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርግሬት ታቸር ።

https://p.dw.com/p/18Cco
ARCHIV - Die ehemalige britische Premierministerin Margaret Thatcher am 6.10.1999 auf dem Jahreskongress der konservativen Partei in Blackpool. Der Falkland-Krieg zwischen Argentinien und Großbritannien war auch der Konflikt zweier schillernder Staatsleute: Die für ihre Unnachgiebigkeit berühmt gewordene Premierministerin Margaret Thatcher und Argentiniens Junta-Chef Galtieri. (zu Themenpaket Falkland) +++(c) dpa - Bildfunk+++
Bildergalerie Margaret Thatcher Archiv 06.10.1999ምስል picture-alliance/dpa

ትናንት ላረፉት ለቀድሞዋ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርግሬት ታቸር የመጨረሻ ስንብትና የቀብር ስነስርዓት ዝግጅት ተጀምሯል ። የመጨረሻው ስንብትና የቀብር ስነርስርዓቱም የዛሬ ሳምንት ረቡዕ እንደሚከናወን የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ቢሮ አስታውቋል ። የብሪታኒያ ፓርላማ አባላት ለታቸር በመንግሥት ደረጃ ለመሪዎች የሚደረግ ስንብት እንዲደረግላቸው ቢጠይቁም የታቸር ቃል አቀባይ ግን ይህ እንዲደረግ እንደማይፈልጉ ታችተር በህይወት ሳሉ ማስታወቃቸውን ተናግረዋል ። ቀዝቃዛው ጦርነት እንዲያበቃ እገዛ ባደረጉት በታቸር ሞት የአለም መንግሥታት የተሰማቸውን ሃዘን በመግለፅ ላይ ናቸው ። በብሪታኒያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ፥ በዚሁ ሥልጣን ረዥም ጊዜ በመቆየትም እንዲሁ የመጀመሪያዋ የብሪታኒያ መሪ ነበሩ ፣ ትናንት በ87 አመታቸው ያረፉት የቀድሞዋ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርግሬት ታቸር ። በጠንካራ አመራራቸውና በቆራጥነታቸው ከቀደሙት ወንድ አቻዎቻቸው የላቀ ቦታ የሚሰጣቸው ታችተር በ20ኛው ክፍለ ዘመን ባራመዱት ፖለቲካ ዝናቸው በአለም ዙሪያ ናኝቷል ። በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 4 1979 ነበር የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መንግሥት የመሰረቱት ።
«ግርማዊት ንግሥት አዲስ መንግሥት እንድመሰርት ጠይቀውኛል። ይህንንም ተቀብየዋለሁ »
ወግ አጥባቂዋ ታችተር እጎአ በ1979 በተካሄደ ምርጫ በብሪታኒያ የተፈጠረውን የኢንዱስትሪ አለመረጋጋት ችግር ማስወገድ ያቀተውን በሌበር ፓርቲ የሚመራውን መንግሥት አሸንፈው ነበር ለሥልጣን የበቁት ። ታችተር በሥልጣን ዘመናቸው ታቸሪዝም የሚል መጠሪያ በተሰጠው ፤የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ ፣ የመንግሥት ንብረቶችን ወደ ግል ይዞታዎች በማዛወር ነፃ ኤኮኖሚን በማራመድ እንዲሁም የገንዘብ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ባተኮረው መርሃቸው ይታወቃሉ ። በርሳቸው ዘመን ወደ ግል ይዞታ ከተዛወሩት በርካታ ኩባንያዎች መካከል የብሪታኒያ አየር መንገድና በእንግሊዘኛው ምህፃር BP በመባል የሚታወቀው የብሪታኒያ ነዳጅ ዘይት ኩባንያ ይገኙበታል ።

Flash-Galerie Michail Gorbatschow 80. Geburtstag
ታቸርና ጎርባቾቭምስል AP
Die britische Premierministerin Margaret Thatcher, Bundeskanzler Helmut Kohl und der US-amerikanische Präsident Ronald Reagan (l-r) am 3. Mai 1985 auf dem Weltwirtschaftsgipfel in Bonn.
ታቸር ኮልና ሬገንምስል picture-alliance/ dpa

በማያዳግም ውሳኔያቸውና በጠንካራ እርምጃዎቻቸው Iron Lady ብረቷ ሴት የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው ታቸር ብዙውን ጊዜ ለህዝብ አስተያየት እብዛም የማይጨነቁ ከዚያ ይልቅ በመርህና በአቋማቸው የሚፀኑ መሪ ነበሩ ።
ነገሮችን አድበስብሰው ማለፍ የማይሆንላቸው ሃሳባቸውን በቀጥታ ከመሰንዘር ወደ ኋላ የማይሉም ነበሩ ። ይህን ባህርያቸውም ከአባታቸው እንደወረሱት ይገመታል ። በአንድ ወቅት እንደተናገሩት አባታቸው ሁሌም የራሳቸውን ሃሳብ እንዲከተሉ ይመክሯቸው ነበር ።
« በልጅነቴ አባቴ ከሌላው ላለመለየት ብለሽ ብዙሃኑን እንዳትከተይ ፣ማድረግ የምትፈልጊውን ራስሽ ወስኚ ሲል በግልፅ ይነግረኝ ነበር ። »
ታቸር ዝና ይበልጡን የናኘው እጎአ በሚያዚያ 1982 በ ፎክላንድ ደሴት ሰበብ ብሪታኒያ ከአርጀንቲ ጋር ያካሄደችው ጦርነት በድል ከተጠናቀቀ በኋላ ነው ። ድሉ በአመቱ የተካሄደውን ምርጫ በሰፊው ለማሸነፍ አብቅቷቸዋል ። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አሜሪካን ብሪታኒያ ውስጥ የኒዩክልየር ሚሳይል እንድትተክል እስከመፍቀድ የደረሱ የያኔው የአሜሪካኑ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን ጥብቅ ወዳጅም ነበሩ ። በቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ የሶቭየት ህብረቱ መሪ ሚኻኤል ጎርባቾቭ አጋር የነበሩት ታቸር የጀርመን ውህደት ደህንነታችንን አደጋ ላይ ይጥላል ሲሉ ተቃውመው ነበር ።

David Cameron und Margaret Thatcher in der Downing Street
ታቸርና ካሜሩንምስል picture-alliance/photoshot

አሁን ወደ አውሮፓ ህብረትነት የተቀየረው የያኔው የአውሮፓ ማህበረሰብ ኃይል መጠናከሩን በ1990 ባደረጉት ንግግር አጥብቀው ተቃውመዋል ። ይህ ንግግራቸው በርካታ ባልደረቦቻቸውን ጭምር አስቆጥቶ ተዋቂ ሚኒስትሮቻቸውም እንዲነሱባቸው አድረገ ። ብዙም ሳይቆዩ ከሥልጣን ተሰናበቱ ። ቀጣዩ ምርጫ በተካሄደበት በ1992 ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ለቀቁ ። በቀጣዮቹ አመታት ሁለት ጊዜ ማስታወሻዎቻቸውን አሳትመዋል ። በታቸር ሞት በርክታ የአለም መንግሥታት ሃዘናቸውን ገልፀዋል ። ከነዚህም አንዱ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ናቸው ።
«ማርግሬት ታችተር በህይወት ዘመናቸው ላከናወኗቸው በርካታ ተግባራት እናመሰግናቸዋለን ። በዚህ ሰአት ለሚሰማን የአውሮፓውያን አንድነት መንፈስ ለአውሮፓ ታሪክና ለአለም ትተዉት ባለፉት ታላቅ ሥምና ዝናቸውም እናደንቃቸዋለን ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ