1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታኅሣሥ 18 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2014

ቸልሲ እና ሊቨርፑል ለእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ዛሬ ማታ ማንቸስተር ዩናይትድ ከኒውካስትል ጋር ይጋጠማል። ሁለተኛው ዙር የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድሮች በልውጡ ኦሚክሮን ተሐዋሲ የተነሳ ያለተመልካቾች እንደሚከናወኑ ተገልጧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን የተመለከተ ዘገባ እና የአትሌቲክስ ዜናም አካተናል።

https://p.dw.com/p/44sSe

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ቸልሲ እና ሊቨርፑል ለእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ዛሬ ማታ ማንቸስተር ዩናይትድ ከኒውካስትል ጋር ይጋጠማል። ሁለተኛው ዙር የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድሮች በልውጡ ኦሚክሮን ተሐዋሲ የተነሳ ያለተመልካቾች እንደሚከናወኑ ተገልጧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን የተመለከተ ዘገባ እንዲሁም የአትሌቲክስ ዜናም አካተናል።

አትሌቲክስ

ከታኅሣሥ 13-17 ቀን፣ 2014 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሲከናወን የቆየው የኢትዮጵያ የአጭር፣ መካከለኛ፣ የ3000ሜትር መሠናክል፣ የርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት ተጠናቋል። ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተከናወነው በዚህ ፉክክር 27 ቡድኖችና 767 አትሌቶች ተሳታፊ እንደነበሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል።

በውድድሩ መጠናቀቂያም በሴቶች አጠቃላይ ፉክክር መከላከያ 210.5 ነጥብ በማግኘት አንደኛ ወጥቷል። በዚህም የዋንጫ ተሸላሚ መኾን ችሏል። 116.5 ነጥብ መሰብሰብ የቻለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።  ኢትዮ ኤሌትሪክ ቡድን በበኩሉ በ66.5 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

በወንዶች አጠቃላይ ፉክክርም መከላከያ 138.5 ነጥብ በመሰብሰብ በአንደኛነት የዋንጫ ተሸላሚ መኾን ችሏል። ሲዳማ ቡና በ129.5 ነጥብ የሁለተኛ ደረጃን ይዟል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ106.5 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። በአጠቃላይ ሴቶችና ወንዶች ድምር ውጤት መከላከያ 349 ነጥብ በመሰብሰብ የዋንጫ ተሸላሚ ኾኗል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ223 ነጥብ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሲዳማ ቡና በአጠቃላይ 186 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ማጠናቀቁን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

መሰል ፉክክሮች በአብዛኛው በረዥም ርቀት ውጤቶች ላይ የተወሰነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በአጭር ርቀት ዙሪያም ራሱን ለመፈተሽ ያስችለዋል ተብሏል። በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው የኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው መጽሄት የስፖርት አምድ አዘጋጅ ዐቢይ ወንድይፍራው ፉክክሩን በስፍራው በመገኘት ተከታትሏል። መሰል ውድድር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ራሱን እንዲመለከትበት ዕድል ሰጥቶታል ብሏል።

በጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ዋዜማ ስፔን ባርሴሎና ውስጥ በሚከናወነው የላ ኩርዛ ዴል ናሶስ የ5 ሺህ ሜርትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እጅግ ይጠበቃሉ። በውድድሩ ያሸንፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ጥቂት ወንድ አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያዊው አትሌት ብርሃኑ አረጋዊ ይገኝበታል። ብርሃኑ ከአንድ ወር ከዐሥራ አምስት ቀን በፊት ፈረንሳይ ውስጥ በተከናወነው እና 12:52 በመሮጥ የግሉን ምርጥ ሰአት ባስመዘገበበት የሊል የ5 ሺህ ሜርትር የሩጫ ፉክክር አንደኛ መውጣቱ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ ርቀት የሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ እንደምትጠበቅ ተዘግቧል። አትሌት እጅጋየሁ የምንጊዜም አምስተኛው ምርጥ የተባለ ሰአቷን 14: 14 በመሮጥ ያስመዘገበችው በሰኔ ወር ኔዘርላንድ ውስጥ በተከናወነው ፉክክር ነው። ለስዊድን የምትሮጠው ምዕራፍ ባህታ በዚህ ውድድር ላይ ያሸንፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ጥቂት አትሌቶች አንዷ ናት። ከዚህ ቀደም ያስመዘገበችው ምርጥ ሰአቷም 15:31 ሲሆን፤ ከእጅጋየሁ አንድ ደቂቃ ከ17 ሰከንድ የዘገየ ነው።  እንደተለመደው ሁሉ ባርሴሎና የዓመቱ የስፖርት ክንውኗን በዚህ የላ ኩርዛ ዴል ናሶስ የሩጫ ፉክክር በመዝጋት የጎርጎሪዮሱን 2021 ለመሰናበት መዘጋጀቷም ተዘግቧል።   

Äthiopien Fußball Nationalmannschaft
ምስል ISSOUF SANOGO/AFP

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚከናወነው 33ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ እሑድ ታኅሣሥ 17 ቀን፤ 2014 ዓ.ም. ወደ ያውንዴ ከተማ አቅንቷል። የልዑክ ቡድኑ ትናንት ከቀትር በኋላ ካሜሩን ዱዋላ ከተማ ደርሶ ለአንድ ሰዓት ከቆየ በኋላ 10:30 ገደማ ነበር ወደ ያውንዴ ያመራው። እዚያም ብሔራዊ ቡድኑ አመሻሹ ላይ የመጀመርያ ቀለል ያለ ልምምዱን ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጧል።  

የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ፉክክር ከሁለት ሳምንት በኋላ በአዘጋጇ ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ካሜሩን ውስጥ ይጀምራል።  የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እስከ ሁለት ቀጣይ ሣምንታት ድረስ ከቡድኑ ውጪ ከሚገኙ ቢያንስ ሁለት ቡድኖች ጋር የአቋም መፈተሺያ ግጥሚያዎችን እንደሚያከናውንም ገልጧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተደለደለው አዘጋጇ ካሜሩን በምትገኝበት ምድብ ሲሆን፤ ቡርኪናፋሶና ኬቨርዴም ይገኙበታል። ዋሊያዎቹ የሚገኙበት ምድብ የሞት ምድብ በመባልም ይታወቃል።  ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪቃ ዋንጫ የምድቡ የመጀመሪያ ግጥሚያውን የሚከናውነው እሁድ ጥር አንድ ቀን ከኬቬርዴ ቡድን ጋር ነው። ከዚያም ሐሙስ ጥር አምስት ቀን ከአዘጋጇ ካሜሩን ጋር ይፋለማል። ሰኞ ጥር 9 የምድቡ ሌላኛው ብርቱ ቡድን ቡርኪናፋሶም ይጠብቀዋል። ብሔራዊ ቡድኑ ከምድቡ ማለፍን ቀዳሚው ግቡ አድርጎ ወደ ካሜሩን መጓዙም ተገልጧል።  

ፕሬሚየር ሊግ

ማንቸሰተር ሲቲ ትናንት ቀበሮዎቹን 6 ለ3 ድል በማድረግ የደረጃ ሰንጠረዡን በ6 ነጥብ ልዩነት መምራት ችሏል። በእርግጥ ተከታዩ ሊቨርፑል አንድ ተሰተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ወደ ኢትሃድ ስታዲየም ያቀኑት ላይስተር ሲቲዎች ረፍት የወጡት 4 ለ0 በመመራት ነበር። ከእረፍት መልስ ግን ያገኙዋቸውን አጋጣሚዎች ወደ ተግባር በመቀየር ወጤቱን እስከ 69ኛው ደቂቃ ድረስ 4 ለ3 ማድረግ ተሳክቶላቸው ነበር። ጨዋታውን በፍጥነት መቆጣጠር የቻሉት ማንቸስተር ሲቲዎች ግን ሁለት ተደጋጋሚ ግቦችን በማስቆጠር ጨዋታው 6 ለ3 ተጠናቋል። በዚህም የአሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ልጆች ነጥባቸውን 47 አድርሰዋል።

Champions League - Group A - Manchester City v Club Brugge
ምስል JASON CAIRNDUFF/Action Images via Reuters

ለማንቸስተር ሲቲ ኬቪን ደ ብሩይነ የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው ጨዋታው በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በ14ኛው ደቂቃ ላይ ሪያድ ማህሬዝ በፍፁም ቅጣት ምት 2ኛዋን ግብ አስቆጥሯል። ኢካይ ጉንዶዋን 21ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛውን ከመረብ አሳርፏል። 25ኛው ደቂቃ ላይም ራሂም ስትርሊንግ 4ኛውን ያስቆጠረው በፍፁም ቀጣት ምት ነው።

ከእረፍት መልስ ላይስተር ሲቲዎች በ55ኛው ደቂቃ በጄምስ ማዲሰን፤ 59ኛው ደቂቃ ላይ ደገሞ በአዴሞላ ሎክማን ሁለት ግቦችን አከታትለው ማስገባት ችለው ነበር። 65ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞው የማንቸስተር ሲቲ አጥቂ ኬሌቺ ኢሃናቾ ያሰቆጠረው ሦስተኛ ግብ ማንቸስተር ሲቲዎችን ያስደነገጠ ነበር። 69ኛው ደቂቃ ላይ አይመሪች ላፖርቴ፤ 87ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ራሂም ስተርሊንግ በፍፁም ቀጣት ምት ከመረብ በማሳረፍ ጨዋታው በማንቸስተር ሲቲ የበላይነት ተጠናቋል።

ማንቸስተር ሲቲዎች ለሚቀጥለው ግጥሚያ የፊታችን ረቡዕ ወደ ብሬንትፎርድ ሲያቀኑ በተከታታይ 10ኛ ድላቸውን ለማስመዝገብ በማለም ነው። የቸልሲ ጀርመናዊ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል በፕሬሚየር ሊጉ የጨዋታ ድልድል ከፍተኛ ቅሬታ እንዳላቸው ይፋ አደረጉ። ከእሳቸው ቀደም ሲል ሌላኛው ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣን ዬርገን ክሎፕምበኮሮና ወቅት የፕሬሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን የጨዋታ ድልድል እና ሽግሽግ ፍትሃዊነት ነቅፈዋል።

በገና ማግስት በተለምዶ ሠራተኞች ከአሠሪዎቻቸው ሥጦታ በሚያገኙበት ቀን (Boxing Day) ቡድናቸው ቸልሲ አስቶን ቪላን 3 ለ1 ቢረታም አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል ግን ቁጣቸውን ገልጠዋል። የቁጣቸው ምንጩ ሌሎች በርካታ ቡድኖች በኮቪድ ሥርጭት የተነሳ ጨዋታቸው ለሌላ ጊዜ ሲሸጋገር ቸልሲ ያን ዕድል አለማግኘቱ ነው። ቡድናቸው ውስጥ ወሳኝ ተጨዋቾች በኮቪድ ምክንያት ባለፉት ጊዜያት መሰለፍ አልቻሉም ነበር። ካሉም ሑድሰን-ኦዲዮ እና ሮሜሉ ሉካኩ በኮሮና የተነሳ መሰለፍ አልቻሉም ነበር። በኮሮና ምክንያት ከቡድኑ ርቆ የነበረው አጥቂው ሮሜሉ ሉካኩ በትናንቱ ግጥሚያ ግብ በማስቆጠር የማሸነፊያ ፍጹም ቅጣት ምትም አስገኝቷል። ጀርመናውያን አጥቂዎቹ ካይ ሐቫርትስ እና ቲሞ ቬርነር አሁንም አይሰለፉም። ተከላካዩ ቲያጎ ሲልቫ እንዲሁም አማካዩ እንጎሎ ካንቴ ቪላ ፓርክ ላይ ድል በተጎናጸፉበት ወቅት ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአሰልጣኙ ንዴት የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው።

Fußball | Premier League | Leicester City - Chelsea | N'Golo Kante
ምስል Graham Wilson/Action Plus/picture alliance

የሠማያዊዎቹ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል፦ «የሆኑ ጽ/ቤቶች ውስጥ በአረንጓዴ ምንጣፍ ሶፋዎች ላይ የተቀመጡ» ሲሉ የነቀፏቸው የፕሬሚየር ሊግ አዘጋጆች አድሎ ፈጽመዋል ብለዋል። «እኛ ለ10 ቀናት ሙሉ አልጋ ውስጥ በነበርንበት ወቅት ጨዋታ ተሸጋሽጎላቸው ለ1 ሳምንት ልምምድ ሲያደርጉ ከነበሩ ቡድኖች ጋር እንድንጫወት መደረጉ ፍትሃዊ አይደለም» ሲሉ ኮንነዋል።

ልክ እደሳቸው ሁሉ የሊቨርፑል አሰልጣኝም ቡድናቸው በተከታታይ እንዲጫወት መደረጉን ወቅሰው ነበር። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ እስካሁን ድረስ 15 የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች በኮሮና የተነሳ ለሌላ ጊዜያት ተሸጋሽገዋል። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ቸልሲ ስምንቱንም ጨዋታዎቹን በሙሉ አከናውኗል። ከነጌ በስትያ ማታ ደግሞ ብራይተንን በሜዳው ስታንፎርድ ብሪጅ ይገጥማል። ብራይተን ትናንት ብሬንትፎርድን 2 ለ0 ድል አድርጓል።  ሳውዝሀምፕተን ዌስትሀም ዩናይትድን 3 ለ2 አሸንፏል። ቸልሲ 41 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሠንጠረዡ ሊቨርፑልን በመከተል 3ኛ ላይ ይገኛል።

ትናንት ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ሊያካኼድ የነበረው አንድ ተስተካካይ ግጥሚያውን ነገ ማታ የሚያደርገው ሊቨርፑል በ41 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በምድቡ የመጨረሻ ረፍድ 20ኛ ላይ የሚገኘው ኖርች ሲቲን ትናንት 5 ለ0 ማንኮታኮት የተሳካለት አርሰናል 35 ነጥብ አለው።  እንደ ኖርዊች ሲቲ ሁሉ ኒውካስል ዩናይትድ 10 ነጥብ ይዞ 19ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ተስተካካይ ጨዋታውን ዛሬ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያከናውናል።   በርንሌይ በ11 ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡንደስሊጋ

የዘንድሮ የየጀርመን ቡንደስሊጋ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ተጠናቋል። እስካሁን በተደረጉ 17 ዙር ግጥሚያዎች የመጀመሪያውን ዙር በ43 ነጥብ መሪ ኾኖ ያጠናቀቀው እንደተለመደው ባየርን ሙይንሽን ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮም የባየርን ሙይንሽን ተከታይ ቢሆንም ከመሪው በ9 ነጥቦች ይበለጣል።  

Deutschland Coronavirus Fußball Geisterspiel Würzburger Kickers vs. TSV 1860 Muenchen
ምስል Julien Christ /Beautiful Sports/imago images

ለገና ሰሞን እና ለአዲስ ዓመት ዝግ ሆኖ የሚቆየው የጀርመን ቡንደስሊጋ የዐርብ ሳምንት ማታ ዳግም ይጀምራል። በዕለቱ የቡንደስሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ መሪ ባየርን ሙይንሽን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን ይገጥማል። ቦሩስያ ሙይንሽን ግላድባኅ ከመሪው ባየርን ሙይንሽን በ24 ነጥብ ተበልጦ በያዘው 19 ነጥቡ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡንደስ ሊጋው ሁለተኛ ዙሩ ሲጀምር ግን በኦሚክሮን ተሐዋሲ የተነሳ ጨዋታዎች የሚከናወኑት በባዶ ስታዲየሞች ያለተመልካቾች መሆኑም ታውቋል። ጀርመን ውስጥ ከነገ ጀምሮ በየግዛቶቹ የሚከናወኑ የስፖርት እንቅስቃሴዎች፤ የባሕል እና በርካታ ሰዎች ሊሰበሰቡባቸው የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ያለ ተመልካቾች እንዲከናወኑም ተወስኗል። ይህንኑም ባለፈው ማክሰኞ የጀርመን መራኄ-መንግሥት ኦላፍ ሾልትስ ዐስታውቀዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ