1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታዳሽ የኃይል ምንጭ ለአፍሪቃ፧

ሰኞ፣ ኅዳር 16 2000

ሲሦው የዓለም ህዝብ፧ ከ ሁለት ቢሊዮን በላይ የሚሆነው ማለት ነው፧ ገና የዘመናዊ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚ ለመሆን አልቻለም። መለስተኛም ቢሆን፧ የዚህ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚ መሆን እስካልተቻለ ድረስ፧ ማንኛውም የዕድገት ሂደት ተሰናክሎ የሚቀር ይሆናል።

https://p.dw.com/p/E0mn
የአቶም ኃይል ማመጫ አውታር፧ በደቡብ አፍሪቃና የአየር ብክለት፧
የአቶም ኃይል ማመጫ አውታር፧ በደቡብ አፍሪቃና የአየር ብክለት፧ምስል AP
ጀርመን በአሁኑ ጊዜ.፧ በ 45 አዳጊ አገሮች፧ በ 1.6 ቢልዮን ዩውሮ፧ የኃይል ምንጭ ፕሮጀክቶችን ትደግፋለች። አብዛኛው ገንዘብ ወጪ የሚደረገው «ታዳሽ« ለሚሰኘው የኃይል ምንጭ ነው። ከዚህ በጣም አነስ ባለ ደረጃ ለአፍሪቃ የኃይል ምንጭ እንዲቀርብ የሚጥሩ አንድ፧ በሃምበርግ የሚኖሩ አዛውንት ጀርመናዊ ኢንጅኔር አሉ። Johann Bormann የሚባሉ! በዚህ ሳምንት በተከታታይ ከሚቀርበው ከአየር ንብረት ጋር ከተያያዘው ዝግጅታችን ለዛሬ፧ በእኒህ ግለሰብ ጥረት ላይ ያተኮረውን ይሆናል የምናሰማችሁ። የዶቸ ቨለ ባልደረባ Jörn Iken ለጻፈው ሐተታ፧ ተክሌ የኋላ.......
Johann Bormann ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከ ኻያ ዓመት በላይ ተቀምተዋል። ከብዙ ሰዎች ጋር ትውውቅ አላቸው። አንዳንዴም የደቡብ አፍሪቃ የኅብረሰተሰብ አባል እንደሆኑ ይሰማቸዋል። አሁን የ68 ዓመት አዛውንት ቢሆኑም፧ ሸንቀጥ ያሉ፧ ፍጹም ጤናማ ሰው በመሆናቸው፧ ሥራቸውን በትጋት ነው የሚያከናውኑት። ቦርማን፧ ለጀርመን ኢንዱስትሪዎች፧ በውጭ ሀገር፧ የኢንዱስትሪ አማካሪና የፕሮጀክት ቀያሽ በመሆን አገልግለዋል። በተለይ በመገናኛ ረገድ፧ በእስያና አፍሪቃ፧ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስወጡ ፕሮጀክቶች እንዲነደፉ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችን አመኔታ ያተረፉ መሆናቸው የሚነገርላቸው፧ አዛውንቱ ቦርማን፧ በአሁኑ ጊዜ፧ የጀርመን ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች፧ አፍሪቃና እስያ ውስጥ፧ በገጠር፧ በየቦታው አነስተኛ የኤልክትሪክ ኃይል ማመንጫ አውታሮችን እንዲተክሉ ከማባበል አልቦዘኑም። በአውሮፓና በአሜሪካ እንደተለመደው፧ ለአፍሪቃና እስያ፧ ማዕከላዊ የኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ አውታር ሳይሆን፧ ለመንደሮች የሚሆን በየቦታው ራሱን ችሎ የሚተከል የኃይል ማመንጫ አውታር ነው የሚያስፈልገው።
(4) «አንድ የተለመደ ፕሮጀክት ለምሳሌ፧ እዚህ ላይ፧ ራሱን የቻለ የኃይል ማመንጫ አውታር በመዘርጋት፧ ውሃ እንዲያስገኝ፧ የባህር ውሃም ከሆነ፧ ከጨው እንዲያጠራ በማድረግ፧ በዲዘል በሚሠራ ሞተር መጠቀም ይቻላል። ዲዘሉን ሙሉ በሙሉ ሳይሆን ግማሽ በግማሽ ብቻ፧ ወይም ሲሦውን መጠቀም ይቻላል።«
ከፀሐይና ነፋስ ኃይል ሌላ፧ የዲዜሉን ሞተር ለሁለገብ አገልግሎት በማዋል፧ የቆዩ፧ ያረጁ ሞተሮችን ማስወገድ ይቻላል። የዴዜሉ ሞተር ልክ እንደ አቶም ኃይል ማመንጫ አውታር ይሆናል የሚያገለግለው።
(5)«በመሠረቱ፧ ይህን የመሰለው በዲዜል የሚሠራ የኃይል ማመንጫ አውታር፧ ኃይል መሥጠት ብቻ ሳይሆን ማሞቂያም ሆኖ የሚያገለግል ነው። ከዚህ በተረፈ ውሃ ከጉድጓድ ለመቅዳት፧ በቧንቧ ለመሳብ፧ ለሌሎች በኤልክትሪክ ለሚሠሩ ለመብሻና ለመሳሰሉ መሣሪያዎችም አገልግሎት ይሰጣል። ይህ ሲሆን፧ ለሰዎች የሥራ በር ይከፍታል፧ የገቢ ማስገኛም ይሆናል። መኖሪያ፧ በውቅያኖስ ዳር ከሆነ፧ ጨው የበዛባትን የውቅያኖስ ውሃ ከጨው ማጥራት ይቻላል። ለግብርና እዚህም ላይ ለመስኖ የሚበጁ መሣሪያዎችንም በማንቀሳቀስ አገልግሎት መስጠት ይችላል።«
Johann Bormann የገጠር አካባቢዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ የሚለውን ብዙ ውይይት የተደረገበትን መርኀ-ግብር አይቀበሉትም። አውሮፓውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት ሲሉ፧ በመጀመሪያ የሚታያቸው በራዲዮ፧ በቴሌቭዥን እንዲሁም፧ በምግብና መጠጥ ማቀዝቀዣ መሣሪያ፧ መጠቀም መቻላቸውን ነው። ቦርማን ከዚያ የላቀና ጠቀሜታ ያለው፧ የአንድን አካባቢ ኤኮኖሚ በኃይል ምንጭ ማንቀሳቀስ መቻሉ ነው፧ ይላሉ።
(6)«ከማዕከላዊነት ተላቆ፧ በየአካባቢው ራሱን ችሎ የሚተከል የኃይል ማመንጫ አውታር፧ በመጀመሪያ ህዝብን፧ ኑዋሪዎችን የሚጠቅም ነው። አለኝታ የሚያሳድር፧ ሥራ ለመፍጠር የሚያስችል፧ ህዝቡም በአገሩ ተረጋግቶ ለመኖር የላቀ ትርጉም እንዲሰጥ ያደርጋል። ወደ አውሮፓ የመጓዝ ምኞትንም ሆነ ጥረትን፧ ለምሳሌ ያህል በግራን ካናሪያ ደሴቶች በኩል በጀልባ ለመግባት በየጊዜው የሚደረገውን ዓይነት፧ ጀብደኛና አደገኛ እርምጃ ይገታል። ህዝቡ፧ በመኖሪያ ሠፈሩ ኑሮውን የሚደግፍበት ብሩኅ ተስፋና ዕድል ሊኖረው ይገባል። ይህ ሊሠምር የሚችለው ደግሞ፧ በቂና ረከስ ባለ ዋጋ፧ የኃይል ምንጭና ውሃ ሲቀርብለት ነው።«
ዮኻን ቦርማን፧ የዓለም ባንክ፧ ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት የገንዘብ እርዳታ፧ የአውሮፓ የልማት ባንክ፧ የጀርመን የቴክኒክ ተራድዖና የመሳሰሉትም፧ ድጋፍ ስለሚሰጡ፧ የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች፧ እንደ ቦርማን አስተያየት መትጋት እንጂ ማመንታት አይገባቸውም።
በፀሐይ፧ በነፋስና በዲዝል ሞተር የሚንቀሳቀሱ አውታሮችን ጥቅም ላይ ለማዋል ተፈላጊ የሙያ ዕውቀት ያሻል። ይህ ደግሞ በዚያው በቦታው ሰዎች በማሠልጠን መፍትኄ ሊገኝለት የሚችል ነው። አውታሩን የሚሠሩ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆኑ፧ ለምሳሌ ያህል በደቡብ አፍሪቃ እንደሚታየው፧ Sustainable Village Africa የተሰኘው ዓይነት ድርጅቶችም አሉ። ማንኛውንም ማሺን፧ ሞተር፧ በገንዘብ መግዛት ይቻላል፧ ሞተሩ እንዴት እንደሚሠራ የሚያውቁት ሰዎች ግን፧ ቦርማን እንዳሉት፧ በመጀመሪያ ሥልጠና ማግኘት አለባቸው። አለበለዚያ አንዳች ነገር ማንቀሳቀስ አይቻልም።