1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታዳጊ አገሮችና የምዕራቡ ዓለም የንግድ ጫና

ሐሙስ፣ ሰኔ 23 1997
https://p.dw.com/p/E0eV

የሕብረቱ ሥራ አስፈጻሚ አካል የአውሮፓው ኮሚሢዮን ከሣምንት በፊት ያቀረበው የለውጥ ሃሣብ ከአፍሪቃ፣ ከካራይብና ከፓሲፊክ አካባቢ አገሮች የሚያስገባውን ነጭ ስኳር ዋጋ 39 በመቶ፤ የአገዳን ዋጋም በ 2006 እና 2008 መካከል 42 በመቶ የሚቆርጥ ነው።

በአውሮፓው ሕብረት ሥም የስኳር ዋጋን የሚቆርጠውን ጽንሰ-ሃሣብ ያቀረቡት የእርሻ ኮሜሣር ማሪያን ፊሸር ቦይል ለለውጡ ዕቅድ አንዳች አማራጭ የለም ሲሉ ነው ለዕርምጃው ቆርጠው መነሣታቸውን የገለጹት። በኮሜሣሩ አባባል እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ለአውሮፓውያን ስኳር አምራች ዘርፍ ቀስ በቀስ ግብዓተ-መሬቱን የማመቻቸትን ያህል ነው።

እርግጥ መፎካከር አቅቷቸው ዘርፉን መልቀቅ ለሚገደዱ የታዳጊው ዓለም አምራቾች ለውጡ የሚኖረውን ማሕበራዊና ኤኮኖሚያዊ ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ መዋቅራዊ ልገሣ እንደሚደረግ ቃል ተገብቷል። ለነዚሁ በአሕጽሮት ACP በመባል ለሚጠሩት የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሲፊክ አካባቢ ሃገራት ምርት አቅራቢዎች የሚሰጠው ልዩ የንግድ አስተያየትም ሆነ የገበያው ክፍት መሆን ቀጣይ ነው።

ሆኖም የታዳጊዎቹ አገሮች አስተያየት ከአውሮፓውያኑ አይጣጣምም። በነዚሁ አመለካከት አውሮፓውያኑ የተነሱለት ለውጥ በራስ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ነው። ለነገሩ በርካታ የ ACP አካባቢ አገሮች በለውጡ ሳቢያ ብርቱ ፈተና እንደተደቀነባቸው የአውሮፓው ሕብረት የልማትና የሰብዓዊ ዕርዳታ ኮሜሣር ሉዊስ ሚሼል እንኳ ሳይጠቅሱ አላለፉም። ቢሆንም ተያይዞ የወጣው የዕርዳታ ዕቅድ በአካባቢያቸው ልማት ላይ ያተኮረ የተረጋጋ ሽግግር እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል ሲሉ ሚሼልም እንደመሰሎቻቸው ለውጡን ማስቀደማቸው አልቀረም።

በአብዛኞቹ ስኳር አምራች ታዳጊ አገሮች የሕብረቱ የልማት ፖሊስ አንድ አካል ሆኖ የቀረበው የለውጥ ዕቅድ በአድልዎ ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም ባሻገር ከገበያ ውጡ ብሎ የማባረርን ያህል ነው የሆነው። እርግጥ ሕብረቱ በወቅቱ በአብዛኛው የቀድሞ የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶች ለነበሩት አገሮች የስኳር ምርት የሚከፍለው ዋጋ ከገበያው መጠን በላይ ከፍ ያለ ነው። እነዚሁ የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሲፊክ አካባቢ አገሮች ለሕብረቱ ገበዮች የሚያቀርቡት ስኳርም ከምርታቸው 70 በመቶውን ድርሻ ይይዛል።

አውሮፓውያኑ ለውጡን ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምሩ ወደ ሕብረቱ ገበያ በሚልኩት ምርት ላይ ጥገኛ የሆኑት ታዳጊ አገሮች ከባድ የኤኮኖሚ ችግር እንደሚገጥማቸው ነው የሚጠበቀው። አብዛኛውን ስኳር ከሚያመርቱት አገሮች መካከል ሞሪሺየስ፣ ስዋዚላንድ፣ ፊጂ፣ ጉዋያናና ጃሜይካ በቀደምትነት ይገኙበታል።

ችግሩ የተደቀነባቸው አገሮች ባለሥልጣናት የታሰበው ለውጥ የኤኮኖሚውን ድክመት ይበልጥ እንደሚያባብስና በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ የሥራ መስኮችንም አደጋ ላይ እንደሚጥል ይናገራሉ። በነዚሁ ግምት ለውጡ በያመቱ 487.4 ሚሊዮን ዶላር ገደማ የሚጠጋ ኪሣራን የሚያስከትል ነው የሚሆነው። በአንጻሩ ተጠቀሱት የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሲፊክ አካባቢ አገሮች በአንዳንዶቹ ዕለታዊው ነፍስ-ወከፍ ገቢ ሁለት ዶላር እንኳ አይሞላም።

በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ የሚባሉ ሃገራት አምባሣደሮችንና የስኳር ኢንዱስትሪ ተጠሪዎችን ያሰባሰበ አንድ ቡድን በበኩሉ የአውሮፓው ሕብረት ለውጥ በዓለም ላይ በዝቅተኛ ደረጃ የሚኖሩ ሕዝቦችን ለዘለቄታው ከድህነት ለማላቀቅ አንድ ሃያል ዕርምጃ ሊሆን እንደሚችል ያምናል። ሆኖም የአውሮፓው ኮሚሢዮን ጽንሰ-ሃሣብ የሕብረቱን የራስ ውስጣዊ ችግሮች ለመፍታት እንጂ ድህነትን ለማስወገድ የተወጠነ አይደለም ባይ ነው።

ቡድኑ ሚዛን በጠበቀ፤ ቀስ በቀስና አስተማማኝ ሆኖ በረጅም የሽግግር ጊዜ የሚራመድ ለውጥ የተሻለው አማራጭ መሆኑን ያስገነዝባል። የስኳር ምርት በኤኮኖሚዋ ላይ 17 በመቶ ድርሳ ያለውና 35 ሺህ ሠራተኛ በዚሁ መስክ የሚተዳደርባት የጉዋያና የውጭ ንግድ ሚኒስትር ክሌመንት ሮሄ IPS ለተሰኘው ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ለውጡ በመሰል አገሮች ላይ የሚፈጥረው መሰናክል ከባድ ነው የሚሆነው።
ከታዳጊዎቹ አገሮች አንጻር ለውጡ ሲበዛ የተፋጠነ፣ ጥልቀት ያለውና የተቻኮለ ነው። በዚህ ሁኔታ ብዙዎች ስኳር አምራች ፋብሪካዎች ሕልውናቸውን ለመጠበቅ አይችሉም፤ ሊከተል የሚችለው ማሕበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግርም በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። የጃማይካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኬይት ዲ. ናይት እንደሚሉት የአውሮፓው ሕብረት ዋጋ በያንዳንዱ ቶን ወደ 451 ዶላር ከወረደ ደሴቲቱ በያመቱ ዘጠና ሚሊዮን ዶላር ልታጣ ትችላለች። ብራስልስ በወቅቱ ከአውሮፓውያን አምራቾች አንዱን ቶን ስኳር የምትገዛው በ 767 ዶላር ነው። ይህም ከዓለም ገበያ ዋጋ ሲነጻጸር ሶሥት እጥፍ ይሆናል።

ኮሚሢዮኑ ሽግግሩን ለማቃለል የሚወስዳቸው አጃቢ ዕርምጃዎች ፍቱንነት እንዲኖራቸው ዕርዳታው አሁኑኑ በዚህ ዓመት መቅረቡ ግድ ነው። ዕርምጃው ከዘገየ የታዳጊው ዓለም ኢንዱስትሪዎች ሁኔታቸውን ከዋጋ ቅነሣው ጋር ለማጣጣም አይችሉም ኬይት ናይት እንደሚያስረዱት። የምንፈልገው ከዚህ ቀደም በሙዝ፣ በሩምና ኮኮ ዘርፎች የአውሮፓው ሕብረት የፊናንስ ድጋፍ ፍሬ ቢስ ሆኖ የቀረበት ሁኔታ እንዳይደገም ነው፤ ዕርዳታው ለአምራቹ በቀጥታ መድረስ መቻል ይኖርበታል ይላሉ የጃማይካው ባለሥልጣን።

የአፍሪቃ፣ ካራይብና ፓሲፊክ አገሮች እንዲሁም በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ የሚገኙ መንግሥታትን ያሰባሰበው ቡድን ዓባል ሃገራቱ የአውሮፓውን ኮሚሢዮን ሃሣብ እንዲቃወሙ ይጠይቃሉ። የሚፈልጉት ዋጋ ቅነሣው ከ 2008 አስንቶ በሥምንት ዓመታት ውስጥ ደረጃ በደረጃ እንዲካሄድ፤ መጠኑም መለስተኛ እንዲሆን ነው። ከዚሁ ተጣምሮ ቅነሣው የታዳጊዎቹን አገሮች ስኳር አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ መልክ ለማቀናጀትና ዘመናዊ ለማድረግ ተገቢው ዕርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል።

ለውጡ ቀስ ብሎ መካሄዱ የዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የኦክስፋም ፍላጎትም ነው። ድርጅቱ በአውሮፓው ሕብረት የስኳር ፖሊሲ ላይ ለውጥ ማስፈለጉን አጠያያቂ አያደርግም። ይሁን እንጂ የወቅቱ የለውጥ ሃሣብ በድሆች አገሮች ለሚገኙ ለብዙ አርሶ-አደሮች ጠንቅ ነው ባይ ነው።

ኦክስፋም የአውሮፓው ሕብረት ገበዮቹን ይበልጥ ለታዳጊ አገሮች እንዲከፍት ሲጠይቅ ሕብረቱ በሚቀጥለው ዓመት ለ 18 ስኳር አምራች አገሮች አቀርባለሁ ያለውን ማካካሻ ከ 48.6 ወደ 605 ሚሊዮን ዶላር ከፍ እንዲያደርግ ይጠይቃል። አለበለዚያ ዝቅ ብሎ የተቀመጠው ማካካሻ ብዙዎች ፋብሪካዎች እንዲዘጉ፣ ሥራ-አጥ እንዲበዛ፣ ቤተሰበ እንዲራብና የድሆች አገሮች የወደፊት የዕድገት ተሥፋም ከንቱ እንዲሆን የሚያደርግ ነው። በመሆኑም የለውጡ ዕቅድ ሲበዛ የጠነከረና ጎጂ ነው።

የሕብረቱ ኮሚሢዮን ጽንሰ-ሃሣብ ከመጽናቱ በፊት በእርሻ ሚኒስትሮችና በአውሮፓ ም’/ቤት ተቀባይ ነት ማግኘት ይኖርበታል።

ሕዝባዊት ቻይና በአሁኑ ጊዜ ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ ታላቅ ኤነርጂ ፈጅ አገር ሆናለች። ይህ ደግሞ በአሜሪካ የቤንዚን ዋጋ እንዲንር እያደረገ ሲሆን ቻይና እንዲያውም ወደ አሜሪካ የጥሬ ነዳጅ ዘይት ገበያ ለመግባት እየተጋፋች ነው። የቻይና መንግሥታዊ የነዳጅ ዘይት ተቋም በያመቱ ብዙ ሚሊያርድ ዶላር ትርፍ የሚያስገባውን በአሕጽሮት UNOCAL በመባል የሚታወቅ ታላቅ የአሜሪካ ኩባንያ ለመግዛት ጠይቋል።
ጉዳዩ በአሜሪካ የካፒታል ገበዮች ላይ ብቻ አይደለም ያልተጠበቀ ድብ-ዕዳ የሆነው። የአሜሪካ ፖለቲከኞችም በቻይና ግፊት የአገሪቱ ስልታዊ ጥቅም አደጋ ላይ ወድቋል፤ አንድ ነገር ይደረግ እስከማለት ደርሰዋል። ቻይና UNocal Corporation የተሰኘውን ካሊፎርኒያ ውስጥ ተቀማጭ የሆነ ኩባንያ ለመያዝ እከፍላለሁ ያለችው ገንዘብ 18.5 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ይጠጋል። ይህም ዩኖካልን ለመግዛት ፍላጎት ያሣየው የቴክሣሱ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ቼቭሮን እከፍላለሁ ከሚለው በሁለት ሚሊያርድ ዶላር ከፍ ያለ መሆኑ ነው።

ጉዳዩ በሁለቱ ኩባንያዎች አመራር መካከል የሃይል ትግልን ከማስከተሉ ባሻገር በሃያሏ መንግሥት በአሜሪካና ወደዚያው ልዕልና በምታመራው በቻይና መካከል ያለውን የኤኮኖሚ ተቀናቃኝነት ማየል ጉልህ አድርጎ እያሣየ ነው። ዩኖካል በአሜሪካ ተቀማጭ ቢሆንም 60 በመቶ የነዳጅ ዘይቱን የሚያወጣው በእሢያ ነው። ተቋሙ በዓመት ስምንት ሚሊያርድ ዶላር የሚያስገባው ዋነኛው አትራፊ የአሜሪካ ነዳጅ ዘይት ኩባንያ ሲሆን በእሢያ ሰፊ የተፈጥሮ ጋዝ ሃብትን ይቆጣጠራል። ከዚህ አንጻር የኤነርጂ ጥሟ ታላቅ የሆነው ቻይና ኩባንያውን ለመቆጣጠር መነሣቷ ብዙም አያስደንቅም።

የቻይና ዕርምጃ በዓለም የነዳጅ ዘይት ሃብት ላይ በሚደረገው ፉክክር ለአሜሪካ ብርቱ ፈተና ነው የሆነው። ዩኖካልን መግዛቱ ለቤይጂንግ ከተሣካ የአሜሪካ ብቻኛ ልዕልና አከተመለት የሚሉም አልታጡም። እርግጥ ችግሩ ከአሁኑ ጎልቶ ነው የሚታየው። ባለፈው ሣምንት የአንድ በርሚል ነዳጅ ዘይት ዋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ 60 ዶላር በመድረስ በኒውዮርኩ የምንዛሪ ገበያ ላይ ውዥምብር መፍጠሩ አይዘነጋም።

የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ክምችት በመጠኑ የተወሰነ ነው። አገሪቱ ከውጭ የምታስገባው ነዳጅም ባለፉት ዓመታት ያለማቋረጥ እያደገ ነው የመጣው። በአሜሪካ ብሄራዊ ሸንጎ ውስጥ በቻይና ላይ የንግድ ገደብ እንዲደረግ ጥሪ መሰማት ከጀመረ ቆይቷል። ይህን በተለይ የቀሰቀሰው ቻይና በአሜሪካ ገበያ ላይ በሰፊው የምታራግፈው ርካሽ ምርት ነው።

ወደ ነዳጅ ዘይቱ ጉዳይ መለስ እንበልና የዩኖካል ኩባንያ አመራር ቀደም ሲል ባለፈው ሚያዚያ ወር ከቼቭሮን ጋር ለመዋሃድ መወሰኑ አይዘነጋም። ይሁንና የኩባንያው ባለ አክሢዮኖች ቻይና የበለጠ ገንዘብ እከፍላለሁ በማለቷ ዕቅዱን ሊያከሽፉት በቅተዋል። እርግጥ ግዢው ዕውን እንዲሆን “የአሜሪካ የውጭ ኢንቨስትመንት ኮሚቲ” የተሰኘው መንግሥታዊ አካል ፈቃድ መስጠት ይኖርበታል። በተለይ የአሜሪካ መንግሥት ወይም ብሄራዊው ሸንጎ ሽያጩ የአገሪቱን የደሕንነት ጥቅም ይነካል ካሉ ተቋሙ ጉዳዩን መግታቱ ግድ ነው የሚሆንበት። ግን በሌላ በኩል የነጻ ገበያውን መሠረተ-ዓላማዎች መጻረሩ ቀላል የሚሆን አይመስልም። ሕዝባዊት ቻይናም ጥቅሟን ,ለማስከበር የተቻላትን ግፊት ማድረጓ የማይቀር ጉዳይ ነው።