1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቴይለርና የሄጉ ችሎት

ሰኞ፣ ግንቦት 27 1999

በጦር ወንጀለኝነት የተከሰሱት ቻርልስ ቴይለር ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም ዓቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተከሳሹ የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ቻርልስ ቴይለር ባልተገኙበት ዛሬ ክሳቸውን ሲያዳምጥ ውሏል ። በተባበሩት መንግስታት የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክሳቸው ሲቀርብ የመጀመሪያው የአፍሪቃ መሪ የሆኑት ቻርልስ ቴይለር በችሎቱ ላይ መገኘት ሲገባቸው ነው የቀሩት ።

https://p.dw.com/p/E0ay
ምስል AP

የቴይለር ጠበቃ ለችሎቱ እንዳሳወቁት ወክለዋቸው እንዳይቀርቡ ቴይለር ፈቃድ የከለከሉዋቸው ሲሆን ለራሳቸው ጥብቅና ለመቆምም እያመለከቱ ነው ። አቃቤ ህግ በቴይለር ላይ ያቀረበውን ክስ ዛሬ ያዳመጠው ዓለም ዓቀፉ ችሎትም ከሀያ ቀን በኃላ ደግሞ የምስክሮችን ቃል መስማት ይጀምራል ። ዓለም ዓቀፉ የሴራልዮን ልዩ ፍርድ ቤት ዛሬ ረፋድ ላይ ነበር የቀድሞውን የላይቤሪያ መሪ የቻርልስ ቴይለርን ክስ ማዳመጥ የጀመረው ። ተከሳሹ ቴይለር ግን ፍርድ ቤት አልመጡም ። ለፍርድ ቤቱ እንደተገለፀው የተሰጡቸው የመከላከያ አማራጮች በቂ ባለመሆናቸውና ነፃ ፍርድ አገኛለሁ ብለው ስለማይጠብቁ ነው ። ጥብቅና እንዲቆሙላቸው የተመደቡላቸው ጠበቃቸው ካሪም ክሀን ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት ቴይለር እንዳይወክሉዋቸው ከልክለዋቸዋል ። ለራሳቸው ጥብቅና ለመቆምም አመልክተዋል ። ጠበቃው ይህን ካሳወቁ በኃላም ዶሴያቸውን ሰብስበው ይቅርታ ጠይቀው ከፍርድ ቤቱ ሊወጡ ሲዘጋጁ እንዲቀመጡ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም ትዕዛዙን ጥሰው ችሎቱን ረግጠው ወጡ ። ከዚያም ችሎቱ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ተሰጥቶ አቃቤ ህግ ክሱን ማሰማት ቀጠለ ። ቴይለር የተከሰሱት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ እስከ ሁለት ሺህ አንድ በሴራልዮኑ የርስ በርስ ጦርነት ፈፅመዋል በተባሉት ወንጀሎች ነው ። በወቅቱ በርካታ ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል የሚወነጀለውንና በእንግሊዘኛው ምህፃር አር ዩ ኤፍ በመባል የሚታወቀውን የሴራልዮኑን የተባበሩት አብዮታዊ ግንባር በማስታጠቅ በማሰልጠንና በመቆጣጠር በምትኩም መጠኑ ያልታደረሰበት አልማዝ ከሀገሪቱ በማጋበስ ነው የተወነጀሉት ። ከዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቃሪ ድርጅት ህዩማን ራይትስ ዎች ሚስ ኤሊስ ኬፕለር ለዶይቼቬለ ራድዮ እንደተናገሩት ቴይለር ከተከሰሱባቸው ወንጀሎች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው ።
“እነዚህ ወንጀሎች ግድያ ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ጠለፋ ፣ የህፃናት ወታደሮች ምልመላ የሰዎችን እግሮችና ሌሎች አካላትንም መቆራረጥ እንዲሁም በሴራልዮኑ ግጭት በደረሱ ሰቅጣጭ ወንጀሎች በሙሉ ነው ። “
ቴይለር የተመሰረቱባቸው አስራ አንድ ክሶች ናቸው ። እነርሱም በጥቅሉ በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀሙና እና በሌሎችም ዓለም ዓቀፍ ሰብዓዊ ህግጋትን የመጣስ ከባድ ወንጀሎች ናቸው ።
እነዚህን በመሳሰሉት ወንጀሎች ፍርድ የሚጠብቃቸው ቴይለር ወንጀለኛ ናቸው ተብሎ ከተከሰሱ ወደ አራት ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ በኃላ ለፍርድ መቅረባቸው ለሴራልዮን እፎይታ ቢያስገኝም መዘግየቱ ግን ቅር ማሰኘቱ አልቀረም ። ጊዜ ወስዶም ቢሆን የቴይለር ዓለም ዓቀፍ ፍርድቤት መቅረብ ለሌች በተመሳሳይ ወንጀሎች ለሚከሰሱ የአፍሪቃ መሪዎች መቀጣጫና ትምህርት ሰጭ መሆኑን ነው ሚስ ኤሊስ ኬፕለር የሚናገሩት
“በኛ አመለካከት ቴይለር ለፍርድ የቀረቡበት ይህ ጊዜ ትልቅ ግምት የምንሰጠው ወቅት ነው እናም በምዕራብ አፍሪቃ በሰብዓዊነት ከተፈፀሙ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ እና በጦር ወንጀለኝነት የተከሰሱት ቴይለር ለፍርድ መቅረባቸው ማንም ከህግ በላይ እንዳልሆነ ጠንካራ መልዕክት ያስተላልፋፋል ለማናቸውም ከባድ ወንጀሎች ያለመከሰስ መብት አይኖርም ። ከዚህ ቀደም በተለይ በምዕራብ አፍሪቃ እጅግ ከባድ ወንጀሎች የፈፀሙ ግለሰቦች የነበራቸው ያለመከሰስ መብት ጊዜው እያለፈበት ነው ። እናም እጅግ ከባድ የሆኑት ወንጀሎች ፍትህ ማግኘታቸው በተለይ ለተወሰኑ ጊዜያት የህግና ስርዓት ክፍተት እንደታየባት እንደ ሴራልዮን በመሳሰሉ አገራት ህግና ስርዓት እንዲከበር ያግዛል የሚል ዕምነት አለን ። ይህ ደግሞ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን አስተዋፅኦ ያደርጋል ። “
በዓለም ዓቀፉ የሴራልዮን ልዩ ፍርድ ቤት ዛሬ ክሳቸው መሰማት የጀመረው ቴይለር ከቀድሞው የዩጎዝላቪያ ፕሬዝዳንት ስሎቦዳን ሚሎሶቪች ቀጥሎ ዓለም ዓቀፍ ጦር ፍርድ በመቅረብ ሁለተኛው መሪ ናቸው ። ከአፍሪቃ ደግሞ ብቸኛው ። ልዩ ፍርድቤቱን ከሴራልዮኑ የርስ በርስ ጦርነት በኃላ ሴራልዮንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ናቸው ያቋቋሙት ። አቃቤ ህግ በቴይለር ላይ የመሰረተውን ክስ ዛሬ መስማት የጀመረው ልዩ ችሎት ከሶስት ሳምንት በኃላ የምስክሮችን ቃል ማዳመጥ ይቀጥላል ። ለአስራ አንድ ዓመታት በዘለቀው የሴራልዮኑ የርስ በርስ ጦርነት ቁጥሩ ወደ ሁለት መቶ ሺህ ሰዎች የሚደርስ ህዝብ ተገድሏል ። ከነዚህ በሺህ የሚቆጠሩት አካላቸው ተቆራርጦ ነው የተገደሉት ።