1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቴዲ አፍሮ እና የቄራው መዘጋት 

ዓርብ፣ ሚያዝያ 13 2009

በዩትዩብ በተለቀቀ በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ነበር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተመልካቾችን ያገኘው። አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን «ኢትዮጵያ» በሚል ስያሜ ለአድማጮች ይፋ ያደረገው ነጠላ ዜማ ደጋፊዎችን ሲያስደስት ተቺዎችንም አነሳስቷል። ለሳምንታት ሲያወዛግብ የቆየው የአህያ ቄራ ኢትዮጵያ ውስጥ የመዘጋቱ ዜና በርካቶችን አስደስቷል።

https://p.dw.com/p/2beIM
Symbolbild Mikrofon
ምስል Fotolia/Serg Nvns

በዩትዩብ በተለቀቀ በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ነበር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተመልካቾችን ያገኘው። አርቲስት ቴውድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በግል የዩቲዩብ ገፁ ለአድማጮቹ ይፋ ያደረገው ነጠላ ዜማ። አርቲስቱ «ኢትዮጵያ» የሚል ስያሜ  የሰጠው  ይኽ ነጠላ ዜማ ደጋፊዎችን እና ነቃፊዎችን የተለያየ ጽንፍ አስይዞ አነታርኳል።  በዚሁ ሣምንት የበርካቶች መነጋገሪያ ከኾኑ ርእሰ ጉዳዮች መካከል አወዛጋቢው የአህያ ቄራ የመዘጋት ዜና ይገኝበታል። በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የቄራው መዘጋት ዜና እጅግ ያስደሰታቸው ሰዎች የሰጧቸው አስተያየቶች ጎልተው ወጥተዋል። 

አነጋጋሪ ሥራዎች

ብዙውን ጊዜ ይዞ የሚቀርባቸው ሥራዎቹ በደጋፊዎቹም ሆነ በነቃፊዎቹ ዘንድ እጅግ አነጋጋሪ ናቸው። ድምጻዊ፣ ገጣሚ እና የዜማ ደራሲ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን በተለምዶ ቴዲ አፍሮ በበአል ሰሞን ይፋ ያደረገው ዜማው በአድናቂዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ሙገሳ እንዲቸረው አድርጎታል። ትችትም አስነስቶበታል። አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን «ኢትዮጵያ» የሚል ስያሜ የሰጠውን ነጠላ ዜማ ይፋ ባደረገበት ወቅት የደጋፊዎቹ ሙገሳ ግን ጎልቶ ተሰምቷል። 

ደጋፊዎቹ፦ ቴዲ ባያዜም እንኳን የኢትዮጵያን ስም ብቻ ቢጠራ ደጋግመን እንሰማዋለን፤ ሁልጊዜም የሚቀርበው ለየት ያለ አነጋጋሪ ነገር ይዞ ነው፤ ቴዲ አፍሮ ራሱን የስኬት ማማ ላይ የሰቀለው ዛሬ ሳይሆን ገና «አቡጊዳ» በሚል ሲያዜም ጀምሮ ነው የሚሉ እና ሌሎች አድናቆቶችን አጉርፈውለታል። 

የቴዲ ነቃፊዎች በበኩላቸው፦ ደጋፊዎቹ ቴዲን ከማድነቅም አልፈው ሊያመልኩት ተቃርበዋል፤ «ኢትዮጵያ» የሚል ስያሜ በሰጠው ነጠላ ዜማ ያቀረበው ከእሱ ደረጃ የማይጠበቅ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። 

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

ሙያዊ ጥልቅ ሂሥ እጦት

የቴዲ ሥራ ላይ ሙያዊ ጥልቅ ሂሥ ከመስጠት ይልቅ ግን በማኅበራዊ መገናኛዎችም ኾኑ እንደ ሬዲዮ ባሉ የመገናኛ ዘዴዎች ጭምር ይሰጡ የነበሩ አስተያየቶች መስመር ሲስቱ፤ ደጋፊ እና ተቃዋሚዎችን በደምሳሳው ሲወርፉ ተስተውለዋል። ይኽን የታዘቡ አስተያየት ሰጪዎች፦ «ኢትዮጵያ ውስጥ ተሳዳቢነት የማንነታችን አንድ መለያ መስሏል» ሲሉ ጽፈዋል። ከሙገሳ እና ትችቱ የመወራረፉ ማስተጋባትን በመታዘብም «ወይ ቴዲ አፍሮ ለስንቱ የሥራ እድል ፈጠርክ»  ያለም ነበር። በማንኛውም የጥበብ ውጤቶች በብቃት ላይ የተመሠረተ እና  በቀና መንፈስ የተቃኘ ሙያዊ ሂሥ ለጥበቡ እድገት ወሳኝ መኾኑ ግን እሙን ነው።

ሌላው ካለፉት ሦስት ሳምንታት አንስቶ የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኖ የሰነበተው የአህያ ሥጋ ለውጭ ሃገራት ሊያቀርብ ቢሾፍቱ ወይንም ደብረዘይት ውስጥ ተከፍቶ የነበረው የአህያ ቄራ ጉዳይ ነበር። ይህ በቀን ሁለት መቶ አህዮችን ለማረድ ተከፍቶ የነበረው የአህያ ቄራ መዘጋት ከእምነት ባሕላችን ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ተግባር ነበር ሲሉ የተቃውሞ ድምፃቸውን ላሰሙ ሁሉ እፎይታን የፈጠረ ዜና ነበር። በእርግጥ የአህያ ቄራ ከፍቶ መዝጋቱ መንግሥት የህዝቡን ተቃውሞ አደምጣለሁ የሚል ስሜት ለመፍጠር ተጠቅሞበታል የሚሉ እንዳሉ ማለት ነው።  

አወዛጋቢው የአህያ ቄራ መዘጋት

ዮናታን በትዊተር ገጹ፦ «የአህያ መብት ተከራካሪዎች ፀሎታቸው የተሰማ ይመስላል» ብሏል በአጭሩ።  ዘመድኩን በቀለ በበኩሉ «ሰበር ዜና.! በኢትዮጵያችን አህያ ነፃ ወጣች!» በሚል ርእስ ዘለግ ያለ የፌስቡክ ጽሑፉን በትዊተር ገጹ አቅርቧል። ዘመድኩን በጽሑፉ የአህያ ቄራው የተዘጋበት ያለውን ምክንያቶች አስፍሯል። ቄራው የተዘጋው  አንድም ሥጋው እና ቆዳው ሊላክላቸው የነበሩ ሃገራት ፍላጎታቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ላለመክስር ተብሎ መኾኑን የሚናገሩ እንዳሉ ጽፏል። በሌላ መልኩ ደግሞ የደብረዘይት ነዋሪዎች ለፋሲካ በዓል ከልኳንዳ ቤቶች ሥጋ ባለመግዛታቸው ልኳንዳ ቤቶች ላይ የደረሰው ኪሳራ በመላው ሃገሪቱ ከተዛመተ አደጋው የከፋ መኾኑን በማየት ነው የሚሉም መኖራቸውን አስነብቧል። 

Esel
ምስል Colourbox

በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ደግሞ ጥላሁን አንተነህ፦ «እንኳን ደስ አለችሁ ስለመዘገቱ» ሲል ደስታውን ገልጧል።  ሚኪያስ ማሞ፥ «የልማት ሀሳብ ደጋፊ ነኝ መቀጠል አለበት» ሲል መዘጋቱን ተቃውሟል፡፡ «በኢትዮጵያ ገበያ እስካልተሸጠ ምን ችግር አለ? ይሥራ» ሲል ከሚኪያስ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ ያቀረበው ደመቀ ዲቻ ነው።  አበጀ ዩሱፍ፦ «የቻይናን ብድር መልሰን እስከ አልከፈልን ድረስ በጥቅማቸው ላይ የመወሰን አቅማችን ዉሱን ነው» ብሏል። 

በመዘጋቱ በርካቶች ደስተኞች ናቸው

በርካታ አድማጮቻችን በዋትስአፕ ገጻችን አስተያየቶቻችሁ ደርሶናል። የአህያ ቄራው በመዘጋቱ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጡ አስተያየቶች ይበዛሉ። «ሃይ ዶቸ ቬሌዎች በቢሾፍቱ የአህያ ቄራ ተከፍቶ የነበረው መዘጋቱን ሰማሁ በጣም ደስ ብሎኛል እዲቆም የሆነው በናንተ ጥረት ነው እና ወደፊትም ቀጥሉበት» ያሉን  ላቃቸው የተባሉ አድማጫችን ከሰሜን ሱዳን ናቸው። 

«መዘጋቱ በጣም ደስ ይላል መከፈቱ እብደት ነበር» ይኽ ደግሞ ከኢትዮጵያ የደረሰን አስተያየት ነው። «ዋው በጣም ደስ የሚል ዜና ነገር ግን ሲጀመር እንዴትስ ሊፈቀድ ቻለ?» ከኢትዮጵያ አድማጫችን የተሰነዘረ ጥያቄ ነው። «በጣም ያሳዝናል እንኳንም ታገደ» ሌላው ከኢትዮጵያ የደረሰን አጠር ያለ አስተያየት።

«ቄራው መዘጋቱ እውነተኛ ከኾነ ትክክለኛ ውሣኔ ነው፤ ምክነያቱም ዛሬ የአሕያ ሥጋ መላክ የጀመረው ቄራ ነገ ከነገ ወዲያ የውሻ ሥጋን ልላክ ማለቱ የማይቀር ጉዳይ ሥለኾነ» ከኢትዮጵያ የተላከ የዋትስአፕ መልእክት ነው።

«ከባሕል እና ከሃይማኖት የተጣረሰ»

«ሀይ ዶይቸ ቬለዎች እንደምን አላችሁ በጣም የሚገርም ነገር። መጀመረያ ፈቃዱን ማን ሰጣቸው ማንሥ ነው ያሥቆማቸው? በበሐልና ቱሪዝም የሀገረችን እምነትና ባህል በአሉበት እንዲቀጥሉ ሲባሉ እንሰማለን በመገናኛ ብዙኃን። አሁን ደግሞ የአህያ ቄራ በኢትዮጵያ ሃይማኖትም ባህልም በጣም የሚወገዝ መሆን አለበት። ከአሁን በኋላ የመቆሙ ጉደይሥ በምንድን ነው የሚረጋገጠው?» የሚል ጥያቄ ከኢትዮጵያ አድማጫችን ደርሶናል። 

Golabal Ideas Walnussernte in Kirgistan
ምስል DW/K. Palzer

ከጅቡቲ የደረሰን አጠር ያለ መልእክት፦ «ይህን ሃይማኖትም አይደግፈውም፤ በጣም አስጠያፊ ተግባር ያሳዝናል» ይላል። «መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል ይላል ያገሬ ሰዉ ለዉጭ የተጀመረ ያህያ ሥጋ ኅብረተሠቡ ላለመመገቡ ምንም ዓይነት ዋስትና አልነበረዉም። እንኳን ተዘጋ ባይ ነኝ» ከኳታር የደረሰ መልእክት ነው።  «ለነገሩ እንደማይቀጥል ያወቅነዉ የቻይና መንገድ ሠራተኞች በላይ አርማጭሆ ትክል ድንጋይ አህያ ከ2 አመት በፊት ጀምረው ህዝቡ ከልክሏቸዋል ብሩክ ከጎንደር» ቻይናዎች መንገድ እንሥራ እያሉ ሲላመዱን ከአህያ ሥጋም አልፈው ሌላ ጣጣ ሊያመጡ ይችላሉ ሲሉም አስተያየት የሰጡ ነበሩ።

«እንደሚዘጋ ቀድሞም ታቅዶ ነው የተከፈተው»

«የሕዝብን ጩኸት ሰምተው ከሆነ ጥሩ ነው። ግን እነዚህን ሰዎችን አላምናቸውም በድብቅ ሊካፍቱት ይችላሉ እኔ ግን የሚመስለኝ ገበያ ጠፍቶ ነው ባይ ነኝ። የሚገዙ ሀገሮች ፍላጓት አለመኖር ይመስለኛል።» ከደቡብ አፍሪቃ.

«ሀይ ዶይቸ ቬለዎች ሠላም ናችሁ ሥለ አህያው ቄራ መዘጋት ጥርጣሬ አለኝ ይኸውም የኢህአደግ መንግሥት በዕውነት የህዝብን ተቃውሞ ተመርኩዞ በአህያ ቄራው ላይ መዘጋት እንዳለበት ውሣኔ አሥተላልፏል ነው የተባለው። እኔ አላምንም፤ ከሆነ እሠየው። ምክንያቱም የልኳንዳ ቤት ሥጋን ባየሁ ቁጥር የሚያጭርብኝ ነገር ነበር ለማንኛውም እውነት ይሁን  ብላክ አሚን ከደሴ»

የአህያ ቄራ በኢትዮጵያ ሲከፈት ለመዘጋቱ ቀድሞ ታቅዶ ነበር ሲሉም አስተያየታቸውን  ያሰፈሩ ነበሩ። መንግሥት የኅብረተሰቡን እምነት እና እሴት በተመለከተ ምላሹ ፈጣን ነው የሚል ስሜት በኅብረተሰቡ ዘንድ ለመፍጠር ታልሞ ቀድሞ የተቀናጀ ነው በማለት ነገሩን በጥርጣሬ የተመለከቱም አልታጡም። በዚህም አለ በዚያ ግን የአህያው ቄራ ለመዘጋት ውሳኔው መተላለፉ በርካቶችን ያስደሰተ ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ