1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትራንስ-አትላንቲክ የፊናንስ ገበዮች ውሕደት

ረቡዕ፣ የካቲት 9 2003

የኒውዮርክና የፍራንክፉርት የፊናንስ ገበዮች ትናንት ታሪካዊ ግምት የሚሰጠው ውሕደት ለማስፈን ተስማምተዋል።

https://p.dw.com/p/R1W2
ምስል DW

ሁለቱ የፊናንስ ገበዮች በውሕደቱ በዓለም ላይ ታላቁን የአክሢዮንና የትርፍ ንግድ ገበያ የሚፈጥሩ ሲሆን የጋራ ካፒታላቸው 26 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የሚደርስ ነው። ሁለቱ ወገኖች በፍራንክፉርት፣ ኒውዮርክ፣ ፓሪስ፣ አምስተርዳም፣ ብራስልስና ለንደን የንግድ ቦታዎች ሲኖሯቸው ትናንት በተደረገው የውሕደት ስምምነት መሠረት የጀርመኑ የፊናንስ ገበያ 60 በመቶና የኒውዮርኩ ደግሞ 40 በመቶ ድርሻ ይይዛል። ለፋራንክፉርቱ የምንዛሪ ገበያ በዝናኛው የኒውዮርክ ዎል-ስትሪት የፊናንስ ንግድ አብሮ ለመወሰን መብቃት ታሪካዊ ግምት የሚሰጠው ነው።

Frankfurter Börse
ምስል picture-alliance/dpa

ታላቁ የፊናንስ ውሕደት

የጀርመኑ የፍራንክፉርት የፊናንስ ገበያና የአሜሪካ መሰሉ የኒውዮርክ ስቶክ ኤክስቼንጅ በዓለም ላይ ታላቁን የፊናንስ ገበያ ውሕደት ለማስፈን ተስማምተዋል። የጋራው የፊናንስ ገበያ ምን ያህል ግዙፍና ሰፊ አካባቢን ያዳረሰ እንደሆነ ትናንት የፍራንክፈርቱ ወገን የበላይ አካል ባልደረባ ማንፍሬድ ጌንትስ ኒውዮርክ ውስጥ በተካሄደ ጋዜጣዊ ጉባዔ ላይ በተናገሩበት ጊዜ ይበልጥ ግልጽ ነበር የሆነው።

“ክቡራትና ክቡራን በኒውዮርክ እንደምን አደራችሁ! መልካም ቀን፤ መልካም ምሽት! በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በእሢያ ለምትገኙ ተቀጣሪዎቻችን!”

እንግዲህ ትራንስ-አትላንቲኩ ትስስር በጊዜም ይሁን በርቀት ስሌት የተለያዩ የዓለም አካባቢዎችን በሰፊው የሚጠቀልል መሆኑ የተሰወረ አይደለም። እናም የፍራንክፈርቱ የፊናንስ ገበያ ሃላፊ ሬቶ ፍራንቺዮኒና የአሜሪካው አቻቸው ዳንካን ኒደርአወር ከብዙ ድካም በኋላ በስምምነቱ ገሃድ መሆን ታላቅ ዕፎይታ ነበር የተሰማቸው።

የሁለቱ ተቋማት አመራር አካላት እርግጥ ስምምነቱን ገቢር ለማድረግ ገና ከባድ ጉዞ ነው የሚጠብቃቸው። አዲሱ የጋራ የፊናንስ ገበያ ወይም ውሕደቱ እስከያዝነው 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ መስፈን ይኖርበታል። ከዚሁ በፊት ደግሞ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች ስምምነቱን ተቀብለው ማጽደቃቸውም ግድ ነው። በዚህ በጀርመን ፍራንክፉርት የምትገኝበት ፌደራል ክፍለ-ሐገር የሔሰን የምጣኔ-ሐብት ሚኒስቴር ለምሳሌ ውሕደቱን በጥልቅ ለመመርመርና የፍራንክፉርቱ ገበያ ጸንቶ መቆየቱንም ለማረጋገጥ ይፈልጋል። ጉዳዩን የሚከታተለው የአውሮፓ ሕብረት የፉክክር ተቆጣጣሪ አካልም እንዲሁ ስምምነቱን መቀበል አለበት። ነገር ግን በዚህም በዚያም ስኬት የሚጠበቅ ሲሆን አዲሱ የፊናንስ ገበያው ውሕደት በዓለም ላይ የበላይነቱን እንደሚይዝ ለሬቶ ፍራንቺዮኒም የተሰወረ ነገር አይደለም።

“በአንድላይ በአውሮፓና በአሜሪካ ለንግዳችን በምንገለገልባቸው ቦታዎች በሁሉም ዘርፍ የገበያው ቀደምት መሪ ነው የምንሆነው”

ይህ ደግሞ ጠቅላላውን የፊናንስ ንግድ ዘርፍ መቀየሩ አይቀርም። ሁለቱን በዓለም ላይ ታላቅና ስኬታማ የሆኑ የፊናንስ ገበዮች ለማስተሳሰር መቻሉ ታሪካዊ ነው። የጀርመኑና የአሜሪካው የፊናንስ ገበዮች ከፍራንክፉርትና ከኒውዮርክ ሌላ በፓሪስ፣ በብራስልስ በአምስተርዳምና በለንደን የንግድ ቦታዎች ሲኖሯቸው የአዲሱ ውሕደት ዋና መቀመጫ የምትሆነውም አምስተርዳም ናት። አዲሱ የገበያ ሕብረት በኔዘርላንድ ሕግ ሥር የሚተዳድ ሲሆን በእስካሁኑ የጀርመን የፊናንስ ገበያ ሃላፊ በሬቶ ፍራንቺዮኒ የሚመራም ነው የሚሆነው። ውሕደቱን በበላይነት የሚመሩት ደግሞ የኒውዮር’ኩ ዳንካን ኒደርአወር ይሆናሉ። ትስስሩ ወደፊት በያመቱ 300 ሚሊዮን ኤውሮ ለመቆጠብ እንደሚያችል ነው የሚነገረው።

እንደሚታወቀው የኒውዮርኩ የፊናንስ ገበያ ዎል-ስትሪት የአሜሪካ የከበርቴ ስርዓት ዕድገት መለያ ሆኖ ነው የኖረው። ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ የአክሢዮኖች ንግድ ሲካሄድበት ቆይቷል። ታዲያ ከዚህ አንጻር የፍራንክፉርት የፊናንስ ገበያ አብዛኛውን የአክሢዮን ድርሻ መያዙ ታሪካዊ ክብደት ይኖረዋል። በሌላ በኩል ውሕደቱ የጊዜው የሕልውና ትግልም ያስከተለው ነው። ዛሬ የፊናንሱ ገበዮች ፉክክር እየጠነከረና እየሰፋ በሄደበት ጊዜ ስምና ዝና ያላቸው የፊናንስ ገበዮችም ቢሆን የጊዜውን ችግር ለመቋቋም ከትስስር ሌላ ምርጫ እንደሌላቸው ሳይረዱት የቀሩ አይመስልም።

NO FLASH Euro europa Münze Rettungsschirm Rettungsfonds
ምስል picture alliance/dpa

የኤውሮ ቀውስ መፍትሄና የዕዳ ቅነሣ

ዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ጥሎት ካለፈው ችግር ለማገገም ጥረት የሚደረገው በአክሢዮኑ ገበዮች ብቻ አይደለም። የአውሮፓ ሕብረትም የበኩሉን ችግር ለመቋቋም እየታገለ ነው። የሕብረቱ የፊናንስ ሚኒስትሮች ትናንት ባርስልስ ላይ ባካሄዱት ስብሰባ የኤውሮን ምንዛሪ ቀውስ ለዘለቄታው ለመፍታት ለፉክክር ብቃት ቋሚ ገንዘብ ማቅረቡንና ዕዳን መቀነሱን ቁልፍ ጉዳይ አድርገው አግኝተውታል። ኪሣራ የደረሰባቸውን ዓባል ሃገራት ለማዳን የሚቀርበውን ቋሚ የገንዘብ ዕርዳታ በፊታችን 2013 የእስካሁኑን በጀት የሚተካ ሲሆን በግልጽ ከፍ እንዲል ተወስኗል።
ይሄው ወደፊት የአውሮፓ የማረጋጊያ መዋቅር በአሕጽሮት ESM የሚሰኝ ሲሆን 500 ሚሊያርድ ኤውሮ በጀት የሚኖረው ነው። የሕብረቱ የምንዛሪ ኮሜሣር ኦሊ ሬህን እንዳሉት በጀቱ ዕርዳታ ለሚሻው ዓባል ሃገር በሚፈለግበት ጊዜ በሙሉ ይዘቱ የሚቀርብ ነው የሚሆነው። ኮሜሣሩ አክለው እንዳስረዱትም፤

“ከዚሁ በተጨማሪ የአውሮፓ ሕብረት ዓባል ካልሆኑ አገሮችና ከዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋምም ሌላ ብድር ሊወሰድ ይችላል። ለዚሁ ደግሞ የአውሮፓው ማረጋጊያ መዋቅር በገበዮች ላይ አመኔታን እንደሚያሰፍን እርግጠኛ ነኝ”

እርግጥ የ 500 ሚሊያርዱ ኤውሮ ስምምነት ለጊዜው የዓላማ ስምምነት እንጂ ጭብጥ ውሣኔ አይደለም። በጉዳዩ የሚወሰነው በፊታችን መጋቢት ወር በሚካሄደው የሕብረቱ ዓባል መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ ላይ ነው። በሌላ በኩል የገንዘብ አቅርቦቱ ድርሻ በመንግሥታቱ መካከል ማከራከሩም አልቀረም። ስለዚህም የሉክሰምቡርጉ የገንዘብ ሚኒስትር ሉክ ፍሪድን እንደሚሉት ለምሳሌ ዋስትና ሰጪዎቹ በብድር ታማኝነት ከፍተኛ ነጥብ የሚሰጣቸው ጠንካሮቹ አገሮች ብቻ መሆን የለባቸውም።

“እዚህ ላይ ሁሉም የኤውሮ-ዞን ዓባል ሃገራት ግዴታ አለባቸው ብዬ ነው የማስበው። እርግጥ ትሪፐል-ኤ በመባል የሚጠሩት ሃገራት የበለጠ! ይሁንና እዚህ የሚጠየቀው የሁሉም ዓባል ሃገራት ድጋፍ ነው”

በኤኮኖሚያቸው ጽኑ የሆኑት ትሪፐለ-ኤ አገሮች ጀርመንን ጨምሮ ስድሥት ሲሆኑ እነዚሁ ለሌሎች አገሮች ጥፋት መስዋዕት በመሆናቸው አጥብቀው ማማረራቸው አልቀረም። የሆነው ሆኖ በጋራ ዘላቂ እርጋታን ከማስፈኑ ሌላ ጎልቶ የሚታይ ምርጫ አለመኖሩም ግልጽ ነው።

Flut China Yangtze Fluss China 2010 Flash-Galerie
ምስል AP

ጃፓን በኤኮኖሚ ልዕልና በቻይና ተበለጠች

ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በማገገም ላይ ከሚገኙት የበለጸጉ ሃገራት አንዷ ጃፓን ስትሆን እሢያይቱ አገር በዓለም ኤኮኖሚ ሃያልነት ከአርባ ዓመታት በላይ ይዛ ያቆየችውን ሁለተኛ ቦታ ለቻይና ማስረከቡ ዘንድሮ ግድ ሆኖባታል። የቶኪዮ መንግሥት ሰሞኑን እንዳስታወቀው የጃፓን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ባለፈው 2010 ዓ.ም. ያደገው በ 5,5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነበር። በዚህም ከቻይናው 5,9 ቢሊዮን ዶላር ዕድገት ሲነጻጸር ዝቅተኛ ሆኖ ነው የተገኘው። ሕዝባዊት ቻይና በአጭሩ በተፋጠነ ዕድገት መገስገሷን ቀጥላለች።

የጃፓን ኤኮኖሚ በተለይም በዓመቱ የመጨረሻ ሩብ በአውቶሞቢል ግዢ ማቆልቆልና በትንባሆ ግብር መጨመር የተነሣ በሰፊው ሲቀንስ በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ የሆነችው የሩቅ ምሥራቅ አገር ምንዛሪ ጥንካሬም ምርቶቿን በውጭ ለበዮች ላይ ውድ ነው ያደረገው። ለነገሩ የጃፓን ኤኮኖሚ የ 3,9 በመቶ ዕድገት ባለፈው 2010 ቀደም ካሉት ሶሥት ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ነበር። ግን የቻይና ጉዞ ሊቋቋሙት የሚቻል አልሆነም።

መለስ ብሎ ለማስታወስ ጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ተዓምራዊ ዕድገት በማድረግ ከአሜሪካ ቀጥላ በዓለም ላይ ሁለተኛዋ የኤኮኖሚ ሃይል ለመሆን ስትበቃ ለ 42 ዓመታትም በዚሁ ደረጃ ላይ ቆይታለች። ሆኖም የጃፓን የኤኮኖሚ ዕድገት በተለይም ከ 90ዎቹ ዓመታት ወዲህ መሰናከሉ ሲታወስ የማቆልቆል ሂደቱ አሁን የዓለም ኤኮኖሚ ከቀውስ ማገገም በያዘበት ሰዓትም ቢሆን መቀጠሉ እንደማይቀር ነው የምጣኔ-ሐብት ባለሙያዎች የሚገምቱት። የሕብረተሰቡ የማርጀት ሂደት በማሕበራዊው ስርዓት ላይ ያስከተለው ከፍተኛ ሸክምም በዚህ በአውሮፓ እንደሚታየው ለኤኮኖሚው ተጨማሪ ጠንቅ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።

የሕዝባዊት ቻይና ኤኮኖሚ በአንጻሩ በያመቱ አሥር በመቶ ዕድገት የሚታይበት ነው። ከዚህ አንጻር የዓለም ባንክና ሌሎች የፊናንስ ተቋማት የሚገምቱት ቻይና እስከ 2025 ዓ.ም. ድረስ አሜሪካን በዓለም የኤኮኖሚ ልዕልና ከመጀመሪያው ስፍራ እንደምትፈነቅል ነው። ቻይና በዚሁ ረገድ ጀርመንን ቀደም ሲል በ 2007 ዓ.ም. ስትደርብ የኋላ ኋላም በውጭ ንግድ ጭምር መብለጧ ይታወሣል። በነገራችን ላይ በተፋጠነ ዕድገት ላይ ከሚገኙት አገሮች መካከል ብራዚልም በኤኮኖሚ ጥንካሬዋ በዓለም ላይ ወደ ስምንተኛው ቦታ ስትደርስ ሕንድም ወደዚያው እየተጠጋች ነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ