1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ የካቲት 10 2004

ትኩረት በአፍሪቃ ሁለት ዓበይት ርዕሰ-ጉዳዮችን አካቷል። የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ትብብር በእንግሊዘኛ ምህፃሩ ECOWAS ጉባኤን የሚመለከተው ቀዳሚው ርዕሳችን ነው። በሳህል አካባቢ ያንዣበበው የረሀብ አደጋ ይከተለዋል።

https://p.dw.com/p/145QT
የሳህል በረሃ
የሳህል በረሃምስል picture-alliance/ dpa
በአፍሪቃ የሳህል አካባቢ
በአፍሪቃ የሳህል አካባቢ
አስቸኳይ ርዳታ ያስፈልጋል
አስቸኳይ ርዳታ ያስፈልጋልምስል AP

ሐሙስ የካቲት 11 ቀን  2004 ዓ. ም. አቡጃ ናይጄሪያ ውስጥ የተከፈተው የ ECOWAS  ጉባኤ በሁለት አበይት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ መክሯል። በቃጣናው በተለይ በጊኒ ባህረ ሰላጤ እየተስፋፋ የመጣው   የባህር ላይ ውንብድና እና የሳህል አካባቢ ድርቅ የECOWAS  ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕሰ-ጉዳዮች ነበሩ። ለሁለት ቀናት በዘለቀው በዚህ ጉባኤ  የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፤ የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት ትብብር የበለጠ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

«ምዕራብ አፍሪቃ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙ አባላት አሉት። ይህ በእጃችን ያለ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችል ጠቃሚ ሀይል ነው። ስለዚህ የቃጣናችንን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ በተግባር ልናውለው እና ልንጠቀምበት ያስፈልጋል። »

ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፤ የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ትብብር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሌሎች አካባቢያዊ ሀገሮች አብነት የመሆኑን ያህል፤ ይህ ብቃቱ አደጋ ውስጥ መውደቁንም ጠቁመዋል። በተለይ አዲስ አበባ ላይ በተከናወነው የኅብረቱን ኮሚሽን እና መሪ የመምረጡ ሄደት  ላይ የ ECOWAS  አባል ሀገራት ኅብረት እና ጥንካሬ ደካማ ነበር ሲሉ ተችተዋል። አያይዘውም ወደፊት ድምፃችን በአንድነት ሊሰማ ይገባል ብለዋል።

በጉባኤው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት የምዕራብ አፍሪቃ ልዑክ ሳኤድ ጂኒት በበኩላቸው፤ ለኮትዲቯር ውዝግብ መፍትሄ ለመሻት የወሰዳችሁት ርምጃ እንዲሁም የላይቤሪያ የምርጫ ሂደትን ለመደገፍ  ያሳያችሁት ተሳትፎ ይደነቃል ብለዋል። ሳኤድ ይህ ትብብር መቀጠል እንዳለበት ሁሉ፤ አካባቢው ላይ ለተደቀኑ ችግሮችም ፈጣኝ መፍትሄ እንደሚያሻ አስገንዝበዋል።

«እነዚህን ስኬቶች ከምንጊዜውም በላይ ማጠናከር ያስፈልጋል። ስኬቱ እዚህ ድረስ የመጓዙን ያህል፤ በቃጣናው ሰሜናዊ ድንበሮች እና የባሕር  ጠረፎች በተለይ በጊኒ ባህረ ሰላጤ በተከሰተው የባሕር ላይ ውንብድና  እንዲሁም በሳህል አካባቢ ባለው ያለመረጋጋት ሊጎዳ ይችላል።»

የወቅቱ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዣን ፒንግ፤ የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት ሕዝቦች በጋራ ባህል እና ታሪካችሁ ስር ጠንካራ ማንነታችሁን በሚያሳይ መልኩ  ትብብራችሁን ማዳበር አለባችሁ ብለዋል። ይህ ደግሞ ህብረት እና ትብብራችሁ እየተጠናከረ እንዲሄድ ያደርገዋል ሲሉም አክለዋል። ዣን ፒንግ አያይዘው ሲገልፁ፥

«በአካባቢው የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የተጠቀማችሁበት መንገድ ወደ አህጉሩ ድርጅትም ሊሸጋገር ይችላል። በዚያም ድርጅቱ አሁን በተጋረጠበት አስቸጋሪ ሁኔታ  ራዕዩን እና ዓላማውን ለማሳካት ይረዳዋል። በጥሞና ስለተከታተላችሁኝ እና ንግግር እንዳደርግ ስለፈቀዳችሁልኝ አመስግናለሁ። ስኬታማ ውይይት እመኝላችኋለሁ።
»

አስራ አምስት አባል ሐገራትን ያካተተው የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ ትብብር ጉባኤ አርብ የካቲት 12 ቀን  2004 ዓ. ም ተጠናቋል። አድማጮች አሁን ወደ ሁለተኛው የትኩረት በአፍሪቃ ርዕሰ-ጉዳያችን ነው የምንሻገረው። የሳህል አካባቢ ያሰጋውን አደገኛ ድርቅ የሚመለከት ነው። ከዚህ መሸጋገሪያ ሙዚቃ በኋላ እንመለስበታለን። ሙዚቃው ከዛው ከምዕራብ አፍሪቃ አካባቢ ነው።

ምዕራብ አፍሪቃ  ውስጥ በአደገኛ ድርቅ የተጠቁት የሳህል አካባቢ ሐገራት ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ፣ ሞሪታንያ፣ ኒጀር እና ቻድ ናቸው። የተከሰተው ድርቅ አፋጣኝ ርብርብ ካልተደረገበት ከፍተኛ ዕልቂትን ወደሚያስከትል ረሐብ ሊቀየር እንደሚችል ከወዲሁ እየተገለፀ ነው። የሁኔታውን አሳሳቢነት ተከትሎ  በዚሁ ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮጳ ኅብረት  ሮም ውስጥ ጉባኤ መቀመጣቸው ተዘግቧል።  የአውሮጳ ኅብረት የሠብዓዊ ርዳታ ኮሚሽነር  ክሪስታሊና ጂዎርጂየቫ የሳህል አካባቢ ድርቅ አሳሳቢነትነትን በዚህ መልኩ ገልፀዋል።
 
«የህፃናቱ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ በዚህች ሴንቲ ሜትር ርቀት የሚለካ ነው። ዛሬ የተነጋገርንበት ጉዳይ በሳህል አካባቢ ወደ ቀዩ መስመር የገቡትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት ማዳን የሚመለከት ነው።  ያን ደግሞ በአንድነት እናሳካዋለን። »

በተለይ በኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ሞሪታኒያና ቻድ  ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ድርቁ ለከፍተኛ አደጋ አጋልጧቸዋል። ድርቅ፣ የዝናብ መዘግየትና የምግብ ዋጋ መናር ችግሩን  እንዳባባሰው ተጠቅሷል። በተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ FAO ዳይሬክተር ሆዜ ግራሲያኖ ዳ ሲልቫ እንደሚሉት ከሆነ ድርቁ አፋጣኝ ርብርብ ያስፈልገዋል።

«ድርቅ አለ፤ ረሐብ ግን አልገባም። ረሐቡ እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል። ለዚያ ሁለት ወራቶች አሉን፤ ምናልትም የሶስት ወር ጊዜያት። ከዚያ ግን ዝንፍ አይልም። በተጨማሪም ልናተኩርባቸው የሚገቡ አካባቢዎች አሉ። እንደ ሶማሊያ ያሉ አካባቢዎች  በቅርቡ  ነው ከረሀብ የተላቀቁት፤ ዛሬም ድረስ ታዲያ ርዳታችን ያሻቸዋል።»


የተባበሩት መንግስታት በሶማሊያ የተከሰተው የረሐብ አደጋ ይፋዊ በሆነ መልኩ ማብቃቱን ከገለፀ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መሆኑ ነው የሳህል አካባቢ ድርቅ ሲከሰት። በዚህ የምዕራብ አፍሪቃ አካባቢ ያንዣበበው አደጋ በአፍሪቃ አዲስ ጥፋት እንዳይደገም ያሰጋል ተብሎለታል። ለሳህል አካባቢ ድርቅ 800 ሚሊዮን ዶላር ርዳታ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ድርጅት ዳይሬክተር ጆሴቴ ሺራን፥

«እስካሁን ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሰብስበናል። በዚያ 62 ሺህ ሜትሪክ ቶን ጭነት እና ለህፃናቱ ተጨማሪ አልሚ ምግብ ማቅረብ እንችላለን።  አራት ሚሊዮን ሰዎችን ለአንድ ወር መመገብም ያስችለናል።»

የአውሮጳ ኅብረት ርዳታውን ወደ 30 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ አሳድጎታል። የፌዴራል መንግስቱ በበኩሉ ከወዲሁ የ12 ሚሊዮን ርዳታ አዘጋጅቷል። እንደ ፋኦ ዳይሬክተር  ዳ ሲልቫ ከሆነ በሳህል አካባቢ የተከሰተው ድርቅ ወደ ረሀብ ከተሻገረ የምዕራብ አፍሪቃ አካባቢን ሊያናጋ ይችላል።

«ይሄ ግጭት ያዳቀቀው አካባቢ ነው። ግጭቱን ሊያባብሱ የሚችሉ በርካታ ምክንያቶች አሉ።  ከነዚያ መካከል በምግብ ራስን ያለመቻሉ ሁኔታ በአካባቢው ግጭት ከሚፈጥሩ ምክንያቶች አንዱ ነው።  ስለዚህ ያንን በምንም መልኩ ማስወገድ ያስፈልገናል። »

የምዕራብ አፍሪቃ የሳህል አካባቢ ሐገራት በዓለም የተከሰተው የከባቢ አየር ለውጥ ሰለባ መሆናቸውም  ተገልጿል። ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም የምግብ ፕሮግራም የታቀፉ በርካታ የሳህል አካባቢ  ሰዎች አሁንም ድረስ ከደረሰባቸው አደጋ እንዳላገገሙ ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ