1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 2 2005

ሶማሊያ ተመልሳ መንግሥት አልባ እንዳትሆን ስጋት ማጫሩ፣ ኬንያ ከአይሲሲ ራሷን ለማግለል ድምፀ ዉሳኔ ማስለፍዋ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለሰላም የአካባቢው ሃገራት ጥሪና ተሳትፎ፣ እንዲሁም ሠሜን ሱዳን ከደቡብ ሱዳን ወደ ድንበሯ የሚዘልቀውን የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ላለመዝጋት ቃል መግባቷ፣ የዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዋነኛ ርዕሶች ናቸው።

https://p.dw.com/p/19dUP
የM 23 ወታደሮች በኮንጎ
የM 23 ወታደሮች በኮንጎምስል Melanie Gouby/AFP/GettyImages

እንደ በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ሁሉ በኬንያም ምርጫ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማስረጪያ ከመሆን ይልቅ የሁከት እና የብጥብጥ ሰበብ ሆኖ ሀገሪቱ ላይ የማይፋቅ የታሪክ ጠባሳ ትቶ አልፏል። የዛሬ አምስት ዓመታት ግድም በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ከ1000 በላይ ሰዎች መገደላቸው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቤት፣ ንብረት፣ ቀዬያቸውን ጣጥለው መሰደዳቸው የጠባሳውን ግዝፈት ያጎላዋል። ከእዚያን ጊዜ አንስቶም ኬንያ የዓለም አቀፉ የወንጀል ጉዳዮች ተመልካች ፍርድ ቤት አብይ አጀንዳ ሆና ቆይታለች።

የዛሬ አምስት ዓመት ግድም በኬንያ የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጤት ተከትሎ በተቀሰቀሰ ሁከትና ብጥብጥ የአሁኑ የኬንያ ፕሬዚዳንት እና ምክትላቸው እጃቸው እንደነበረበት በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል። ከእዚያም አልፎ ዓለም አቀፉ የወንጀል ጉዳዮች ተመልካች ፍርድ ቤት በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ ICC ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን እና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶን ከሶ ፍርድ ቤት ለማቆም ይሻል። የኬንያ የምክር ቤት አባላት ግን አይሲሲ የኬንያን ልዕልና ከመፃረሩም በላይ የዳግማይ ቅኝ ገዢዎች አገልጋይ ነው ሲሉ በብርቱ ተችተዋል። ምክር ቤቱ ሀገሪቱ ከአይ ሲሲ ስምምነት ፈራሚ ሃገራት አባልነቷ እንድትወጣም ባሳለፍነው ሐሙስ ድምፅ ሰጥቷል። በኬንያ የእንደራሴዎች ምክር ቤት አብላጫ ድምፅ ያለው ፓርቲ መሪ አዳን ዱዋሌ በምክር ቤቱ የሚከተለውን ተናግረዋል።

የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ
የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶምስል picture alliance/dpa

«በመቀጠል ክቡር አፈጉባኤ፤ አሁን እየወጡ ያሉ ዘገባዎችን ሊመለከቱ ይችላሉ። የምክትል ፕሬዚዳንቱ የክስ ሂደት ሊታይ ሶስት እና ሁለት ቀናት እየቀሩት እንኳን አይሲሲ ምስክሮችን እያሰባሰበ ነው። ሆኖም ክቡር አፈጉባኤ እንደ ሀገር ዛሬ ሉዓላዊነታችንን መሰረት ባደረገ መልኩ ከውሳኔ የደረስን ይመስለኛል። ሁላችንም ብንሆን የመረጠን ሕዝባችንን እና አካባቢያችንን እንወክላለን፤ ከእዚያም ባሻገር ሕገመንግሥቱንና የሀገሪቱን ልዕልና ለማስጠበቅ በእናንተ እና በሕገመንግሥቱ ፊት ቃለ መሀላ ገብተናል። ክቡር አፈ ጉባኤ በውሳኔው እንድንገፋበት እማፀናለሁ።»

ለወትሮው ሄግ ከሚገኘው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር ለመስራት ፍቃደኝነታቸውን ሲያሳዩ የቆዩት የኬንያ ከፍተኛ ባለስልጣናት አሁን የጫወታውን ሜዳ የቀየሩት ይመስላል። ቀድሞ ባላንጣ የነበሩት፣ አይሲሲ ክስ ሊመሰርትባቸው የሚፈልጋቸው የኬንያ ፕሬዚዳንት እና ምክትሉ የሚመሯቸው ፓርቲዎች በኬንያ ብሔራዊ እንዲሁም የእንደራሴዎች ምክር ቤት አብላጫውን መቀመጫ ይይዛሉ። ሠነዱ እንደታቀደለት በኬንያ የእንደራሴዎች ምክር ቤት ተፈርሞ ወደ ተግባር የሚሸጋገር ከሆነ ኬንያ ከ11 ዓመት በፊት ከፀደቀው የሮም ስምምነት እራሷን በማግለል የመጀመሪያዋ ሀገር እንድትሆን ያስችላታል ማለት ነው። አይሲሲን በተመለከተ በኬንያ ምክር ቤት በተካሄደው የድምፅ አሰጣጥ ወቅት በምክር ቤቱ አነስተኛ ድምፅ ያለው ፓርቲ መሪ ፍራንሲስ ንዬንዜ አቋሟቸውን እንደሚከተለው አሰምተዋል።

«መሪዎቻችን በሙያው ብቃት የተካኑ የሕግ ባለሙያዎች አሏቸው፤ እናም ተመራጩ ሀሳብ በፍርድ ቤት መሟገቱ ነው። ሆኖም የሕጉ ተፃራሪ ሆኖ መታየቱ ለሀገሪቱ የሚበጅ አይደለም። እኔ ይህን ጉዳይ ባንሞክረው ይሻላል ባይ ነኝ። ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ድርጊታችን እንኳን ከሮም ስምምነት እያፈነገጥን ነው፤ ያ ደግሞ ለኬንያ የሚጠቅም አይደለም። ምክንያቱም ተስማምተን ፈርመንበታል።»

የሮም ስምምነት ዓለም አቀፉ የወንጀል ጉዳዮች ተመልካች ፍርድ ቤት፤ አይሲሲ እንዲቋቋም መሠረት የሆነው ዓለም አቀፍ የሕግ መዋቅር እውን የሆነበት ነው። ከእዚህ ስምምነት ማፈንገጥ ኬንያን በዓለም አቀፉ መድረክ ጥላ እንዲያጠላባት ያደርጋል ሲሉ ፍራንሲስ ንዬንዜ ስጋታቸውን አክለዋል። የኬንያ ምክር ቤት ኬንያ ከሮሙ ስምምነት ውጪ እንድትሆን የሚያስችላት ሠነድ በ30 ቀናት ውስጥ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብለት በምክር ቤቱ አፈጉባኤ ጀስቲን ሙቱሪ በኩል ውሳኔውን አስተላልፏል።

ከሮም ስምምነት ለመውጣት ድምፅ የሰጠው የኬንያ ምክር ቤት
ከሮም ስምምነት ለመውጣት ድምፅ የሰጠው የኬንያ ምክር ቤትምስል Simon Maina/AFP/Getty Images

«ይህምክር ቤትየዓለምአቀፍወንጀሎችተመልካችሕግቁጥር 16 ሕዝባር 2008ን ተቀባይነት እንዳይኖረው የሚያስችልደንብ በ 30 ቀናት ውስጥ እንዲያሰናዳ ከስውሳኔ ላይ ደርሷል። ደ ንቡን ተከትሎም መንግሥት በሀምሌ 17 ቀን 1998 በተባበሩት መንግሥታት የዲፕሎማቶች ጉባኤ ላይ ከፀደቀው የዓለም አቀፍ የወንጀል ጉዳዮች ተመልካች ፍርድ ቤት ማለትም ከ አይሲሲ የሮም ስምምነት እራሱን ባስቸኳ ይያገላል። በእዚህ እንስማማለን የምትሉ ድምፃችሁን አሰሙ፤ አንስማማም የምትሉ እንደዛው፤ እንስማማለን የሚለውበ ልጧል።»

እጎአ በ2007 በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተቀሰቀሰው ሁከት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ኬንያውያን በምክር ቤቱ ውሳኔ ቅር መሰኘታቸውን ገልፀዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናልም የኬንያ ምክር ቤት ድምፅ አሰጣጥን በማውገዝ የአይሲሲ ተግባር በኬንያም ሆነ በአህጉሪቱ እንዲስተጓጎል ሰበብ ይሆናል ሲል ስጋቱን አሰምቷል። የዩኤስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በበኩሉ የኬንያ መንግሥት ከአምስት ዓመት በፊት የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተቀሰቀው ብጥብጥ ሰለባ ለሆኑ ኬንያውያን ፍትህ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት የገባውን ቃል እንዲያከብር በጥብቅ አሳስቧል። ዩኤስ አሜሪካ የሮማው ስምምነት ፈራሚ ሀገር አለመሆኗ ይታወቃል። ዓለም አቀፉ የወንጀል ጉዳዮች ተመልካች ፍርድ ቤት ማለትም አይሲሲ ክስ መመስረት የሚችለው የሮማውን ስምምነት ፈርመው በተቀበሉ ሃገራት ውስጥ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ብቻ ነው።

ኬንያ በዓለም አቀፉ የወንጀል ጉዳዮች ተመልካች ፍርድ ቤት ሕጎች ላለመዳኘት እና እራሷን ከአባልነት ለማግለል ብትሻም ከአባልነቷ ለመወገድ ግን በቅድሚያ ማመልከቻዋን በይፋ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስገባት ይጠበቅባታል። ከእዚያም ሂደቱ ውሳኔ እስኪሰጥበት ድረስ ቢያንስ አንድ ዓመት ያህል ሊዘልቅ ይችላል። ያም በመሆኑ የኬንያ ምክር ቤት ውሳኔ አይሲሲ የጀመረውን የወንጀል ማጣራት ስራ በምንም መልኩ የሚያሰናክል አይደለም ሲሉ የአይሲሲ ቃል አቀባይ ፋይድ ኤል አብዳላህ ሐሙስ፣ ነሐሴ 30 ቀን 2005 ዓም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው አስታውቀዋል። ሆኖም ኬንያ ለተባበሩት መንግሥታት የምታስገባው ማመልከቻ ተቀባይነት ካገኘ ሀገሪቱ ውስጥ ወደፊት ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ቢፈፀሙ እንኳን አይሲሲ ክስ መመስረት አይቻለውም።

የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ እና የኮንጎው ጆሴፍ ካቢላ
የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ እና የኮንጎው ጆሴፍ ካቢላምስል picture-alliance/dpa

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

ወደ ታላላቅ ሀይቆች አዋሳኝ ሃገራት እናምራ። በከርሰ ምድር ሀብት እጅግ የበለፀገችው ሆኖም ሕዝቦቿ በድህነት አረንቋ የሚማቅቁባት፣ ተደጋጋሚ ጦርነት እና የእርስ በእርስ ግጭት ያዳቀቃት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ነው የምንቃኘው። በኮንጎ መንግሥት እና M23 በሚል ስያሜ በሚታወቀው ዓማፂ ቡድን መካከል አፋጣኝ የሰላም ድርድር እንዲጀመር የተጠየቀው ሐሙስ፣ ነሐሴ 30 ቀን 2005 ዓም ነበር።

ጥሪውን ያደረጉትም የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ናቸው። የምሥራቃዊውን ኮንጎ ቀውስ ለማስወገድ የታላላቆቹ ሃይቆች አዋሳኝ መንግሥታት መሪዎች ፣ ካምፓላ ዩጋንዳ ውስጥ ያደረጉትን ጉባዔ ተከትሎ አማፂያኑ ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል። በአንፃሩ የኮንጎ መንግሥት በቅርቡ ከተ መ ድ ጣልቃ ገብ ጦር ጋር ሆኖ በዓማፂያኑ ላይ ከተቀዳጀው ድል አንፃር ከንግግር ይልቅ ፍላጎቱ ዓማፂያኑን ትጥቅ ማስፈታቱ ላይ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። የደቡብ አፍሪቃ የጸጥታ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ሚስ ናኒ ካካ እንደሚሉት የሰላም ንግግር ጥሪው ጥሩ ለአካባቢው መረጋጋት መልካም አጋጣሚ ነው።

«ምክንያቱም ሁለቱም ወገኖች ወደ ውይይት ጠረጴዛ እንዲመለሱ የአካባቢው ሃገሮች መሪዎችም እንዲሳተፉበት አስችሏል።የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ፕሬዚዳንት ጆሰፍ ካቢላም ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተዋል። የተመድ የአካባቢው ልዩ መልዕክተኛ ሜሪ ሮቢንሰን እና የአፍሪቃ ኅብረቷ ዶክተር ድላሚኒ ዙማም መገኘታቸው የፖለቲካ ግፊት አለው። እንደሚመስለኝ ይህ መልካም አጋጣሚ ነው።»

የኮንጎ መንግሥት በ ተ መ ድ ጣልቃ ገብ ጦር የሚደገፍ ሲሆን፤ M 23 የተሰኘው የአማጺያን ቡድንን ደግሞ ሩዋንዳ ከጀርባ እንደምታግዝ ብሎም ነፍጥ እንደምታስታጥቅ ይነገራል። በምስራቃዊ ኪቩ የሚንቀሳቀሱት የM23 አማፂ ቡድን አባላት ቁጥራቸው ወደ 1000 እንደሚጠጋ ይገመታል። በአካባቢው የተመድ 20 000 የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን አስፍሯል። የተመድ ሰላም ለማስከበር በሚል በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ካሰፈራቸው የሰላም አስከባሪ ጓዶች መካከል በቁጥር ኮንጎ ውስጥ የሰፈሩትን የሚስተካከል የለም። እንዲያም ሆኖ ግን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት በተመድ እየተደገፈም ቢሆን በቁጥር አነስተኛ የሆኑትን አማፂያን ሊያሸንፍ ያለመቻሉ ምስጢር ብዙዎችን የሚያስደምም ጉዳይ ነው።

በሶማሊያ ሞቃዲሾ የመንገድ ትዕይንት
በሶማሊያ ሞቃዲሾ የመንገድ ትዕይንትምስል DW/B. Rühl

M23 የተሰኘው ዓማፂ ቡድን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦር ከድተው የወጡ ወታደሮች ያቋቋሙት ቡድን ነው። የእዚህ ዓማፂ ቡድን አባላት አብዛኛዎቹ በትውልድ የቱትሲ ጎሳዎች እንደሆኑ ይታወቃል። ከሩዋንዳው የዘር ፍጅት ወዲህ በርካታ የሁቱ ሚሊሺያዎች ከነትጥቃቸው ወደ ኮንጎ ድንበር ሸሽተው በሰፋፊ ጫካዎች ውስጥ የመሸጉ ሲሆን፤ የሁቱ ሚሊሺያዎችን ያባረረው የሩዋንዳ መንግሥት አብላጫ ቱትሲዎች የሚገኙበትን የM23 ዓማፂ ቡድን ከጀርባ ይደግፋል በሚል ተደጋጋሚ ትችት ይሰነዘርበታል።

በሐሙሱ ጉባኤ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጆሰፍ ካቢላ ካምፓላ ውስጥ ተገናኝተው መነጋገራቸው ለሂደቶች መለሳለስ አስተዋጽዖ ሳያደርግ እንዳልቀረ ተገምቷል።

ሱማሊያ ዳግም መንግሥት አልባ እንዳትሆን ማስጋቱ

የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን ሶማሊያ ተመልሳ መንግሥት አልባ እንዳትሆን ያሰጋታል ሲሉ በእዚሁ ሳምንት ማስጠንቀቃቸው ተደምጧል። ዋና ፀሐፊው ያ እንዳይከሰት ሶማሊያ ውስጥ ሰላም ለማስከበር ለሰፈረው የአፍሪቃ የሰላም አስከባሪ ሀይል የጦር ሄሊኮፕተሮችና ተሽከርካሪዎች ድጋፍ በአፋጣኝ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል። አልሸባብ የተሰኘው እስልምና አክራሪ ታጣቂ ቡድን አሁንም ድረስ አብዛኛውን የሶማሊያ ደቡብ ክፍሎች ተቆጣጥሮ እንደያዘ ነው ሲል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። ሰኞ፣ ነሐሴ 27 ቀን 2005 ዓም ጀምሮ ለአምስት ቀናት የዘለቀው የሶማሊያ መንግሥት ጉባኤ በሀገሪቱ የፌዴራል መንግሥትን በማጠናከር፣ ሕገመንግሥቱን በማሻሻል እና አሁን ያለው መንግሥት የስልጣን ዘመን ከሶስት ዓመታት በኋላ ሲጠናቀቅ ምርጫን በማከናወን ዙሪያ መነጋገሩ ተጠቅሷል። በጉባኤው ራሷን ነፃ ሀገር አድርጋ የሰየመችው ሶማሊላንድ እና ከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ተወካዮቻቸውን እንዳልላኩና በጉባኤው እንዳልተሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።

የደቡብ ሱዳን እና የሱዳን ፕሬዚዳንቶች
የደቡብ ሱዳን እና የሱዳን ፕሬዚዳንቶችምስል Reuters

ደቡብ ሱዳንና ሱዳን የነዳጅ ሀብት ቁርሾ

ደቡብ ሱዳን በሀገሪቱ ሩብ የበጀት ዓመት ብቻ ከነዳጅ ሽያጭ ወደ 1, ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገባቷን የነዳጅ ሚንስትሩ በእዚሁ ሳምንት አስታውቀዋል። ደቡብ ሱዳን ይህን ያህል ገቢ ያገኘችው ከሱዳን ጋር በገባችው ቁርሾ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የነዳጅ ሽያጭ በሚያዝያ ወር በድጋሚ ካንሰራራ ወዲህ መሆኑ ነው።

ደቡብ ሱዳን ከነዳጁ ሽያጭ 91 ሚሊዮን ዶላሩን ሱዳንን ለሚያቋርጠው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ የአገልግሎት ኪራይ ክፍያና ለፖርት ሱዳን የወደብ አገልግሎት መክፈሏንም ሚንስትሩ አክለው ጠቅሰዋል። ተጨማሪ 147 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ስትገነጠል ሱዳን ላጣችው ገቢ ካሳ እንዲሆን መክፈሏንም የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ሚንስትር ይፋ አድርገዋል። ደቡብ ሱዳን በቀን 180 000 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ እንደምታመርት የሚታወቅ ሲሆን አሁን ሱዳን በድንበሯ የሚያልፈውን የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ እንደማታቋርጥ ቃል ከገባች ወዲህ ተጨማሪ 20 000 በርሜል ነዳጅ ለማምረት ማቀዷን አስታውቃለች። 98 በመቶ ዓመታዊ ገቢዋ በነዳጅ ሽያጭ ላይ የተመሰረተው ደቡብ ሱዳን ድፍድፍ ነዳጇን በመሸጥ ምጣኔ ሀብቷን ለመደጎም እጅግ የመሻቷን ያህል ሱዳንም ከነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦው ክፍያ የሚገኘውን ገቢ አጥብቃ ትፈልገዋለች። ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ከመገንጠሏ አስቀድሞ ነዳጅ ለሱዳን የውጭ ንግድ ዋነኛው እንደነበር ይታወሳል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ