1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 28 2013

በተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራት የሠፈረዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት በየአካባቢዉ ከሸመቁ ደፈጣ ተዋጊዎች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ብቃት፣ ንቃትና ትጥቅ ያለዉ ሠራዊት ነዉ።ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣቱ ግን እያጠያያቀ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3uS0q
UNO-Mission Kongo
ምስል DW/D. Köpp

የተመድ የሰላም ተልዕኮ በአፍሪቃ፣ የሶማሊላንድ ምርጫ

ትኩረት በአፍሪቃ ሁለት ርዕሶችን ይዳስሳል።የመጀመሪያዉ አፍሪቃ ዉስጥ በተለያዩ ሐገራት የሠፈረዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ተልዕኮዉን በአግባቡ መወጣት አለመቻሉን የሚቃኝ ነዉ።በተለይ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የሠፈረዉ የዓለም አቀፉ ድርጅት ሠራዊት ሠላማዊ ሰዎችን ከጥቃት አለመከላከሉን ዝግጅቱ እንደ አብነት ይጠቅሳል።ሁለተኛዉ ርዕሥ፣ ሶማሊላንድ ዉስጥ ባለፈዉ ሰኞ የተደረገዉን የብሔራዊና የማዘጋጃ ቤት የምክር ቤት አባላት ምርጫን ነዉ የሚያወሳዉ።ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተለዉ አጠናቅራቸዋል።

ሠላም ማስከበር ሠላማዊ ሕዝብ

በተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራት የሠፈረዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት በየአካባቢዉ ከሸመቁ ደፈጣ ተዋጊዎች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ብቃት፣ ንቃትና ትጥቅ ያለዉ ሠራዊት ነዉ።ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣቱ ግን እያጠያያቀ ነዉ።ምሳሌ፤ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ።በዚያች ሰፊ፣ ለም፣ የማዕድን ሐብታም ሐገር፣ ሰሜናዊ ኪቩ በተባለዉ ግዛት በምትገኘዉ በኒ ወረዳ የሸመቁ ደፈጣ ተዋጊዎች ከ2019 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ) ወዲሕ ብቻ 1200 ሰዎች ገድለዋል።
ባካባቢዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራዊት ከሠፈረ ዓመታት አስቆጥሯል።የዶቸ ቬለዉ ባልደረባ አይዛክ ሙጋቤ ይጠይቃል፣ ሠላም አስከባሪ ወታደሮች ሠላማዊ ሰዎችን ከጥቃት መከላከል እንዴት ተነሳናቸዉ? እያለ።መልስ፣ ለጊዜዉ የለም።ከ1200ዉ አንዷ ግን በቀደም ተቀበሩ።
ሟች ቩቶሊቶል የተባረዉ መንደር ነዋሪ ነበሩ።የገደላቸዉ የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይላት (ADF) የተባለዉ አማፂ ቡድን ነዉ።ADF ሠላማዊ ሕዝብን የሚያሸብር ነዉጠኛ ቡድን እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል።የሟች ወንድም ካሴሬካ ካሉም አባባሉን ይጋራሉ።
                                             
«እሕቴ ናት።በተባባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይላት (ADF) ተገደለች።ሕፃናት ትታብን ሞተች።መንግስት  የADF አሸባሪዎችን ለማጥፋት እንዲረዳን የምንጠይቀዉ ለዚሕ ነዉ።እሕታችን የአምስት ወር ጨቅላ ጥላ ነዉ የሞተችዉ።ባጠቃላይ 7 ልጆች ነበሯት።»
አማፂያኑ ባንድ ሌሊት ብቻ 22 ሰላማዊ ሰዎችን በስለትና በገጀራ ገድለዋል።ኮንጎ ዉስጥ MONUSCO በሚል ምፃረ ቃል የሚጠራዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ በርካታ ሠላም አስከባሪ  ወታደሮች አሠፍሯል።በሠላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃትና ግድያ ግን አላስቆመም።በምሕፃሩ SOAS ተብሎ የሚጠራዉ የለንደኑ  School of Oriental and African Studies ዩኒቨርስቲ ባልደረባ ፊል ክላርክ MONUSCOን አዝጋሚ ተማሪ ይሉታል።
 «MONUSCO ለመማር በጣም አዝጋሚ ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ኮንጎ ዉስጥ ሠላም ማስከበር እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ረጅም ጊዜ ወስዶበታል።ከኪንሻሳ መንግስት ጋር የተጣጣመ ግንኙነት ለመመሠረት ለረጅም ጊዜ ሲታገል ነበር።ይልቅዬ ከኮንጎ ጦር ኃይል ጋር ያለዉ ግንኙነት ጥንቃቄ የተሞላበት ቢሆንም የተሻለ ነዉ።ጦሩ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግፍ እየፈፀመ እንኳ ተልዕኮዉ ትብብሩን አላቋረጠም።»
የዓለም አቀፉ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ባልደረቦች ሴቶችን አስገድደዉ ወይም በጥቅማ ጥቅም ደልለዉ  መድፈር፣ ማንገላታታቸዉና ፆታዊ ጥቃት ማድረሳቸዉ የሠራዊቱንና የአጠቃላይ ተልዕኮዉን  ተዓማኒነት አጠያያቂ አድርጎታል።የደረሰዉን ግፍና በደል ያጋላጠዉ ኮድ ብሉ ካምፔይን የተባለዉ ስብስብ ባልደረባ ፓዉላ ዶኖቫን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ሳይቀር ትወቅሳለች።
ዶኖቫን እንደምትለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ሳይቀሩ የድርጅቱን ሠላም አስከባሪ ኃይል ሴቶችን ከሚደፍሩና የፆታ ጥቃት ከሚያደርሱ ወገኖች ማፅዳት አልፈለጉም።
«ፆታዊ ጥቃት በማድረስ የተጠረጠሩi የተባበሩት መንግስታት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ባልደረቦች ካልተመረመሩና ጥፋተኞቹ ለፍርድ ካልቀረቡ፣ ተጠያቂነት የለም።ይሕ ለጥፋተኞቹም ለሌሎችም የሚያስተላልፈዉ መልዕክት እንዲሕ ዓይነቱ ጥቃት ይፈቀዳል የሚል ነዉ።»
የጀርመኑ የፍሬድሪሽ ኤበርት ተቋም የአፍሪቃ ጉዳይ ኃላፊ ሔንሪክ ማያሐክ ግን የሠላም አስከባሪ ተልዕኮዎች ሚናን አሳንሶ መመልከት አይገባም ባይ ናቸዉ።ማያሐክ እንደሚሉት ሠላም አስከባሪዉ ሠራዊት በዘመተና በሠፈረበት አካባቢ የሚገጥመዉ ዉስብስብ ሁኔታ ሊጤን ይገባል።
«ሠላም አስከባሪ ተልዕኮዎች ጠቃሚ ናቸዉ።ምክንያቱም እንደ ደቡብ ሱዳንና ማሊን በመሳሰሉ ሐገራት ሠላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ይከላከላሉ።ለልማት የሚረዳ መረጋጋት ያሰፍናሉ፤ አንዳድ አካባቢዎች በመንግስት ግንባታ ሒደት ጠቃሚ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።የተለያዩ ሐገራት በተልዕኮዉ ስለሚሳተፉ (ሠራዊት ስለሚያዘምቱ) ኃላፊነት የመጋራት ምልክትም ነዉ።»
በዓለም እጅግ  የተወሳሰበ ወይም ከባድ ከሚባለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 5 ሠላም የማስከበር ተልዕኮ 4ቱ የሚገኘዉ አፍሪቃ ዉስጥ ነዉ።ማሊ፣ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ማዕከላዊ አፍሪቃና ደቡብ ሱዳን።
ድርጅቱ የ4ቱን ሐገራት ጨምሮ አፍሪቃ ዉስጥ በ12 ሐገራትና ግዛቶች ሠላም አስከባሪ ሠራዊት አሥፍሯል።ያም ሆኖ አፍሪቃ ዉስጥ የሚደረገዉ የሠላም ማስከበር ተልዕኮና ዉጤቱ ባለፉት 25 ዓመታት ብዙም መሻሻል አላሳየም።ሠላማዊ ሰዎችም በየአካባቢዉ ከሸመቁ ሚሊሺያዎች፣ከየሐገሩ መንግስት ጦር ጥቃትና  አንዳዴም ከራሱ ከሠላም አስከባሪዉ ሰራዊት እንግልትና መደፈር አላመለጡም።
 

Demokratische Republik Kongo | Rebellengruppe : Mama Faida: "Ich schlafe mit meiner Waffe, wie mit einem Baby"
ምስል Mariel Müller/DW
Martin Kobler Chef der UNO-Mission Kongo Besuch Schule
ምስል Dirke Köpp

የሶማሊላንድ ምርጫ 

Somaliland Wahlen
ምስል Getty Images/AFP

ከሠላም መደፍረስ-ማስከበሩ ጣጣ ገለል-ፈንጠር፤ ከፖለቲካ ምጣኔ ሐብቱ ዉዝግብ-ከበርቻቻ ሰከን-ራቅ ብላ ዓለምን ረስታ በረሳችዉ ዓለም የተረሳችዉ ሶማሊላንድ ባገባደድነዉ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ የምክር ቤት እንደራሴዎችንና የማዘጋጃ ምክር ቤት አባላትን መርጣለች።
እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1991 ከሞቃዲሾዉ ማዕከላዊ አስተዳደር ተገንጥላ የራስዋን ሪፐብሊካዊ መንግሥት ካወጀች ዘንድሮ 30 ዓመት ደፈነች።ሐርጌሳ ላይ ለቆመዉ መንግስት እስካሁን አድም ሐገር እዉቅና አልሰጣትም።
ከኢትዮጵያ እስከ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ከአዉሮጳ እስከ ዩናይትድ አረብ ኤምሬስትስ የሚገኙ መንግሥታት ግን ወደብ-ሥልታዊ ምድሯን ሲፈልጉ አብረዋት ይሰራሉ።ሐገራት እዉቅና ሰጧትም ነፈጓት ሠላም በማያዉቀዉ የአፍሪቃ ቀንድ የሰላም ደሴት፣የዴሞክራሲ አብነትም እየሆነች ነዉ።ፕሬዝደንቷን በምርጫ ትሾማለች።ዘመነ-ሥልጣኑ ሲያበቃ አዲስ መርጣ አሮጌዉን ታሰናብታለች።
የምክር ቤት እንደራሴዎች ምርጫ ስታደርግ ግን በ16 ዓመታት ዉስጥ የሰኞዉ የመጀመሪያዉ ነዉ።82 መቆመጫዎች ላሉት ምክር ቤት 246 ዕጩዎች ተወዳድረዋል።አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ድምፅ ሰጥቷል።የሐርጌይሳዉ ነዋሪ  እንደሚሉት ምርጫዉ ትንሺቱን ሥልታዊቱን፣ ሰላማዊቱን  ግን በዓለም የተረሳችዉን ሶማሊላንድ ከዓለም ለመቀየጥ ተስፋ የሚያሳድር ነዉ።
«ይሕ ዛሬ የተደረገዉ የምክር ቤት አባላት ምርጫ ለሶማሊላንድ ትልቅ እመርታ ነዉ።በዚሕ ምርጫ ዓለም እዉቅና እንዲሰጠን እንፈልጋለን።በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዉስጥ መቀመጫ እንዲኖረን እንፈልጋለን።»
የአዛዉንቱ ምኞት እንዲሕ ባጭር ጊዜ መሳካቱ አጠራጣሪ ነዉ።የፕሬዝደንት ሙሲ ብሒን ገዢ ፓርቲን ጨምሮ ሶስት ትላልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፎካከሩበት ምርጫ ዉጤትም ገና አልታወቀም።የድምፅ  አሰጣጡን ሒደት ከታዘቡት አንዱ ኬንያዊዉ የፀረ-ሙስና ታጋይ ጆን ጊቶንጎ እንደሚሉት ግን ሶማሊ ላንድ ከተራዉ ሕዝብ ወደ ፖለቲከኞች (ከታች ወደላይ) በሚያድግ ባልተበረዘ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ናት።
ከደቡብ አፍሪቃ የተጓዘዉን የታዛቢዎች ቡድን የመሩት ግሬግ ሚልስ ደግሞ ሶማሊላንድን «ለዴሞክራሲና ለልማት በፅናት የቆመች፣ ሁሉም ወገን ሊደግፋት የሚገባ፣ የአፍሪቃ አብነት ብለዋታል። 

Somalia Frauen in Berbera, Somaliland
ምስል picturealliance/robertharding/M. Runkel

ነጋሽ መሐመድ