1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቸርኖቢልና ፉኩሺማ፣

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 19 2003

የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር እስክምን ድረስ አስተማማኝ ነው? ይህ ጥያቄ መልስ ሳያገኝ የቸርኞቢሉ አደጋ በተከሠተ በ 25ኛው ዓመት፣ በጃፓንም ተመሳሳይ ሁኔታ ማጋጠሙ ፤ እስካሁን ውይይቱ እንዲቀጥል አድርጓል።

https://p.dw.com/p/RKgO

በትናንቱ ዕለት፤ ዩክሬይን ውስጥ ከ 25 ዓመት በፊት በኑክልየር ኃይል ማመንጫ አውታር ፍንዳታና ቃጠሎ በሰውና በተፈጥሮ ላይ የደረሰው አደጋ፣ በልዩ ሥነ ሥርዓት መታሰቡ የሚታወስ ነው። የአቶም ኃይል አደጋ ፣ ቸርኖቢል ተባለ ፉኩሺማ ድንበር የሚያግደው አይደለም። ታዲያ የኑክልየር አደጋን የሚመለከት ትክክለኛ ፍትኀዊም የሆነ ዓለም አቀፍ ተቋም አለ ወይ? ለሚደርሰው ጥፋት ተጠያቂው፣ ዋጋ ከፋዩ ማን ይሆናል?

በዓለም ዙሪያ የተለያዩ መንግሥታት፤ የቸርኖቢሉ አውታር የፈነዳበትን ቦታ ፣ የህንጻውን ውስጣዊ ግንብ ለማጽዳት 550 ሚሊዮን ዩውሮ ሊሰጡ ቃል ገብተው ነበር። ቦታው ፣ ከ 25 ዓመታት ወዲህም ቢሆን እስካሁን እንደተበከለ ነው። በዚያ ቦታ መርዘኛው የአቶም ጨረር ፣ የግሪን ፒስ ባልደረባና ተመራማሪ ሃይንትዝ ስሚታል እንዳሉት ከመደበኛው 100 እጥፍ የላቀ ነው።

(1) ጨረሩ ከምድር አይደለም የሚፈነጥቀው በቀጥታ ከአውታሩ ፣ ሜትር ስፋት ካለው ግንብ ውስጥ ነው የሚወጣው። »

በዓለም አቀፍ ደረጃ 25 ዓመታት ሲያነጋግር የቆየው የቸርኖቢሉ የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር ፍንዳታ ፤ ወደፊት የሚመጣውን ትውልድም ሲያነጋግር የሚኖርና የሚያሳስብ ሁኔታ ነው። በቸርኖቢል የተደናገጠው የዓለም ማኅበረሰብ ፤ የጃፓኑ የፉኩሺማው ተመሳሳይ አደጋ ተጨምሮለታልና።

የዩክሬይን መንግሥት በቅርቡ ኪቭ ላይ በተካሄደው የገንዘብ ለጋሽ አገሮች ጉባዔ በ 1,5 ቢልዮን ዩውሮ በቸርኖቢልና አካባቢው የማጽዳት እርምጃ ለመውሰድና አካባቢውን መልሶ የደኅነነት ቀጣና ለማድረግ አቅድ እንዳለው ነው ያስታወቀው። ለታቀደው እርምጃ ድጎማ የሚሰጡ የሚችሉ አገሮች ብቻ ናቸው። በኑክልየር አደጋ የሚደርስን የጥፋት ወጪ ከፋዮች ፤ እስካሁን በተናጠል መንግሥታት እንጂ ዓለም አቀፍ ተቋም አይደለም።

በጀርመን ፤ የታኅታይ ሳክሰኒ (ኒደርዛኽሰን)ፌደራል ክፍለ-ሀገር ም/ቤት የአረንጓዴው ፓርቲ አባልና የህዝብ እንደራሴ እሽቴፋን ቬንትዘል---

«ያኔ በሩሲያ አልነበረም የምንኖረው ግን እንዴት በጣም የሚያናድድ ነገር ነው። ያኔ የሶቭ የት ዜጎችም ሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአጠቃላይ የውሸት ዜናም ሆነ መረጃ እንደቀረበለት ሁሉ ፤ እንሆ ዘንድሮም ከጃፓን ፤ ፉኪሺማ ተመሳሳይ ሁኔታ መቅረቡ የሚያበሳጭ ነው። ይህን የተዛባ ሁኔታ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትና ዓለም አቀፉ የአቶም ኃይል ተቋም እንዲሁ መቀበላቸው፤ የጀርመን የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ሚንስቴርም ሆነ መንግሥት ፤ ይህ ትክክል አይደለም ብለው እንዲታረም አለማድረጋቸው ይገርማል። ይህ መጠየቅ ያለበት ጉዳይ ነው። የየሃገራቱ ፓርላማዎች እንዲነጋገሩበት መጠየቅ ያሻል። እስካሁን ይህን ጉዳይ በተመለከተ ትክክለኛ ውይይት ተካሂዶ አያውቅም»።

የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮች፤ ፍጹም አስተማማኝ ሊሆኑ እንደማይችሉ ፤ መላው ዓለም በፉኩሺማ ከደረሰው አደጋ ሳይማር አልቀረም። የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር፣ በተፈጥሮ አደጋና በሰው ሠራሽም ቢሆን አደጋ ሊያጋጥመውና ለሰዎች፣እንስሳት፤ ዕጽዋት አፈር ፣ ድንጋይ ፣ ለሁሉም ጠንቅ የሚሆነውን መርዘኛ ጨረር በየቦታው በነፋስና ደመና ሊያዳርስ የሚችል ነው። የሳይንስ ምሁርና የአቶም ኃይል ተቺ Keith Baverstock በአቶም ጨረር ሳቢያ የሚደርስ አደጋን፣ ከመድረሱ በፊትና በኋላም እንዴት መከላከል እንደሚቻል እርምጃ እንዲወሰድ የሚያበቃ የተቀናጀ ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅት የለም ይላሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች፤ IAEA እና WHO እንደርሳቸው አባባል ያን ይህል እምነት የሚጣልባቸው አይደሉም።

«እንደሚመስለኝ፤ ኀላፊነትን መሸከም የሚችሉ አማራጭ ድርጅቶችያስፈልጉናል። እናው ራሳችን ማቋቋም እንችላለን። በዚህ ጥያቄ ረገድ፣ መንግሥታትንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶችን እናምናለን። ግን የራሳችንን ፤ ከመንግሥት ቁጥጥር ነጻ ሆነው ፤ በሙያ ብቃት ባላቸው ሰዎች በመካት የሚሠሩ ድርጅቶች መመሥረት እንችላለን። ይህን መሰሉ ድርጅት ደግሞ፤ ዛሬ ካሉት ተመሳሳይ ወይም ላቅ ያለ ተዓማኒነት ያለው ይሆናል።»

(ሙዚቃ)

ወደቀጣዩ ርእስ እንሸጋገር። አፍሪቃ ከኋላ ቀርነት ለማንሠራራት ብሎም በሁለንተናዊ ልማት ለማደግ-ለመመንደግ ፣ በራሱ ሥነ ቴክኒክ መመካትና ጠንክሮ መሥራት ይበጀዋል ካሉን፤ በደቡብ አፍሪቃ ከ 40 ሺ የማያንሱ ተማሪዎች የሚገኙበት የስዋኔ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ከሆኑት ከደክተር ማሞ ሙጬ ጋር ያደረግነው ጭውውት ፣ ክፍል ሁለት ይቀጥላል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ