1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ቻርሊ ኤብዶ» በሙስሊሙ ዓለም ቁጣ ቀሰቀሰ

ቅዳሜ፣ ጥር 9 2007

የፈረንሳዩ ምጸታዊ ጋዜጣ «ቻርሊ ኤብዶ» ነብዩ መሐመድ ላይ የሚሳለቅ ምስል በገፁ ላይ በድጋሚ ካወጣ በኋላ በዓለም ዙርያ በሚገኙ የሙስሊም ሃገራት ከፍተኛ ተቃዉሞ አጭሯል። በኒጀር ዚንደር ከተማ በሚገኝ አንድ የፈረንሳይ የባህል ተቋም እና ሦስት አብያተ ክርስትያናት ላይ የእሳት ቃጠሎ ጥቃት ደርሶ አራት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1EMAR
Niger Proteste gegen Mohammed Karikaturen in Charlie Hebdo 16.1.2015
ምስል STR/AFP/Getty Images

ከሟቾቹ መኻከል አንደኛው ፖሊስ እንደሆነ ተገልጧል። በጥቃቱ 45 ሰዎች መቁሰላቸዉም ተመልክቷል። በኒጀር ከፍተኛ ተቃዉሞ ከተካሄደ ከአንድ ቀን በኋላ ቅዳሜ ጥር 9 ቀን 2007 ዓም መዲና ኒያሚ ላይ ዳግም ከፍተኛ ተቃዉሞ መደረጉ ተጠቅሷል። መዲና ኒያሚ በሚገኘዉ አንድ ትልቅ መስጊድ አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የሚያደርጉትን ከፍተኛ ተቃዉሞ ለመበተን የፀጥታ አስከባሪ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ መጠቀሙም ተመልክቷል። ይህ የተቃዉሞ ሰልፍ እንዳይደረግ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ቀደም ሲል አግደዉ ነበር። በኒጀር የሚገኘዉ የፈረንሳይ ኤንባሲ ፈረንሳዉያን ከቤታቸዉ እንዳይወጡ ማስጠንቀቁም ተመልክቷል።

ፓኪስታን ካራቺ ከተማ የሚገኙ ሙስሊም እምነት ተከታዮች በፈረንሳይ ኤንባሲ ላይ ጥቃት ጥለዉ ሦስት ሰዎች መጎዳታቸዉም ተገልጾአል። በዮርዳኖስ እና በአልጀርያ መዲኖች ኦማን እና አልጀርስ ዉስጥ ታላቅ የተቃዉሞ ሰልፍ እንደነበርም ተያይዞ ተመልክቷል። በእስራኤል እየሩሳሌም ጽዮን ተራራ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ተሰብስበዉ ተቃዉሟቸዉን አሳይተዋል። የፈረንሣዩ «ቻርሊ ኤብዶ» በድጋሚ ያወጣው የነብዩ መሐመድ ምስል የሚያነባ ሲሆን፦ «እኔም ሻርሊ ነኝ» የሚል ፅሑፍ አለው። «እኔም ሻርሊ ነኝ» የሚለው መፈክር ፈረንሣይ መዲና ፓሪስ ውስጥ በእስልምና አክራሪዎች ለተገደሉት 12ቱ ሰዎች አጋርነትን ለማሳየት የተሰራጨ እንደሆነ ይነገራል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ