1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻይናና አፍሪቃ

ዓርብ፣ ሰኔ 9 1998

የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ያባው አፍሪቃን ይጎበኛሉ

https://p.dw.com/p/E0ib

ዌን ከቅዳሜ አንስቶ አንድ ሳምንት በሚዘልቀው የአፍሪቃ ቆይታቸው ግብፅ፣ ጋና ፣የኮንጎ ሪፐብሊክ ፣አንጎላ ፣ደቡብ አፍሪቃ ፣ታንዛንያና ኡጋንዳን ነው የሚጎበኙት።የጉዞአቸው አላማም ከተጠቀሱት አገራት ጋር የኢኮኖሚና የንግድ ስምምነቶችን መፈራረም ነው። በአሁኑ ወቅት ከአፍሪቃ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት አቅርቦት የምታገኘው ቻይና በአህጉሪቱ ልዩ ልዩ የልማት ዕንቅስቃሴዎች ውስጥም በስፋት ተሰማርታለች።ቻይና ከአፍሪቃ አገራት ጋራ ያላትን ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረች ነው።መሪዎችዋም በተደጋጋሚ ጊዚያት አፍሪቃ እየተመላለሱ ነው። በዚህ ዓመት ብቻ የቻይና መሪዎች የአፍሪቃ ጉብኝት ሲታይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርዋ በጥር ወር ፕሬዝዳንትዋ በሚያዚያ አፍሪቃ ነበሩ። አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትርዋ ከመጪው ቅዳሜ አንስቶ በሰባት የአፍሪቃ አገራት ይዘዋወራሉ።በአሁኑ ሰዓት ከሀምሳ ሶስቱ የአፍሪቃ አገራት አርባ ሰባቱ ከቤይጂንግ ጋራ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አላቸው።አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ሀገራት በቻይናውያን ሰራተኞች ተጨናንቀዋል።ቻይናውያን በአፍሪቃ በአውራ ጎዳና ፣ በባቡር ሀዲድ ፣ በወደብ ስራ እና በህንፃ ግንባታዎች በብዛት ተሰማርተዋል። የቻይና ሸቀጣ ሸቀጦችም በአፍሪቃ ያልገቡበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል። የቻይናና የአፍሪቃ የንግድ ልውውጥ ከቀድሞው ጋራ ሲነፃፀር እጅግ አድጎዋል። የዓምናው የንግድ ልውውጥ አርባ ቢሊዮን ዶላር ነበር።ይህ ደግሞ ከካች ዓምናው ጋራ ሲነፃፀር በሰላሳ አምስት በመቶ ከፍ ያለ ነው ።ከዛሬ አራት ዓመቱ ጋራ ሲወዳደርም በአራት ዕጥፍ ነው የጨመረው ።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቻይናን ከአፍሪቃ ጋር ይበልጥ እያቀራረባት የመጣው ዋነኛው ጉዳይ ደግሞ ወደፊት በመገስገስ ላይ ባለው ኢኮኖሚዋና ምክንያት የነዳጅ ዘይት ፍላጎትዋ እጅግ መናሩ ነው።ቻይና ወደ ሀገርዋ ከምታስገባው ድፍድፍ ዘይት አንድ ሶስተኛውን የምታገኘው ከአፍሪቃ ነው።ከአፍሪቃም ለቻይና በብዛት ነዳጅ ዘይት የምታቀርበው አንጎላ የአሁኑ የዌን ጉዞ ትኩረት ናት እየተባለ ነው።ከሰሀራ በታች ከሚገኙ ሀገራት ከናይጀሪያ ቀጥሎ በነዳጅ ዘይት ምርትዋ ሁለተኛውን ደረጃ የምትይዘው አንጎላ በመጋቢት ወር ወደ ሁለት ነጥብ ስድስት አንድ ሚሊዮን ቶን ድፍድፍ ዘይት ነበር ወደ ቻይና የላከችው። ቻይናም በአንጎላ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታዎች ስራ ላይ ተሰማርታለች።ከአራት ዓመት በፊት ከርስ በርስ ጦርነት ለተላቀቀችው ለአንጎላ ቻይና የሁለት ቢሊዮን ዶላር ብድር ሰጥታለች።አንድ የቻይና የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ኩባንያም በሶስት የአንጎላ የነዳጅ ዘይት ፍለጋ ስራዎች ውስጥ በዚህ ሳምንት አክስዮን መግዛቱም ተመልክቶዋል።ይሁንና የቻይና ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂ እና አንዳንድ ቻይናውያን ታዛቢዎች እንደሚሉት የአሁኑ የዌን ጉዞ ትኩረት ነዳጅና አንጎላ ብቻ አይደለም።የቻይና የአፍሪቃ የንግድ ዕንቅስቃሴ ምክርቤት ቃል አቀባይ ቹ ሹን ቻንግ እንዳስታወቁት ቻይና ከዚህ በተጨማሪም ከአፍሪቃውያን ጋር የምትጋራቸው ጥቅሞች አሉ።እንደ ሹንቻንግ የአሁኑ የዌን ጉብኝትም የቻይና ድርጅቶች አፍሪቃ ያሉትን የስራ ዕድሎች የበለጠ ለመረዳት ሁኔታዎችን የሚያመቻችም ነው።በዚሀ አጋጣሚም አፍሪቃውያን ቀደም ባሉት ዓመታት ድሀ ከነበረችው አሁን ደግሞ በኢኮኖሚ ከበለፀገችው ከቻይና ዕድገት መማር ይችላሉ ብለዋል የቻይና የአፍሪቃ ጥናት ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዛንግ ያንግ። አፍሪቃውያኑም ከቻይና ጋራ ለመተባበር ፈቃደኛ ናቸው።ቻይና ዕንዴት እንደዳደገች ማወቅ ይፈልጋሉና