1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቻይና፤ ስልታዊና የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 2 1998

ሕዝባዊት ቻይና ስልታዊ ለሆነ የብልጽግና ግብ የምታደርገው የኤኮኖሚ ዕርምጃ በፍጥነቱ በተለይ በዚህ የምጣኔ-ሐብት ዕድገቱ ከዓመት ወደ ዓመት በመቆርቆዝ፤ ወይም ባለበት በመራመድ ላይ በሚገኘው በምዕራቡ ዓለም የማይታሰብ ነው። የቻይና ዕርምጃ እንዴት፤ ከየት፣ ወዴት? መሥፍን መኮንን!

https://p.dw.com/p/E0dY
ወደ ቲቤት የሚያመራ የባቡር ሃዲድ ድልድይ
ወደ ቲቤት የሚያመራ የባቡር ሃዲድ ድልድይምስል AP

በዓለም ላይ በሕዝብ ብዛቷ ቀደምት የሆነችው ቻይና ዛሬ ብልህነትና ቁርጠኝነት በተመላው መንፈስ ተጽዕኖዋን በማስፋፋት ላይ ነው የምትገኘው። ቤይጂንግ በአሁኑ ጊዜ የምዕራቡን ዓለም ገበዮች በምርቶቿ ከማጥለቅለቋ ባሻገር በኢንዶ-ቻይና አካባቢ የያዘችው የሃያል መንግሥትነት የኤኮኖሚ ሚናም በደቡብ-ምሥራቅ እሢያ ቀደምቱን ምዕራባውያን መንግሥታት አሜሪካን፣ አውሮፓንና ጃፓንንም ሣይቀር ቀስ በቀስ መሠረት እያሳጣ ነው። አቅጣጫና ግቧም ይሄው ከበለጸጉት ቀደምት መንግሥታት የመስተካከል የምጣኔ-ሐብት ልዕልናን ማረጋገጥ መሆኑ የተሰወረ አይደለም።

ሕዝባዊት ቻይና ዛሬ በያዘችው የተፋጠነ የምጣኔ-ሐብት ዕርምጃ ባለፉት ጊዜያት እስከ አሥር በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ስታደርግ ነው የቆየችው። የኤኮኖሚ ዕድገታቸው በአንድና ቢበዛ ሁለት በመቶ እንኳ በማይሞላ ተጎታች ዝግመት ላይ የሚገኘው ምዕራባውያን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት የቻይናን ዕርምጃ ሊከተኩት ቀርቶ ሊያልሙት እንኳ የሚችሉ ሆነው አይገኙም።

በምጣኔ-ሐብት ሃያልነት ላይ ላለመው የቻይና ግብ አንቀሳቃሽ መንኮራኩር ሆኖ የሚገኘው አገሪቱ ከማንኛውም የውጭ ተጽዕኖ ለመላቀቅና ብልጽግናን ለማስፈን የምትችለው ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ላይ ስትደርስ ብቻ መሆኑን ጽኑ ግንዛቤ ማድረጓ ነው። ጃፓን እንደምን ሰለጠነች? አንዴ የዓለም መነጋገሪያ ተዓምር ነበር። ዛሬ የቻይናም ዕርምጃ በዚያው መጠን ማስደነቅ የያዘ ጉዳይ ነው።

ደቡብ-ምሥራቅ እሢያይቱ ግዙፍ አገር ዛሬ ከተኛችበት ተነስታ የምታካሂደው ፈጣን ዕርምጃ ማንም የማያቆመው፤ ራሷም ተመልሳ የማትገታው እየሆነ ሲያስገመግም ነው የሚገኘው። በወቅቱ ከደረስንበት ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ሁኔታ አንጻር ለቻይና ዕርምጃ በአገሪቱ ከተሰረጸው ሃያል የመሆን ዕምነትና ፍላጎት ባሻገር ተጨባጭ ምክንያቶች ሆነው የሚገኙት ከበለጸገው ዓለም ሲነጻጸር የሠርቶ-አደሩ ደሞዝና የአመራረቱ ዋጋ ዝቅተኛነት፤ እንዲሁም የዓለምን ገበያ ያጥለቀለቀው ምርቷ ርካሽነትም ናቸው።

ዛሬ የተለያዩ የቻይና የኢንዱስትሪ ምርቶች ያልገቡበት አካባቢ በዓለም ላይ ተፈልጎ አይገኝም። በጨቅላ ዕድሜ ላይ የሚገኘው የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪዋም ምናልባት እንደ ጃፓን የዓለም ገበዮችን የሚያጨናንቅበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። በነገራችን ላይ የቻይና የውጭ ንግድ ትርፍ ባለፉት ዓመታት አቻ ባልተገኘለት ሁኔታ እየናረ ሲሄድ ነው የታየው። ይህ ደግሞ ብሄራዊውን የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ በማጠናከር ድህነትን በመቀነሱ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ቻይና እንደ ታዳጊ አገር የምትታይ እንደመኗ መጠን የተባበሩት መንግሥታትን ድህነትን የመቀነስ የሚሌኒየም ዕቅድ ማሳካት ይዘዋል ከሚባሉት ጥቂት አገሮች መካከል ዛሬ አንዷ ናት።

እርግጥ የኤነርጂና የጥሬው ምርት ፍላጎት እየተፋጠነ ከመጣው ዕርምጃ ጋር ተጣጥሞ ሊራመድ አለመቻሉ ለጊዜውም ቢሆን በኤኮኖሚው የዕድገት ሂደት ላይ ገቺ መሰናክል እንዳይሆን ማስጋቱ አልቀረም። ይሁንና የአገሪቱ ባለሥልጣናት ካለሙለት ዘላቂ ግብ ወደ ኋላ እንዲሉ ጨርሶ የሚገፋፋ አልሆነም። ምርጫው አንድ፤ መንገዱም አንድ ነው። ቻይና በመጪዎቹ ጥቂት አሠርተ-ዓመታት በዓለም ላይ በኤኮኖሚ ዕድገት የበለጸገች ሃያል መንግሥት ለመሆን የያዘችው ጉዞ ላንዳፍታ እንኳ የሚያጠያይቅ አይደለም።

ይህ ለመሆኑ ለምሳሌ አገሪቱ በትዕግሥትና በቁርጠኝነት ውስጥ-ውስጡን የደቡብ-ምሥራቅና ማዕከላዊ እሢያን አካባቢ ኤኮኖሚ፤ በአፍሪቃም ነዳጅ ዘይትን የመሳሰለ የጥሬ ሃብት ለመቆጣጠር የያዘችው ጥረት አንድ ምሥክር ነው። ሕዝባዊት ቻይና ዛሬ ከኢንዶ-ቻይና እስከ ማዕከላዊው እሢያ የምታራምደው በወዳጅነትና በትብብር መንፈስ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ የአካባቢውን አገሮች ድጋፍ እያገኘ፤ እየተስፋፋ የሚሄድ ጉዳይም ሆኗል።

የኢንዶ-ቻይናው ጦርነት ጥሎት ያለፈው አሻራ ገና ጨርሶ ባይወገድም በላኦስ፣ በካምቦጃ፤ በበርማና በተለይም በቪየትናም ዕድገትና ብልዕግና ቀስ በቀስ ማንሰራራት ይዟል። አብዛኛው ጸጋ ወደአካባቢው የሚዘልቀውም ከበስተሰሜን ከሕዝባዊት ቻይና ነው። በርካታ የቻይና ነጋዴዎች ዛሬ በሜኮንግ ወንዝ ዳርቻ ላይ በምትገኘው የላኦስ ዋና ከተማ ጭምር በአካባቢው ሰፍረዋል። ሕንጻ ተቋራጮቹ፤ ከቴሌቪዥን አንስቶ እስከ ሞተር ቢስክሌት ምርት አቅራቢና ጠጋኞቹ፤ አውራ-ጉዳና ዘርጊዎቹም ሆኑ ግድብ ሠሪዎቹ ቻይናውያን ናቸው። በቻይና ዕርዳታ የሚቋቋሙት “Joint Venture” የጋርዮሽ ይዞታ ፋብሪካዎችም ጥቂቶች አይደሉም።

የንግዱን ዘርፍ ከተመለከትን የቻይና ምርቶች ዋጋ ርካሽ መሆን በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ ያደርጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል በቻይና የሚመረት አንድ ሞተር-ቢስክሌት ወይም ኩርኩር 200 ኤውሮ ገደማ ቢያወጣ ነው። ማነጻጸር ከተፈለገ ተመሳሳይ የጃፓን ምርት እጥፍ ዋጋን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ለአካባቢው ነዋሪ ከአቅም በላይ ነው፤ የሚቀመስ አይደለም።

ሕዝባዊት ቻይና ላኦስን፣ ካምቦጃንና ቪየትናም የመሳሰሉትን አገሮች ይህ ነው በማይባል ፍጥነት በኤኮኖሚና በፖለቲካ ግንኙነት ይበልጥ ከራሷ ጋር እያስተሳሰረች መሄድ ከያዘች ሰንበት ብላለች። በተለያዩ የቻይና የወሰን ዳርቾች አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል ለማለት ይቻላል። የዕድገቱ ታሪኩ የሚጻፈው ደግም ቤይጂንግ ውስጥ ነው። ቻይና ግቧን በተመለከተ ጠንካራ፤ በመስፋፋት ዘዴዋ ግን ተጨባጭ ሃቅን ያገናዘበች ሆና በደቡብ-ምሥራቅ እሢያ አካባቢ ተጽዕኖዋን ማጠንከሯ አሜሪካንና ጃፓንን ቀስ በቀስ ዋጋ የሚያሳጣ ሆኗል።

አሜሪካ በበኩሏ በእሢያ-ፓሢፊክ አካባቢ ግዙፍ ገበያ ለማስፈን የአካባቢውን መንግሥታት የኤኮኖሚ ሕብረት በአሕጽሮት አፔክን ለመፍጠር ራዕይዋን ላለፉት 17 ዓመታት ስታራምድ ነው የቆየችው። 21 መንግሥታትን የያዘው ይሄው ስብስብ ቻይናና ታይዋን፤ እንዲሁም ካናዳ፣ ቺሌና ሩሢያም የሚገኘት ሲሆን በአብዛኛው ቅራኔ የተጣባው መሆኑ በያጋጣሚው ታይቷል። አፔክን ከራሷ ጥቅም አንጻር አሰባስባ የያዘችው አሜሪካ ደግሞ እስካሁን የእሢያ አገሮች በገበዮቿ ላይ ያለባቸውን ጥገኝነት መሣሪያ አድርጋ መጠቀሟ አልቀረም።

ሆኖም ግን ቻይና የዋሺንግተንን ጥረት እያከበደች ስትሄድ ነው የሚታየው። ቤይጂንግ ሌላው ቀርቶ አሜሪካን በጃፓንና በደቡብ ኮሪያ ሣይቀር በመፈንቀል ዋነኛዋ የንግድ ሸሪክ ለመሆን በቅታለች። በአካባቢው ታይላንድ ከ 2001 እስከ 2003 ዓ.ም. ለቻይና የሸጠችው ምርት ወደ 90 በመቶ፤ ከሞላ-ጎደል በእጥፍ ሲያድግ በዚሁ ጊዜ ቻይና በአንጻሩ ያቀረበችው ምርትና የሰጠችው አገልግሎትም በ 50 በመቶ በላይ ከፍ ማለቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህም የእሢያ መንግሥታት ከዋሺንግተን ገሸሽ እያሉ በቻይና ላይ ማተኮር መያዛቸውን የሚያመለክት ነው።

ለነገሩ ምዕራባውያን ባለካፒታሎች የምንዛሪውን ውድቀት ባባባሱበትና ንብረታቸውን ባሸሹበት በእሢያው የ 1997 የኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት አካባቢው በምዕራቡ ዓለም፤ በተለይም በአሜሪካ ላይ ጥርሱን ነበር የነከሰው። በጊዜው የማሌይዚያው ጠቅላይ ሚኒስትር ማሃቲር ሞሐመድ ድርጊቱን ዓድማ ሲሉ ብዙዎች በልባቸው ያሰቡትን ነበር የተናገሩት።

ቻይና በአንጻሩ በእሢያው ቀውስ ወቅት እንደ አሜሪካ ሣይሆን በችግር ሰዓት ፈጥኖ ደራሽ ወዳጅ በመሆን ታማኝነትና ታቃፊነቷን ልታጠናክር በቅታለች። እሢያ ዛሬ በአጠቃላይ ማንም በማይገታው ፍጥነት እያደገች ሲሆን ሕዝባዊት ቻይናም በአካባቢው የምታልምለትን ግብ፤ የሃያል መንግሥትነቱን ሚና እየጨበጠች ነው የምትታየው። የቻይና የግንቢያ ሠራተኞች በ 2007 ዓ.ም. ተጥናቆ የደቡባዊቱን አባቢ ክፍለ-ሐገር የዩናንን ዋና ከተማ ኩንሚንግን ኢንዶ-ቻይናን አቋርጦ ከታይላንድ ርዕሰ-ከተማ ባንግኮግ የሚያገናኝ ርዝመቱ ሁለት ሺህ ኪሎሜትር የሆነ ፈጣን አውራ ጎዳና ለማነጽ በወቅቱ በአካባቢው አፈር-ድንጋይ እየገለበጡ ነው።

ወጪውን የምትሸፍነው ቤይጂንግ ስትሆን ቻይና ጎረቤቶቿ ላኦስ፣ በርማና ቪየትናም በመንገዶች፣ በባቡር ሃዲዶች፣ በኤሌክትሪክ መረብ ዝርጋታና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አዲስ የኤኮኖሚ ክልል ሆነው እንዲያብቡ ለማድረግ ካላት ሰፊ ውጥን አንዱ ነው። ቤይጂን የአካባቢው አገሮች የብልጽግናው ባለድርሻዎች እንዲሆኑ በማድረግ በአዋሣኝ ክፍለ-ሐገሮቿ ድህነትን ለመቀነስ፣ ለኢንዱስትሪ ምርቶቿም አዳዲስ ገበዮች መፈጠራችውን እንደምትሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ ከዓመት ገደማ በፊት ያስረዱት ጉዳይ ነበር።

እርግጥ የብልጽግና ተካፋይነቱ ማራኪ ቢሆንም የቻይና የተፈጥሮ ሐብት ጥም ጎረቤቶቿን ጥቂትም ቢሆን ማሳሰቡ አልቀረም። ቤይጂንግ ለምሳሌ ከሕንድ ውቂያኖስ በርማን አቋርጦ ቾንግኪንግ ወደተሰኘች ከተማዋ የሚዘልቅ የነዳጅ ዘይት ቧምቧ የመዘርጋት ውጥን አላት። በወቅቱ በርማ ውስጥ አንድ ታላቅ ግድብ የምታንጸውም ምናልባት ለዚሁ በማካካሻነት ሣይሆን አልቀረም። የቧምቧው ግንቢያ ዓላማ በማላካ የባሕር መንገድ የሚያልፈውን ውድ የሆነና ለወታደራዊ ጥቃት የተጋለጠ የመርከብ ትራንስፖርት መተካት መሆኑ ይታመናል። በተለይ ከአሜሪካ ጋር ያላት ሽኩቻ የኤነርጂ አቅርቦቷን እንድታረጋግጥ ግፊት ያሳደረባት ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።
ቤይጂንግ ዛሬ የኤነርጂ ጥሟን ለማርካት በያዘችው ቁርጠኛ ፖሊሲ በአፍሪቃም ተጽዕኖዋን እያጠናከረችና ለምዕራቡ ዓለም ብርቱ ተፎካካሪ እየሆነች መሄዷ ይታወቃል። በሱዳን ነዳጅ ዘይት የምታወጣው ቻይና ናት። ከሌሎች ነዳጅን ጨምሮ የተለያየ የተፈጥሮ ሃብት ካላቸው የአፍሪቃ መንግሥታት ጋር የወዳጅነትና የትብብር ውል በመፈራረምም ምዕራቡን ዓለም ቀስ በቀስ ከክፍለ-ዓለሚቱ የኤኮኖሚ መድረክ እየፈነቀለች ነው። የአፍሪቃ ፖሊሲዋ ስልታዊነትና ዘላቂነት አለው። ግንባታም ሆነ ሌላ ተግባራትን በርካሽ ዋጋና ያለብዙ ቅድመ ግዴታ የምታከናውን መሆኗም ይበልጥ ተቀባይነት እያስገኘላት መሄዱ አልቀረም።


በአጠቃላይ የቻይና የኤኮኖሚ ግፊት በማዕከላዊው እሢያ የቀድሞ ሶቪየት ሬፑብሊኮች ሣይቀር ሥር መስደድ የያዘ ጉዳይ ነው። በዚህም አካባቢ የቻይና ምርቶች በሰፊው ይራገፋሉ። አካባቢው ሰፊ ምርት ተቀባይ፤ መጪው ገበያ መሆኑን ደግሞ የተረዱት ምዕራባውያን የበለጸጉ መንግሥታት ብቻ አይደሉም። ቻይና የምትከተለው ስልታዊ የኤኮኖሚ ፖሊሲ፤ የርካሽ ምርትና የአገልግሎት አቅርቦቷ በአማካይና በረጅም ጊዜ ቀዳሚና ተመራጭ የሚያደርጋት ነው። ቻይና ከየት ወዴት? የኤኮኖሚ ዕርምጃዋ ቀጣይ፤ ግቡም የሚደረሰት መሆኑ ብዙም አያከራክርም። ጥያቄው ቆርጣ የተነሣችለት ብልጽግናና ልዕልና መቼ ዕውን ይሆናል ነው።