1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናይሮቢ፥ የምክር ቤት አባልና አጃቢዎች ተገደሉ

ቅዳሜ፣ ጥር 30 2007

ኬንያ መዲና ናይሮቢ ውስጥ ጭምብል ያጠለቁ ታጣቂዎች የሀገሪቱ አንድ የምክር ቤት አባልን ቅዳሜ፤ ጥር 30 ቀን፣ 2007 ዓም አውራ ጎዳና ላይ ተኩሰው በመግደል መሸሻቸው ተገለጠ።

https://p.dw.com/p/1EXlH
Nairobi Kenia Abgeordnete Parlament Debatte Sicherheitsgesetz 18.12.2014
ምስል picture-alliance/AP Photo/Ben Curtis

በተኩስ ሩምታው የኬንያ የምክር ቤት አባል የሆኑት ጂዮርጅ ሙቻይ እና ኹለት የግል ጠባቂያቸው እንዲሁም የመኪና አሽከርካሪያቸው መገደላቸውን የናይሮቢ ፖሊስ እዝ ኃላፊ ፓውል ዋንጃማ አስታውቃዋል። ባለሥልጣኑ እና አብረዋቸው የነበሩት ሦስቱ ሰዎች የተገደሉት ከአንድ ሸቀጥ መደብር ጋዜጣ ለመሸመት መኪናቸውን ባቆሙበት ቅጽበት እንደነበረም ተጠቅሷል። የሟቹ ባለስልጣን ልጆች እና ቤተሰቦች በሌላ ተሽከርካሪ ከኋላ ይከተሉ እንደነበረም ተዘግቧል። አራቱ ሰዎች የተገደሉት ደረታቸው እና ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተደብድበው ነው ተብሏል። የኬንያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ «ኬንያ እየደማች ነው፤ ፍርኃት እና ተስፋቢስነት በሀገሪቱ እየተዛመተ መጥቷል» ብለዋል። ኬንያ በሶማሊያ ወታደሮች ማሰማራቷን ተከትሎ የሶማሊያን መንግስት የሚወጉት ታጣቂዎች የበቀል ጥቃት ለመሰንዘር መዛታቸው ይታወሳል። ግድያውን ተከትሎ በኬንያ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት መከተሉም ተጠቅሷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ