1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናይጀሪያ፣ ቦኮ ሀራም እና የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 2 2006

ናይጀሪያ መዲና አቡጃ ካለፈው ረቡዕ እስከ ትናንት ድረስ በተካሄደው ያካባቢው የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ላይ የተሳተፉት እንግዶች በሀገሪቱ አክራሪው የሙሥሊሞች ቡድን ቦኮ ሀራም ባስፋፋው ሽብር እና በፀጥታ አጠባበቁን አስተማማኝ ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መወያየት ግድ ነበር የሆነባቸው።

https://p.dw.com/p/1BxKP
ምስል Reuters

በዚህም የተነሳ የጉባዔው አጀንዳ ሊያስተላልፈው የነበረው አህጉሩ በኤኮኖሚው ዘርፍ የሚታየው ብሩሁ የአህጉሩ የወደፊት ዕድል እንደተፈለገው ሳይጎላ ቀርቶዋል።

በሰሜን ምሥራቃዊ ናይጀሪያ በቦርኖ ግዛት አቅራቢያ በሚገኘው ቺቦክ አክራሪው የሙሥሊሞች ቡድን ቦኮ ሀራም 276 ልጃገረዶችን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከአንድ ትምህርት ቤት ያገተበት እና በዚያ በሰነዘረቸው ጥቃቶች በርካቶችን የገደለበት ድርጊት የአሸባሪው ቡድን ጥቃት ሰለባዎችን በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በተከፈተው ባካባቢው የዓለም ኤኮኖሚ ጉባዔ ላይ ጥላ አጥሎበታል።

Weltwirtschaftsforum in Abuja (Nigeria)
ምስል Pius Utomi Ekpei/AFP/Getty Images

ምንም እንኳን ባለፉት ቀናት የዓለም መገናኛ ብዙኃን ቦኮ ሀራም በናይጀሪያ ስላስፋፋው ሽብር አዘውትረው ቢዘግቡም ከአፍሪቃ እና ከሌሎች አህጉራት የተውጣጡ ወደ 1000 የሚሆኑ ልዑካን ወደ አቡጃው ጉባዔ መሄዳቸው አበረታቺ እንደነበር የዚሁ የውይይት መድረክ መሥራች የሆኑት ክላውስ ሽቫብ ገልጸዋል። የናይጀሪያ ፕሬዚደንት ጉድላክ ጆናታንም በበኩላቸው የጉባዔው ተሳታፊዎች ሽብር ሳያስፈራቸው በጉባዔው መካፈላቸው መንግሥታቸው በሽብርተኝነት አንፃር ለጀመረው ትግሉ ትልቅ ድጋፍ መሆኑን አመልክተዋል። በምዕራብ አፍሪቃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሽብር አንፃር መቆሙን የሚያሳይ ግልጽ ምልክት መሆኑን የአፍሪቃ የልማት ባንክ ፕሬዚደንት ዶናልድ ካቤሩካ አስረድተዋል።

« በአሁኑ ጊዜ ወደ ናይጀሪያ መምጣታችን ሽብርተኝነት እንደማያሸንፍ ግልጸ መልዕክት ያስተላ,ለፈ ርምጃ ነው። ልጃገረዶቹ የታገቱበትን ድርጊት በተመለከተም ፣ ዕገታው ሽብርተኝነት መሆኑን እና የልጃገረዶች የትምህርት መብትንም ጭምር የሚገፍም መሆኑን ሁለት ግልጽ መልዕክት ለማስተላለፍ ዕድል ሰጥቶዋል። »

Demonstration Freilassung Boko Haram Entführung Schülerinnen Nigeria
ምስል DW/H. Fischer

ይሁን እንጂ፣ ይህ ከናይጀሪያ ጋ የታየው ትብብር ሁሉ የመድረኩ አዘጋጂዎች ጉባዔውን በናይጀሪያ እንዲካሄድ ሲወሰን በመጀመሪያ ያስቀመጡት ዓላማቸው ፣ ማለትም፣ አፍሪቃን ወደፊት የሚጠብቁዋትን ብዙ ተግዳሮቶችን ለማሸነፍ ዝግጁ የሆነች የመጪው ዘመን ባለተስፋ ክፍለ ዓለም መሆኗን ለማጉላት የነበራቸው ዕቅድ እንዳሳቡት ማዕከላዩን ትኩረት ሳያገኝ ነበር የቀረው። ይህ ግን አፍሪቃ እአአ በ1990 ዎቹ ዓመታት በአህጉሩ ብዙ ሀገራት እና ሕዝቦች በጦርነት ይሰቃዙ የነበረበት አሳሳቢ ችግር ላይ ትገኛለች ማለት አለመሆን ነው ካቤሩካ ያስታወቁት። ታታሪ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አመለካከት ያተረፉት የናይጀሪያ ገንዘብ ሚንስትር ንኮዚ ኦኮንጆ ኢዌላም ባለሀብቶች በጊዚያዊ ሽብርተኝነት ተደናግጠው ወረት ከማሰራት ወደኋላ እንደማይሉ አስረድተዋል።

« እርግጥ የፀጥታ ጉዳይ ስጋት መደቀኑ እና ልማትንም ሊያደናቅፍ መቻሉ የሚታወቅ ነው። ይህንን መቀበል አለብን። ይሁንና፣ እዚህ ወረት ካፈሰሱ ወገኖች ጋ ካደረግሁት ውይይት እንደተገነዘብኩት ወራቾቹ በአህጉሩ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚፈልጉ ይመስለኛል። ይህ አስገራሚ ክስተት ሆኖ አግንቼዋለሁ። አህጉሩን እንደ ባለ ተስፋ ነው የተመለከቱት። ያጭሩን ጊዜ ስጋት ብቻ ሳይሆን አህጉሩ የመጪው ዘመን ባለተስፋ ክፍለ ዓለም መሆኑን አስምረውበታል። ብዙዎቹ ወደ አህጉሩ የሚመጡት ለረጅም ጊዜ ለመቆየት መሆኑን ነው የገለጹት። »

Schweiz Weltwirtschaftsforum in Davos Ngozi Okonjo-Iweala aus Nigeria
ምስል dapd

ከአህጉሩ ውጭ ስለአፍሪቃ ባለው አመለካከት እና በአህጉሩ እየታየ ባለው ሂደት መካከል ያለው ልዩነት ግዙፍ መሆኑንም አሜሪካዊው ባለወረት ቦብ ዳይመንድ አመልክተው፣ ጥያቄው መሆን ያለበት ወረት ወዳፍሪቃ መሳብ የሚለው ሳይሆን ፣ የአፍሪቃ የባንኩ ዘርፍ ራሱን ለንዑሳኑ እና ለመካከለኛው ተቋማት ክፍት ማድረግ ይገባዋል የሚሰኘው መሆኑን አስረድተዋል።

በዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃን በመጀመሪያ ደረጃ የሚታየው የአፍሪቃ ገፅታ አሉታዊ መሆኑ ትክክለኛውን የአህጉሩን ገፅታ እንደማያመለክት ናይጀሪያዊው የመገናኛ ብዙኃን አማካሪ ቢዮላ አላቢ አስታውቀዋል። ቦኮ ሀራም ስላስፋፋው ሽብር፣ ስለታገቱት ልጃገረዶች፣ ብቻ ሳይሆን በአፍሪቃ ስለሚታየው አዎንታዊ እንቅስቃሴ መንገር ፣ እንዲሁም፣ ሕዝቡ ስር ስለሰደደው ሙስና ለማሳወቅ እያደረገ ያለውን ማሳወቅ የአፍሪቃውያኑ ፈንታ መሆኑን አላቢ አክለው ያስረዱት።

« አሁን የምንኖርበት ዓለም ሐቁን መደበቅ የማንችልበት ዓለም ውስጥ ነው። ሐቁ የሚታይ ነው፣ ግልጽነት አለ። በመሆኑም፣ በናይጀሪያ እና አፍሪቃ ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች ጠለቅ ያለ ምርምር በማድረግ ጥሩ ስራ ለሚያቀርቡበት ጥረታቸው ሊመሠገኑ ይገባል። ሰሞኑን እያነበብን ያለነው ደግሞ ዜጎችም እንዴት ዘገባዎችን እንደሚያቀርቡ ነው። »

በአቡጃ በተካሄደው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ላይ የተካሄደው ውይይት በአፍሪቃ ከሚታየው የፀጥታ ስጋት ጎን በአፍሪቃ እና በቻይና መካከል እየተጠናከረ ስለመጣው ግንኙነትም ትኩረት ሰጥቶ በሰፊው መክሮዋል። በጉባዔው የተሳተፉት ብቸኛው አፍሪቃዊ ያልሆኑት የሀገር መሪ የቻይና ጠቅላይ ሚንስትር ሊ ኬኪያንግ አፍሪቃውያቱ ሀገራት መሠረተ ልማቱን ለማስፋፋት ለጀመሩት እና ለዘላቂ የልማት ሂደት ዋነኛ ቅድመ ግዴታ ለሆነው ጥረታቸው የቻይና ድጋፍ እንደማይለያቸው ቃል ገብተዋል። ፈጣን የባቡር መስመር እና የመንገዶች መረቦች ዝርጋታ፣ እንዲሁም፣ ተገቢ አገልግሎት የመስጠት አቅም የሚኖራቸው ያካባቢ አየሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ በቻይና ድጋፍ ውስጥ ተካተዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ሊ ኬኪያንግ ቻይና ለአፍሪቃ የምትሰጠውን ብድር በተጨባጭ ከ20 ወደ 30 ቢልየን ዩኤስ ዶላር፣ እንዲሁም፣ ለአፍሪቃ ልማት የመደበችውን ርዳታ ከሦስት ወደ አምስት ቢልየን ዩኤስ ዶላር ከፍ እንደምታደርገው በማመልከት፣ ሀገራቸው ለአፍሪቃ በምታደርገው ድጋፍ ላይ መቼም ቢሆን የፖለቲካ ቅድመ ግዴታ እንደማታሳርፍበት አረጋግጠዋል። አንዳንዶች ይኸው የአፍሪቃና የቻይና ግንኙነት አፍሪቃ በቻይና ላይ ጥገኛ የምትሆንበትን ክስተት ሊፈጥር ይችላል በሚል ያሰሙትን አስተሳሰብ ብዙዎቹ የአቡጃ ጉባዔ ተሳታፊዎች አጣጥለውታል። ናይጀሪያዊቷ የገንዘብ ሚንስትር ኦኮንጆ ኢዌላም አህጉሩ የሚያደርገው ማንኛውም ሽርክና በእኩልነት ላይ ለሚመሠረትበት እና የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም ለሚሆንበት ድርጊት ትኩረት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

Weltwirtschaftsforum in Abuja (Nigeria)
ምስል Pius Utomi Ekpei/AFP/Getty Images

« አፍሪቃ ብዙ ነገሮችን በሚገባ ማስተዋል የምትችል ይመስለኛል። በአሁኑ ጊዜ ከሁሉም አቅጣጫ ወረት ያስፈልገናል። እና ከተሻራኪዎቻችን ጋ በእኩልነት የምንተባበርበትን ሁኔታ የመፍጠሩን የቤታ ስራ ማከናወን የኛ ፈንታ ነው። ለምሳሌ የውጭ ሀገር ተቋማት ሰራተኞቻቸውን ከሀገራቸው ይዘው ሊመጡ አይችሉም፣ ምክንያቱም በዚሁ ረገድ ያወጣናቸው ሕጎች አሉና። ናይጀሪያ 170 ሚልዮን ሕዝብ የሚኖርባት ትልቅ ሀገር ናት። ብዙ ስራ የሌላቸው ዜጎችም አሉ። እና አንድ የውጭ ተቋም በናይጀሪያ ወረቱን ለማሰራት ሲፈልግ ይዞት መግባት የሚችለው የሰራተኛ ቁጥር የተወሰነበትን የሀገራችን ሕግ መከተል ይኖርበታል። አዎ፣ የሚፈለገው የሙያ ሥልጠና ያላቸው ሰዎች ወረቱን በሚያሰራበት ሀገር ውስጥ ካላገኘ፣ ሰራተኛውን ይዞ ሊመጣ ይችላል፤ ጉዳዩ ይህ ካልሆነ ግን ናይጀሪያውያንን መቅጠር ይኖርበታል። »

Chinesen bauen Straßen in Kenia
ምስል picture alliance/Photoshot

ይህ ቻይናውያኑን ባለተቋማትም የሚመለከት መሆኑን ያስረዱት ናይጀሪያዊቱ ገንዘብ ሚንስትር ቻይናውያን የአፍሪቃን ጥሬ አላባ በንግድ ወደ ሀገራቸው ማስገባት ብቻ ሳይሆን የሚፈልጉት፣ ከአህጉሩ ጋ ዘላቂ ግንኙነት መመሥረትም ጭምር ነው ብለዋል።

አፍሪቃ ፣ በተለይ ከሰሀራ በስተደቡብ የሚገኙት ሀገራት ባለፉት ዓመታት ያስመዘገቡት ከፍተኛው የኤኮኖሚ ዕድገት በአህጉሩ አዳዲስ የስራ ቦታ በመፍጠሩ ረገድ ያን ያህል ያበረከተው ድርሻ ያላበረከተበት ድርጊት በአቡጃው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ተሳታፊዎችን አሳስቦዋል። ይህንን ለመቀየር ሁነኛ ጥረት ሊነቃቃ ይገባል ከሚሉት ወገኖች መካከል በአፍሪቃ በሀብታምነታቸው የሚታወቁት ናይጀሪያዊው ባለ ተቋም አሊኮ ዳንጎቴ አንዱ ናቸው። አፍሪቃ ውስጥ የውጭ ባለሀብቶችን የሚስብ አማላይ የወረት ማንቀሳቀስ መርህ የለም በሚል አንዳንዶች የሚያቀርቡት ምክንያት የተሳሳተ እንደሆነ ዳንጎቴ በመግለጽ፣ የሚያስፈልገው የራሳችን ታታሪነት መሆኑን አስረድተዋል።

« በአሁኑ ጊዜ የገጠመን ትልቁ ተግዳሮት በአፍሪቃ የምንገኝ አንዳንዶቻችን ገንዘባችንን በአፍሪቃ በማሰራት ፈንታ በውጭ ሀገራት ባንኮች ማስቀመጡን የመረጥንበት ጉዳይ ነው። በዚሁ ተግባራችን ወራቾች በአህህጉሩ ላይ እምነት እንዳያድርባቸው እያደረግን ነው። ግን የውጭ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን በአፍሪቃ እንዲያሰሩ ከፈለግን እንደ አንድ አፍሪቃዊ ማድረግ ያለብን ራሳችን ገነዘናችንን በአህጉራቸን በማነቀሳቀስ እምነት መፍጠር ይሆናል። »

ቶማስ መሽ/አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ