1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኔቶ እና የሶርያ ጦርነት

ሐሙስ፣ መስከረም 27 2008

የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ኪዳን ፣ ኔቶ አባል በሶርያ እየተጠናከረ የመጣውን የሩስያ ጦር እንቅስቃሴ እንደሚገመግም የኪዳኑ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልትንቤርግ አስታወቁ።

https://p.dw.com/p/1GlG7
NATO-Verteidigungsminister in Brüssel
ምስል picture-alliance/dpa/O. Hoslet

ከአንድ ሳምንት በፊት በሶርያ በሚገኙት IS ይዞታዎች ላይ ጥቃት የጀመረችው ሩስያ በትናንቱ ዕለት ጥቃቷን በካስፒያን ባህር ከሚገኝ የጦር መርከቧ በተኮሰቻቸው ተምዘግዛጊ ሚሳይሎች ማጠናከሯ እንዳሳሰባቸው ስቶልትንበርግ በመግለጽ ኪዳኑ አባላቱን እንደሚከላከል አስታውቀዋል። እንደሚታወሰው፣ የሩስያ ተዋጊ አይሮፕላኖች የኔቶ አባል የሆነችውን ቱርክ አየር ክልል ጥሰዋል ሲል ኪዳኑ በተደጋጋሚ ተቃውሞውን አሰምቶዋል። ምዕራባውያን መንግሥታት የሩስያ ጥቃት በIS ይዞታዎች ላይ ብቻ ሳይሆን የIS ተቀናቃኝ በሆኑ ዩኤስ አሜሪካ እና አጋሮቿ የሚደገፏቸው ደፈጣ ተዋጊዎች በያዙዋቸው አካባቢዎችም ላይ ነው በሚል ሩስያን ወቅሰዋል። ሞስኮ የሶርያን ፕሬዚደንት በሺር ኤል አሳድን መደገፏን እንድታቆም እና በሶርያ ያየር ጥቃት ከቀጠለችው ዩኤስ አሜሪካ ጋር እንድታስተባብር አሳስበዋል። ሞስኮ የምዕራባውያኑን ወቀሳ ሀሰት ስትል አስተባብላለች። ፕሬዚደንት ፑቲንም የሃገራቸውን የጦር እንቅስቃሴ ከዩኤስ አሜሪካ ጋር የማስተባበር እቅድ እንደሌላቸው ገልጸዋል።

Russland, Kampfflugzeug MiG-35
ምስል picture-alliance/dpa/S. Chirikov

« አሜሪካውያኑ ፣ ምንም እንኳን ሕገ ወጥ ቢሆንም፣ በሶርያ ያየር ጥቃት ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በላይ በመሆኑ፣ በዚያ ስላለው ሁኔታ የተሻለ እውቀት አለን ካሉ፣ ዒላማዎቹን ይስጡን፣ እናጠቃቸዋል።»

የዩኤስ አሜሪካ መከላከያ ሚንስትር አሽ ካርተር የሩስያ ጥቃት የተሳሰተ ሲሉ ወቀሳቸውን በድጋሚ አሰምተዋል።

« የ«አይስል» ያልሆኑ ዒላማዎችን መደብደባቸውን ቀጥለዋል። ይህ መሰረታዊ ስህተት ነው ብለን እናምናለን። ሩስያውያኑ የፈለጉትን ቢሉ፣ የተሳሰተ ስልት በመከተል እነዚህን ዒላማዎች መምታታቸውን እስከቀጠሉ ድረስ፣ እኛ ከነርሱ ጋር ለመተባበር አልተስማማንም። »

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የሶርያ ጦር በታጣቂ ተቃዋሚ ቡድኖች አንፃር ግዙፍ ዘመቻ መጀመሩን ዛሬ አስታውቋል።

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ