1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኖቤል-የሰላም ሽልማት ሊዩና የቻይና ቁጣ

ሰኞ፣ ጥቅምት 1 2003

ለመብት የሚሟገት ሰዉ ነፃነቱን ማጣቱና ክትትል የሚደረግበት መሆኑ በሥራ ላይ እንደሚያጋጥም አደጋ የሚታይ ነዉ።ይሕ የሥራዉ አካል ነዉ።በሌሎቹ አይን አንተ እንደ ታላቅ ሰዉ ወይም እንደ ጀግና ትታይ ይሆናል።ይሁን እንጂ አንተ (በሌሎቹ ለመደነቅ ሳይሆን) ምግባርሕ የራስሕ ምርጫ መሆኑን በግልፅ መገንዘብ አለብሕ

https://p.dw.com/p/PbVe
ሊዩ

ተራ መምሕር እንጂ፣ ሚኻኤል ጎርቫቾቭን አልነበሩም-አይደሉምም።ጎርቫቾቭ ለሞስኮ ያለሙ-ያደረጉት ቤጂንግም እንዲደገም መመኘታቸዉ ግን አልቀረም።ጎርቫቾቭ ለዉለታቸዉ ዋጋ ኖቤል ሲሸለሙ ግን እሳቸዉ ለቤጂንግ የተመኙትን ቤጂንግ ላይ በመናገራቸዉ ተወንጅለዉ ወሕኒ ነበሩ።ከወሕኒ ሲወጡ አገቡ።ግን-ከጫጉላ ቤት እንደወጡ ተጋዙ።ከስራም ተባረሩ።እስራት፣ ግዞት፣ ሥራ አጥነት፣ አባወራነትም አልበገራቸዉም።እንደገና ተናገሩ-ፃፉም።እንደገና ታሰሩ።ጎርቫቾቭ ኖቤል መሸለማቸዉን እስር ቤት ሆነዉ በሰሙ በሃያኛዉ አመት ዘንድሮ-እንደታሰሩ ኖቤል ተሸለሙ።ሊዩ ሽኦቦ።የመሸለማቸዉ ምክንያት፥ የአሳሪ-ወንጃዮቻቸዉ ቁጣ ንረት-መነሻ፣ የፅናታቸዉ ጥልቀት-ማጣቀሻ፣ አስተምሕሮቱ መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
«የኖውዌዉ የኖቤል ኮሚቴ የ2010 ሩ የሰላም ኖቤል ሽልማት ቻይና ዉስጥ የሰብአዊ መብት እንዲከበር ለረጅ ጊዜ በሰላማዊ መንገድ ለታገሉት ለ-ሊዩ ሽኦቦ እንዲሰጥ ወስኗል።በነፃነትና በሰብአዊ መብት መከበር መካካል ጥብቅ ግንኙነት እንዳለ የኖቤል ኮሚቴዉ ማስታወቅ ይፈልጋል።
ማኦ ዜዱንግ የመሯቸዉ የቻይና ኮሚንስቶች የቤጅግ ቤተ-መንግሥትን ከተቆጣጠሩበት ከ1949 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎር ጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የሞስኮና የቤጂንግ ገዢዎች ላንድ ፍልስፍና ያደሩ፣ ላንድ አላማ የቆሙ፣ ለጋራ ፖለቲካዊ ርዕዮት-ስርፀት በጋራ የሚታገሉ መሆናቸዉን ያልተናገሩ፣ ያልፈከሩ፣ ያላስፈከሩበት ዘመን በርግጥ አልነበረም።ከነበረም ጥቂት ነበር።

የሁለቱ ሐገራት ገዢዎች በኮሪያዉ ልሳነ ምድር፣ በቬትናሙ ጦርነት፣ በአንዳድ የፍሪቃና የደቡብ አሜሪካ ዉጊያዎች የ-ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ የካፒታሊስቱ ዓለምን እርምጃና ተፅኖን በመፃረር በ«የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነዉ» ሥልት ባንድነት መቆማቸዉም እርግጥ ነዉ።ከዚሕ ባለፍ ግን ባንድነት-ላንድ አለማ ከመቆማቸዉ ይልቅ-የድንበር ግዛት ይገባኛል ዉዝግባቸዉ፥የርዕዮተ ዓለም አተረጓጎም ልዩነት፥ የደጋፊ ሽሚያ ሽኩቻቸዉ እንደደመቀ፥ኮሚንስታዊ ሥርዓታቸዉ ጨለመበት።

የአደባባይ-ቃል ፕሮፓጋንዳ፥ የጋራ ጠላት መርሕ በአንድነት ሥም የጀቦነዉ ልዩነት በአርባ አመቱ ፈጋ።1989።በኮሚንስቱ ሥርዓት ለዘመናት በተቀፈደደዉ ሕዝብ ስበት፥ በምዕራቡ አለም ግፊት አለምን እየነጣ የሚምዘገዘዉ የለዉጥ ማዕበል ሚኻኤል ጎርቫቾቭን ጨምሮ-ለዉጡን የጀመሩት ሐያላት ማዕበሉ እራሳቸዉን እንዳይደፍቃቸዉ እርምጃቸዉን ከፈጣኑ ለዉጥ ጋር ለማጣጣም ደፋ ቀና ይሉ ነበር።
የቦን መሪዎች ጀርመንን ለሁለት የገመሰዉን የበርሊንን ግንብ የሚያስንዱበትን ሥልት ገቢር ለማድረግ-ምሥራቅ አዉሮጳን ካጥለቀለቀዉ ፈጣን ሕዝባዊ አመፅ-ለዉጥ ጋር ሠልፋቸዉን ሲያሳምሩ፥ ከቤጂንግ ቤተ-መንግሥት ጋር እየተላተመ-ቻይና ዩኑቨርስቲዎች ዉስጥ የሚንተከተከዉ የለዉጥ ጥያቄ ታይናንሜን-አደባባይ ገነፈለ።ሚያዚያ ነበር።

Friedensnobelpreis für Menschenrechtler Liu Xiaobo Dossierbild 2/3
ሆንግኮንግ-ድጋፍምስል picture alliance/dpa

የቤጂንግ አደባባይ በተማሪዎች ጩኸት እንደደመቀ፥ የኢትዮጵያ ጄኔራሎች መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ አዲስ አበባ ዉስጥ እንደተጥመለመሉ፥ ጄኔራል ዑመር ሐሰን አል-በሸር የመሯቸዉ የሱዳን የጦር መኮንኖች ደም ሳያፈሱ-የሳዲቅ አል-መሒዲን ሲቢላዊ መንግሥት አስወግደዉ የካርቱምን ቤተ-መንግሥት ተቆጣጠሩ።ግንቦትም ተገባደደ።ኢትዮጵያ ለደም ምሷ ርካታ ከፊል ጄኔራሎችዋን ጭዳ-አድርጋ ሌሎቹን ወሕኒ አጉሯ የአዲስ አበባ ዩኒቨርቲ ተማሪዎችዋን ስታንጫጫ-ቤጂንግ በዩኒቨርቲ ተማሪዎችዋ ደም ጨቀየች።ሰኔም አራት አለ።ወሕኒ ቤቶቿ በለዉጥ ጠያቂ ተማሪ-ሙሕሮችዋ ተጨናነቁ።አንዱ እሱ ነበር።

«ብስክሌት እየነዳሁ ወደ ቤቴ-እየተጓዝኩ ነበር።እኩለ ሌት ግድም ነዉ።አንድ መኪና ይከተለኝ ነበር።ቤቴ አጠገብ ስደርስ መኪናዉ ከፊት ቆሞ-አስቆመኝ።ወዲያዉ የሆኑ ሰዎች ከመኪናዉ ወረዱና አይኖቼን በጨርቅ አሰሯቸዉ።አንጠልጥለዉ ከመኪናዉ ዉስጥ ወረወሩኝ።ሁኔታዉ በሙሉ አስፈሪ ነበር።በእዉነቱ ፈርቼ ነበር።ወዴት እንደሚወስዱኝ ምንም አይነት ፍንጭ አልነበረኝም።ሊገድሉኝ ካልሆነ በስተቀር ወዴት ይወስዱኛል ብዬም አሰብኩ።»

ሊዩ ሽኦቦ።የሰላሳ-አራት አመቱ የሥነ-ፅሁፍ መምሕር ሁለት አመት ታሠረ።ያስተምርበት ከነበረዉ ዩኒቨርቲ-ተባረረም።ግን እንደፈራዉ አልተገደለም።ፈራ ግን አላማ-ምግባሩን ወደደዉ።ሊያቋርጠዉ አልተቻላቸዉምም።

እንዲያዉም እሱ እንደ መምሕር እያበረታታ ለሰልፍ ካሳደማቸዉ ተማሪዎቹ የተወሰኑት በመገደል-መታሰራቸዉ ተጠያቂነኝ የሚል ስሜት ሰረፀበት።ግን ደማቸዉን በደም ሳይሆን በሕግ ሊበቀል እራሱ ለራሱ ቃል ገባ።ገዳዮቻቸዉን በሕግ ሊሞግት።
«በሰኔ አራቱ አመፅ ብዙ ንፁሐን ተገድለዋል።በሕይወት እንደተረፈ ሰዉ ለተገደሉት ሰዎች በፍርድ ቤት መሟገት አለብኝ የሚል እምነት አለኝ።ለሰዎቹ መገደል እኔ ላስወግደዉ ባልችልም በሆነ ደረጃ ተጠያቂነኝ የሚል ስሜት አለኝ።»

ወጣቱ መምሕር የሚደርስበትን በርግጠኝነት አያዉቀዉም።ግን አልተበገረም።የዲሞክራሲ፥ የሰብአዊመብት ክብር ፍቅር-ፍቅሯን የማረከባት ፍቅረኛዉ እንደ አደገኛ ሰዉ እያየች ገሸሽ-ገለል ታደርገዉ ገባች።ግን ደግሞ ከተክለ ሰዉነቱ ይልቅ አላማ ምግባር ፅናቱ የማረካት የድሮ-የትምሕርት ቤት ባልጀራዉ ፍቅረኛዋን ራቅ-ፈቀቅ እያደረገች እሱን ጠጋ ጠጋ ትለዉ ያዘች።ሊዩ ሺያ።

እሷ ራሷ የራቀችዉን፥ እሱ ራሷ ያራቀችዉን ፍቅረኞቻቸዉን እርግፍ አድርገዉ ትተዉ ተጋቡ።1996።ከእንግዲሕ ሁለቱም በምግባርም በእድሜም በትዳርም አንቱ ናቸዉ።አዲስ ፍቅር፥ አዲስ ሕይወት።በርግጥ ትዳር-ፍቅሩ እንጂ የሕይወቱ አዲስ እነት ዳር አልዘለቀም።ሊዩ የጫጉላ ሽርሽራቸዉን እንደጨረሱ ዳግም ትምሕር በጉልበት ሥራ የሚል የሰወስት አመት ቅጣት ተጥሎባቸዉ ወደ ሚሰሩበት ሠፈር ተጋዙ።

Liu Xia
የተሽላሚዉ ባለቤትምስል Mathias Bölinger

ተደጋጋሚ እስራት-ግዞት፥ እንግልት፥ ክትትል አደብ ገዘትተዉ እንዲቀመጡ ወይም ከሐገር እንዲወጡ መሆኑን አልዘነጉትም። በ1980ዎቹ ማብቂያ አላማ-ምግባራቸዉን ደግፈዉ የቆሙ ወይም ከሳቸዉ በፊት ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብት የታገሉ ወገኖቻቸዉ የደረሰባቸዉን-የደረሱበትንም ያዉቁታል።አብዛኞቹ ጥያቄ ተቃዉሟቸዉን እርግፍ አድርገዉ ትተዉታል።ጥቂቱ ተሰደዋል።ክብ-ፊቱ ባለ ትልቅ መነፅሩ-ሰዉዬ ግን እንቢኝ አሉ።ፅናቸዉ ለሩቁ ቻይናዊ አይደለም ለባለቤታቸዉም አጃኢቢ ነዉ።

«የእሱ አይነት አላማ የነበራቸዉ ብዙዎቹ ትተዉታል።የሽኦቦ ፅናት ግን የማይታመን ነዉ።ለአንድ አለማ ከቆመ አላማዉ ከግብ ሊደርስ እንደማይችል በትክክል እያወቀ እንኳን በጀመረዉ እስከመጨረሻዉ ይጓዛል።የተለየ እና የማይታመን ወኔ ያለዉ ሰዉ ነዉ።»

ከግዞት መልስ ቻይና ሐይማኖታዊ ችግር አርግዛ ስታምጥ ጠበቀቻቸዉ።የቻይና መንግሥት የሰይጣን ሐራጥቃ የሚሉትን የፉላን ጎንግ ሐይኖታዊ ሐራጥቃ ተከታዮች የሐገሪቱ ፀጥታ አስከባሪዎች እያደኑ ያስሩ ነበር።1999።ሰዎች የሚፈልጉትን ሐይማኖት በመከተላቸዉ ምክንያት መዋረድ፥ መታሰር መዋከባቸዉን ሊዩ እንደየትኛዉም የመብት ተሟጋች ሁሉ ተቃወሙት።

በ2001 «ፋሉን ጎንግን የመደፍለቁ መዘዝ» በሚል ርዕሥ ያሳተሙት መጣጥፍ ወትሮም ያልዘነጋቸዉን የሐገራቸዉን የሥለላ ተቋም ትኩረትን፥ የመንግሥታቸዉን ቁጣ ሲያብስ-ከተራዉ ወገናቸዉ በድብቅ ከዉጪ አለም በይፋ አደንቆቱ ይጎርፍላቸዉ ገባ።
በሁለት-ሺሕ ሰወስት የቻይና የብዕር ፀሐፍት የተሰኘዉ ቡድን መሪ ሆኑ።ቡድኑ የቻይናን ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ችግሮችን እያነሳ የተለያዩ ተቺ መጣጥፎችን ዉጪ ሐገር በሚዘጋጅ አምደ-መረብ አማካይነት የሚያሰራጭ ነዉ።
ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተዉ ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የሸለማቸዉም በአምደ መረብ የሚወጣዉን መጣጥፋቸዉን ይዘት ካጤነ በሕዋላ ነበር-2004።የድብቅ፥የይፋዉን አድናቆት ሽልማት እንደ ጥሩ ማበረታቻ ማየታት-መቀበላቸዉ አልቀረም።የአላማ ፅናታቸዉ መሠረት ግን በሁለት ሺሕ ሰባት እንዳሉት ፍላጎታቸዉ ብቻ ነዉ።

«ከዚሕ በፊትም ተናግሬዉ ነበር።ለመብት የሚሟገት ሰዉ ነፃነቱን ማጣቱና ክትትል የሚደረግበት መሆኑ በሥራ ላይ እንደሚያጋጥም አደጋ የሚታይ ነዉ።ይሕ የሥራዉ አካል ነዉ።በሌሎቹ አይን አንተ እንደ ታላቅ ሰዉ ወይም እንደ ጀግና ትታይ ይሆናል።ይሁን እንጂ አንተ (በሌሎቹ ለመደነቅ ሳይሆን) ምግባርሕ የራስሕ ምርጫ መሆኑን በግልፅ መገንዘብ አለብሕ።ነጋዴ አስተማሪ ወይም ሌላ ብዙ ገንዘብ የምታገኝበት ሥራ ልተሰራ እንደምትችልም ማሰብ አለብሕ።ከዉሳኔ ላይ ከደረስሕ ግን የሚገጥምሕንም ጫና እና መከራ በፅናት፥ በርጋታና በራስ መተማመን መንፈስ መቀበል አለብሕ።»

Anhänger von Friedennobelpreisträger Liu Xiaobo werden in Peking von der Polizei festgenommen
ቤጅንግ የሚገኙ የተሸላሚዉ ደጋፊዎች ታስሩምስል DW

ተቀበለዉ ቀጠሉበት። ቻርተር 08 ያሉትን የዲሞክራሲያዊ ለዉጥና የሰብአዊ መብት መከበር መጣጥፍ ሲያሳትሙ ታሰሩ።ቻርተሩን በመላዉ አለም የሚገኙ በሺሕ የሚቆጠሩ እዉቅ ሰወች ደግፈዉ ፈርመዉታል።እሳቸዉ ግን በታሰሩ ባመቱ አምና ታሕሳስ አስራ-አንድ አመት እስራት ተበየነባቸዉ።ባመቱ ዘንድሮ ኖቤል ተሸለሙ።

«ባለቤቴ ተፈቶ ይመጣልኛል ብዬ አስባለሁ።ሽልማቱ ተጨማሪ ሐላፊነት ማለትም ነዉ።የኖቤል ሽልማት እንደሚያገኝ እሱም ያስብ እንደነበር ጓደኞቹ ነግረዉኛል።ይሕ ማለት ቻይና ራስዋን ለመቀየር እድል አላት ማለት ነዉ።ቻይና ሰላማዊና ትርጉም ያለዉ ሽግግር ማድረግ ትችላለች።ሁሉም የሚጠብቀዉ ይሕንን ነዉ።ብዙ ሰዎች በሽልማቱ መበረታታቸዉን እየገለጡ ነዉ።ቻይና ዉስጥ እዉነተኛ ለዉጥ እንዲመጣ በሥራቸዉ በርትተዉ መጣር አለባቸዉ።»

ለቻይናን መንግሥት ግን ተቃራኒዉ ነዉ የታየዉ።የኖርዌዉ የኖቤል ኮሚቴ በወንጀለኝነት ለተፈረደበት ሰዉ ኖቤል መሸለሙን ቻይና እንደጥፋት ነዉ ያየችዉ።ሸላሚዉ ድርጅት ከየትኛዉም መንግሥት ተፅዕኖ ነፃ ሆነ በነፃነት መወሰኑን ቢያስታዉቅም ቻይና የምትቀበለዉ አይነት አይሆንም።የሊዩ መሽለም ከኖርዌ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደሚያበላሸዉም አስጠንቅቃለች።

በሽልማቱ እጅግ የተደሰቱት ወይዘሮ ሊዩ በወር አንዴ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር እየተጓዙ እስረኛ ባለቤታቸዉን ይጎበኙ ነበር።ከትናንት ጀምሮ ግን ታግደዋል።ከሉበት ሥፍራ ሳይስፈቅዱ እንዳይንቀሳቀሱ ተከልክለዋል።የቤት-ዉስጥ እስረኛ ሆነዋል።
በርካታ የሰብአዊ መብት ተቋማት፥ ድርጅቶች የተለያዩ ሐገራት መንግሥታት የቻይናን መንግሥት እርምጃ ተቃዉመዉታል።የሊዩን መሸለም ደግፈዉታል።ጀርመን ከቀደሚዎቹ አንዷ ናት።የሐገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ ሽቴፋን ዛይበርት።
የታናንሜኑ ሰልፍ-እርምጃ የአለምን ትኩረት ተቃዉሞ በሳበበት በ1989 የኖርውዌዉ ሽላሚ ኮሚቴ የቲቤቱን መንፈሳዊ መሪ ዳላይ ላማን መሸለሙ የቤጂንግ መሪዎችን ቁጣ፥ ዛቻ አስከትሎ ነበር።ሽልማቱም ቁጣ ዛቻዉም በሃያኛ አመቱ ዘንድሮ ተደገመ።ዳላይ ላማም ቃል አቀባያቸዉ በቀደም እንዳሉት አጋር ያገኘ ያክል በድጋሚ ተደሰቱ።
«ዳላይ ላማ በዚሕ ዜና በጣም ነዉ የተደሰቱት።ለ-ሊዩ ሽኦቦ ልባዊ ደስታቸዉን ይገልጣሉ።ሊዩ ሽኦቦና ሌሎች በርካታ የቻይና ምሑራን የፈረሙት ቻርተር 08 ለቻይና በጣም ተገቢ ነገር ነዉ ብለዉ ያምናሉ።ወጣቱ የቻይና ወጣት ትዉልድ የነዚሕን ብርቱዎች ትግል ፍሬ ይቀምሳል የሚል ተስፋም አላቸዉ።»

ጎርቫቶች ግላሲኖስትና ፔሬስትሮይካ ብለዉ የጀመሩት መርሕ የአብዛኛዉን አለም ኮሚንስታዊ ሥርዓት ከፈረሰ እነሆ-ሃያ አመት አለፈ።የቻይናዉን ግን የምዕራቡ ጫና፥ የጎርቫቾቭ ሥልት፥ የተማሪዎችዋ ሰልፍ፥ የምሁራንዋ ፅሁፍ፥ የዳይላ ላማ ፀሎት-እንዲያዉ በምጣኔ ሐብቱ መስክ አፈረጠመዉ እንጂ አልነቀነቀዉም።ከእንግዲሕስ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ