1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አልረታ ያለ ዓለምን አንቆ የያዘ ድህነት

ሐሙስ፣ የካቲት 16 1998
https://p.dw.com/p/E0e0

አሁንም ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጥ የዓለም ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ተገቢው የጤና እንክብካቤና መኖሪያ፤ እንዲሁም ለዕለታዊ ኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ሁኔታዎች ሳይሟሉለት መቀጠሉ ነው ጎልቶ የሚታየው። ይህን በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት መቀመጫ ተሰብሰበው የነበሩ የልማት አዋቂዎችና ነጻ ታዛቢዎች በጋራ አረጋግጠዋል።

“ድህነት ያለማቋረጥ በዓለም ዙሪያ የሚስፋፋ የተላላፊ በሽታን ያህል መቅሰፍት ነው!” ይህን በቅርቡ የተናገረችው ባለፈው አሠርተ-ዓመት ድህነትን በመታገሉ አኳያ የተደረገ ዕርምጃ ካለ ለመገምገም በተሰየመው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ አንድ የሲቪል ማሕበረሰብን ቡድን ወክላ ንግግር ያሰማች የ 17 ዓመት ወጣት ፊሊፒናዊት ነበረች። ወጣቷ የሱሣ ጋምቦዋ የዘመቻው ዓላማ የሚገባውን ያህል በሕዝብ ዘንድ አለመስፋፋቱንና እንዲያውም በተለይ የሕጻናትና የወጣቱ ድህነት ይበልጥ እየከፋ እንደመጣ ከራሷ ቤተሰብ ጭብጥ ሁኔታ በመነሣት አስረድታለች።

ያለፈውን አሥር ዓመት ድህነትን የማጥፋት ዘመቻ ውጤት ለመገምገም የተካሄደውን ስብሰባ የመራው የተባበሩት መንግሥታት የማሕበራዊ ልማት ኮሚሢዮን ነው። ጸረ-ድህነቱ ዘመቻ የተንቀሳቀሰው ዴንማርክ ርዕሰ-ከተማ ኮፐንሃገን ላይ እ.ጎ.አ. በ 1995ዓ.ም. የተካሄደው የዓለም መንግሥታት የማሕበራዊ ልማት ፖሊሲ ጉባዔ ያስተላለፈውን ውሣኔ ተከትሎ እንደነበር ይታወሣል። በጊዜው የመንግሥታቱ መሪዎች ከዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ ጋር በመተባበር ድህነትን፣ ሥራ-አጥነትንና ማሕበራዊ መገለልን ለመታገል የየራሳቸውን ብሄራዊ የተግባር መርህ ለማስፈን መስማማታቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ይሁንና ድህነትን ለማስወገድ የተወጠነው የአሥር ዓመት ጊዜ አሁን ሲጠናቀቅ የዓለምአቀፉ ድርጅት ባለሥልጣናት፣ ነገር አስተንታኞች፣ የሲቪል ማሕበራት ተጠሪዎችና ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ዘመቻው የረባ ውጤት አለማስከተሉን በአንድ ድምጽ በመናገር ላይ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት የኤኮኖሚና የልማት ጉዳይ ምክትል ባለሥልጣን ሆሤ-አንቶኒዮ-ኦካፖ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር ምንም እንኳ በተወሰኑ አካባቢዎች የማይናቅ ዕርምጃ መደረጉ ባይቀርም ኮሚሢዮኑ ድህነትን ከማስወገድ ውጥኑ ገና ብዙ ርቆ እንደቀጠለ መሆኑን ነበር ያስገነዘቡት።

ኦካፖ በምሥራቅና በደቡባዊው እሢያ፤ እንዲሁም በሰላማዊው ውቂያኖስ አገሮች ድህነትን ለመቀነስ ቢቻልም በሌሎች የዓለም አካባቢዎች ከዘጠናኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ወዲህ እንዲያውም የኋልዮሽ ሂደት ሰፍኖ መቀጠሉን ሳይጠቅሱ አላለፉም። የድህነት ቀንበር በብዙዎች አገሮች፣ በተለይም ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል በከፋ ሁኔታ እንደጸና ቀጥሏል።

እርግጥ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ዕቅድ ተቋም የ 2005 ዘገባ መሠረት በአማካይ መስፈርት ሲታይ በታዳጊ አገሮች ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ የሚተዳደረው ድሃ ሕዝብ ብዛት ከ 1990 እሰከ 2000 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከ 27 ወደ 21 በመቶ ዝቅ ብሏል። 130 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋ ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ጥቂት ሊሻሻል ችሏል ማለት ነው።

ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል የታየው ሃቅ ከዚህ ለየት ያለ ነው። ከ 1990 እስከ 2001 ባለው አንድ አሠርተ-ዓመት በአካባቢው የዕለት ኑሮውን አንዲት ዶላር በማትሞላ ገቢ የሚገፋው ሕዝብ ቁጥር እንዲያውም በመቶ ሚሊዮን መጨመሩን ነው ዘገባው ያመለከተው። በአጠቃላይ ጸረ-ድህነት ዘመቻው ከተከፈተ ከአንድ አሠርተ-ዓመት በኋላም ከአርባ በመቶ የሚበልጠው የዓለም ሕዝብ ገና ከዕለታዊው የድህነት መዘዝ ሊላቀቅ አልቻለም።

ከመንግሥታት ነጻ የሆኑት ድርጅቶች የማሕበራዊ ልማት ኮሚቴ ያለፈውን አሠርተ-ዓመት ዓለም የገባውን ቃል ያፈረሰበት የድህነት አሠርተ-ዓመት ነው ብሎታል። የኮሚቴው ሊቀ-መንበር ለጉባዔው እንዳስረዱት ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ ከእንግዲህ አብዛኛው ሕዝብ በድህነት እንዲኖር የተገደደባትን ዓለም በትዕግሥት ሊመለከት አይገባውም። በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት የማሕበራዊ ልማት ኮሚሢዮን በገባው ቃል በመጽናት በአዲሱ አሠርተ-ዓመት ፍቱን ስልት አውጥቶ መቀጠል ይጠበቅበታል።

ምርጫው ዘዴን አሻሽሎ በዘመቻው መቀጠል ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል የተባበሩት መንግሥታት ኮሚሢዮን ዘመቻውን ፍቱን ለማድረግ አስተማማኝ’ የሰንጠረዥ አያያዝ ዘዴን በአስቸኳይ ማስፈኑ አስፈላጊ መሆኑን ቀደምት የኤኮኖሚ ጠበብት ያሳስባሉ። አንዲት ዶላር በቀን በሚል መስፈርት ላይ የተመሠረተው የእስካሁኑ ዘዴ በድህነት መቀነስም ሆነ መጨመር ላይ ተገቢውን ግምት ለመውሰድ አመቺ ሆኖ አልተገኘም የሚል ማሳሰቢያም ተሰንዝሯል።

የተባበሩት መንግሥታት ዓባል ሃገራት ከአሥር ዓመታት በፊት ድህነትን በማስወገዱ ዓላማ የገቡትን ቃል በተለይ ድርጅቱ በ 2000 ዓ.ም. ጉባዔው ኒውዮርክ ላይ ባሰፈነው የሚሌኒየም ዕቅድ አማካይነት ደግመው ማረጋገጣቸው የሚታወስ ነው። ከሚሌኒየሙ ዕቅድ ሥምንት ነጥቦች መካከል እስከ 2015 ድህነትና ረሃብን በግማሽ መቀነሱ፣ መሠረታዊ ትምሕርትን ለሁሉም ማዳረሱ፣ የሕጻናትን መሞት በሶሥት-አራተኛ መቀነሱና የበሽታን መስፋፋት መግታቱ፤ እንዲሁም የተፈጥሮን ጥበቃን የመሳሰሉት ዓበይት ጉዳዮች ይገኙበታል።

የምጣኔ ሐብት አዋቂዎች እንደሚሉት እነዚህን ውጥኖች ከግብ ማድረስ-አለማድረሱ ባለፉት ዓመታት በተለይ በምዕራባውያን አበዳሪዎች የልማት ዕርዳታ መጨመር ላይ ጥገኛ ሆኖ ነው የታየው። ግን ይህ በተግባር እምብዛም ገቢር አልሆነም። ምክንያቱም በጎ ፈቃድ ጠፍቶ እንጂ አቅሙ ታጥቶ አይደለም። የቀድሞይቱ የብሪታኒያ መንግሥት የካቢኔ ዓባልና የም/ቤት እንደራሴ ክሌር ሾርት እንደተናገሩት ዓለም ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰውልጅን ከድህነት፣ ከመሃይምነትንና ከድህነት መቅሰፍት ለማላቀቅ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ብቃት ያገኘበት ወቅት ነው።

የወቅቱ የዓለም ኤኮኖሚ ትስስር ሂደት ሁኔታውን ለመለወጥ ወይም ለመላው የዓለም ሕዝብ የልማት ዕድል ለመስጠት በቂ ዕውቀት፣ ገንዘብና የቴክኖሎጂ ጥበብ መኖሩን ያረጋግጣልም ብለዋል። ይሁን እንጂ ብቃቱ መኖሩ ባይታበልም በዓለም ላይ በአስከፊ የድህነት ሁኔታ የሚኖረውን ሕዝብ ቁጥር እስከ 2015 በከፊል ለመቀነስ የተገባውን ቃል በብዙዎች አገሮች ዕውን ማድረጉ አጠያያቂ ጉዳይ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ለዚህም ምክንያት አልታጣም።

ሃብታም አገሮች ወጪው ሲበዛ ከፍተኛ ሆናል በሚል ግዴታቸውን ከመወጣት ማንገራገራቸው ሃቅ ነው። ድህነትን አለማስወገድ የሚያስከትለው ወጪ ይበልጥ የላቀ መሆኑን ለመቀበል አልቻሉም ወይም አልፈለጉም የሚሏቸው ተቺዎች ጥቂቶች አይደሉም። በአጠቃላይ ሁኔታው ካልተለወጠ ያለፈው አሠርተ-ዓመት ክስረት የመጪውም አሠርተ-ዓመት ገጽታ መሆኑ የማይቀር ጉዳይ ነው የሚመስለው።

የደቡብ አፍሪቃ መሬት ለደቡብ አፍሪቃውያን! የሚለው በአገሪቱ መንቀሳቀስ የያዘ ሃሣብ ለሃብት ወደ ውጭ መሸሽ ምክንያት እንዳይሆን በአገሪቱ ባለሥልጣናት ዘንድ ጥቂትም ቢሆን ስጋት ሳያሳድር አልቀረም። ለደቡብ አፍሪቃ ብዙሃን ጥቁሮች የመሬት ስሪት ለማድረግ የገባውን ቃል እስካሁን ዕውን ያላደረገው የፕሬቶሪያ መንግሥት የሰየመው አሥር ዓባላትን ያቀፈ አንድ ቡድን ሰሞኑን ባቀረበው የጥናት ውጤት የውጭ ተወላጆች አንድ ዘላቂ ሕግ እስኪሰፍን ድረስ ለጊዜው መሬት ከመግዛትም ሆነ ከመሸጥ እንዲታቀቡ መንግሥትን አሳስቧል።

ኮሚቴውን በ 2004 ዓ.ም. የሰየሙት የደቡብ አፍሪቃ የእርሻና የመሬት ይዞታ ሚኒስትር ቶኮ ዲዲዛ ናቸው። ዲዲዛ ሰሞኑን ፕሬቶሪያ ውስጥ የኮሚቴውን ዘገባ እንደተቀበሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሃሣቡን ለመንግሥታቸው ካቢኔ እንደሚያቀርቡና ይሄው ሰነድ በጉዳዩ ለመከራከር ጠቃሚ መረጃ መሠረት እንደሚሆንም አስረድተዋል። የኮሚቴው ውሣኔ መሬት የሌለውንና በአፓርታይዱ አገዛዝ ዘመን ንብረቱ የተወረሰውን ዜጋ ስሜት በሚገባ ያስተዋል ሳይሆን አልቀረም።

ከአፓርታይዱ አገዛዝ ዘመን በኋላ በ 1994 ዓ.ም. የተቋቋመው የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በነጮች ከተያዘው መሬት ሰላሣ በመቶውን በአምሥት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጥቁሮች እንደሚያስተላልፍ ነበር በጊዜው ቃል የገባው። ግን ዛሬ ከ 11 ዓመታት በኋላ ሁለት በመቶው መሬት ብቻ ነው ወደ ጥቁሮች ዕጅ ሊሸጋገር የበቃው። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በበለጠና በተፋጠነ ሁኔታ ለውጡ መካሄድ አለበት የሚለው አስተሳሰብ በሕብረተሰቡ ውስጥ እያደገ መጥቷል።

ፕሬዚደንት ታቦ እምቤኪ በቅርቡ ለሕዝብ ባሰሙት ንግግር መንግሥታቸው በነጮች የመሬት ይዞታና አጠቃቀም ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩር መጥቀሳቸው የተጓተተው የመሬት ስሪት መካሄዱን የሚሹትን የብዙሃኑን ድጋፍ ማስከተሉ በግልጽ ታይቶ ነበር። በሌላ በኩል ይሁንና የነጮች መሬት ቢነጠቅ ወይም በተወሰነ የካሣ ክፍያ ቢወረስ የውጭ ካፒታልን ማቆልቆል አስመልክቶ በደቡብ አፍሪቃ ላይ ሊኖረው የሚችለው የኤኮኖሚ ተጽዕኖ እስከምን እንደሚሆን የሚቀርብ ተጨባጭ ግምት የለም። በወቅቱ ሌላው ቀርቶ ምን ያህል መሬት በነጮች ተይዞ እንደሚገኝ እንኳ በትክክል ለመናገር አዳጋች መሆኑ ነው የሚነገረው።

ለማንኛውም የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ለብዙሃኑ ጥቁሮች የገባውን ቃል በማጓተት መቀጠል ከማይችልበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል። የዚምባብዌን መሰል በሃይል የነጮችን መሬት የመንጠቅ ሁኔታ ፍርሃቻ መቀስቀሱም አልቀረም። እርግጥ የእርሻ ሚኒስትሩ ዲዲዛ እንደሚሉት የደቡብ አፍሪቃ ሕገ-መንግሥት መልሶ ለማከፋፈል አግባቢ ሁኔታ እስካልሰፈነ ድረስ መሬት መውረስን የሚፈቅድ አይደለም። ግን መንግሥት ተገቢ ሆኖ የሚገመት ካሣ ለገበሬዎች በመክፈል ችግሩን ለማቃለል ይችላል።

የሆነው ሆኖ የፕሬቶሪያ መንግሥት በአጥኚው ኮሚቴ የቀረበለትን ሃሣብ እንዳለ ተቀብሎ ገቢር ለማድረግ መወሰኑን የሚጠራጠሩት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው። ምናልባት ለውጡን በገጠር አካባቢዎች ትዕግስቱን እያጣ የመጣውን ሕዝብ ለማስታገስ ያህል ለዘብ ባለ መልክ ለማፋጠን ዕርምጃ እንደሚወሰድ ነው የሚታመነው።