1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አልበሽር ታሰሩ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 3 2011

በተለይ ለአራት ወራት የዘለቀውን ተከታታይ ተቃውሞ ሲያስተባብር የነበረው የሱዳን ሙያተኞች ማህበር ወታደራዊውን መፈንቅለ መንግሥት እንደማይደግፍ አስታውቋል። ማህበሩ የአል በሽር አስተዳደር በሲቪል የሽግግር መንግሥት እንዲተካ እንጂ ሥልጣኑን ወታደራዊ ምክር ቤት እንዲይዝ እንደማይፈልግ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/3GdNM
Sudan Weiterhin Proteste |
ምስል Reuters/M. Nureldin Abdallah

አል በሽር ከሥልጣን ወረዱ ታሰሩም

የሱዳን ጦር ኃይል የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽርን ዛሬ ከሥልጣን ማውረዱን እና ማሰሩን አስታውቋል። የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር በመንግሥታዊው ቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ ሀገሪቱ በሚቀጥሉት ሀለት ዓመታት በወታደራዊ ምክር ቤት እንደምትመራ ተናግረዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ዛሬ ጠዋት አደባባይ በመውጣት ደስታውን ሲገልጽ የነበረው ህዝብ የሽሽግሩ ምክር ቤት ሊቀመንበርም ከሆኑት ከመለላከያ ሚኒስትሩ መግለጫ በኋላ ተቃውሞውን ማሰማት ቀጥሏል ። ለወራት የዘለቀውን አመጽ ያስተባበረው ማህበር በወታደሩ የተፈጸመውን መፈንቅለ መንግሥት እንደማይደግፈው ተናግሯል። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኝ ወታደራዊው መፈንቅለ መንግሥት የሱዳኑን ተቃውሞ ሊያባባስ ይችል ይሆናል ብለዋል።የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አል በሽር ከሥልጣን መውረዳቻቸውን እና በቁጥጥር ስር መዋላቸውን  በሱዳን መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ያሳወቁት የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር እና ምክትል ፕሬዝዳንት አዋድ ኢብን አውፍ ናቸው። አዋድ ኢብን አውፍ ዛሬ ከቀትር በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የጦር ኃይሉ ሥልጣኑን ተረክቧል፤ ሀገሪቱን የሚመራ ወታደራዊ ምክር ቤት ተመስርቷል።
«በጎርጎሮሳዊው 2005 ዓም የጸደቀውን የሱዳን ህገ መንግሥት በማገድ፣ ሀገሪቱን ለሁለት ዓመት የሚመራ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት መመስረቱን አስታውቃለሁ። ለሦስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲሁም በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ለሊት 10 ሰዓት የሚቆይ ሰዓት እላፊ ለአንድ ወር ተደንጓጓል። ተጨማሪ ማብራሪያ እስኪሰጥ ድረስ የአየር ክልሉን እና ወደ ሀገሪቱ የሚያስገቡ ወደቦችን በሙሉ ለ24 ሰዓታት ዘግቻለሁ። ፕሬዝዳንታዊውን ተቋምና ካቢኔውንም አፍርሻለሁ»
አውፍ ጦር ኃይሉ የሽግግሩን ጊዜውን በዋነኝነት እንዲመራ እና ሀገሪቱን ከደም መፋሰስ እንዲከላከል ጦር ኃይሉን እና ሌሎች አካላትን ያካተተው የደህንነት ኮሚቴ ነው መወሰኑን ነው በመግለጫቸው ያሳወቁት ። የሀገሪቱ ብሔራዊ የስለላ እና የደህንነት መሥሪያ ቤት የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ እንደተፈቱ አስታውቋል። የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ አንዳንድ የአልበሽር አስተዳደር ባለሥልጣናት መታሰራቸውም ተስምቷል። አልበሽር ከሥልጣን እንደሚወርዱ ሲጠብቅ የነበረው  ህዝብ በዋና ከተማይቱ በካርቱም ጎዳናዎች ደስታውን ሲገልጽ ቢውልም ከመከላከያ ሚኒስትሩ መግለጫ በኋላ ግን ስሜቱ ተቀዛቅዟል። በተለይ ለአራት ወራት የዘለቀውን ተከታታይ ተቃውሞ ሲያስተባብር የነበረው የሱዳን ሙያተኞች ማህበር ወታደራዊውን መፈንቅለ መንግሥት እንደማይደግፍ አስታውቋል። ማህበሩ የአል በሽር አስተዳደር በሲቪል የሽግግር መንግሥት እንዲተካ እንጂ ሥልጣኑን ወታደራዊ ምክር ቤት እንዲይዝ እንደማይፈልግ አስታውቋል። አል በሽርን ያነሳው ጦር ኃይሉ ሥልጣኑን መያዙ በሀገሪቱ ለ4 ወራት ሲካሄድ የቆየውን ተቃውሞውን ሊያባባስ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። አቶ አበበ አይነቴ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስልታዊ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ እና በተለይም የጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አጥኚ  ስጋቱን ይጋራሉ። 
«በጦር ኃይሉ መካከል መከፋፈል የሚኖር ከሆነ ተቃውሞው መጣም ሊቀጥል ይችላል። ተቀውሞው የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ የበለጠ የወታደራዊ ኃይሉ ጉልበት እንዲያገኙ እና ወደ ኃይል እርምጃ ሊገባ ይችላል። ወደ ኃeile እርምጃ የሚገባ ከሆነ ደግሞ የአገሪቱ ሰላም ይናጋል በዚህም የብዙ ሰዎች መፈናቀል እና መሰደድ ሊኖር ይችላል።»  
በአቶ አበበ አስተያየት የሱዳኑ ተቃውሞ ቀጥሎ አለመረጋጋትን ካስከተለ ደግሞ በቀጣናው ሀገራት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም።
«ደቡብ ሱዳን አልተረጋጋችም። ኢትዮጵያም የውስጥ ፖለቲካ ችግር አለባት ኤርትራም እንደዚሁ የኤኮኖሚ የፖለቲካ ማህበራዊ ችግር ያለባት ሀገር ነች። የሶማሊያ ጉዳይ ሌላው ራስ ምታት ነው። እንግዲህ በቀጣናው ያሉ ሀገሮች በሙሉ አቅማቸው የተከፋፈለ እና የየሀገራቱ ኤኮኖሚ እየተዳከመ የውስጥ ፖለቲካውም ያለመረጋጋት ሁኔታ ስላለ አጠቃላይ ይሄ ተደምሮ በቀጣናው ሰላም እና ደህንነት ጉዳይ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ሚና ማሰደሩ የማይቀር ይሆናል።»
ላለፉት 30 ዓመታት ሱዳንን በብረት ጡንቻ በገዙት በፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በአል በሽር ላይ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው በሱዳን ለሦስት ሳምንታት የዶቦ እጥረት ከተፈጠረ እና የዳቦ ዋጋም በሦስት እጥፍ ከጨመረ በኋላ በጎርጎሮሳዊው ታህሳስ 19፣2019 ነበር። ከዚያ በፊትም ባለፈው ዓመት በጥር ወር በምግብ ዋጋ ግሽበት ሰበብ ሰላማዊ ሰልፎች የተካሄዱ ቢሆንም በአጭሩ ነበር የተቀጩት። በጎርጎሮሳዊው 2011 በሀገራቸው የተጀመረው የዓረቡ ዓለም አብዮትም እንዲሁ ብዙም አልዘለቀም። የቀድሞው የኮማንዶ ጦር አባል አል በሽር ሥልጣን የያዙት ደም ባላፋሰሰ መፈንቅለ መንግሥት በጎርጎሮሳዊው 1989 ዓም ነበር። የ3 አስርት ዓመታት  የሥልጣን ዘመናቸውም በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ውስጥ የተለያዩ ቀውሶች ቢገጥመውም በራሳቸው መንገድ ሲወጡት ቆይተዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በጎርጎሮሳዊው 1993 የሱዳንን መንግሥት ሽብርን  ይደግፋሉ ከምትላቸው ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ካስገባች ወዲህ  ሱዳን ለረዥም ዓመታት ተገላ ነበር። አል በሽርም በዳርፉር ተፈጽሟል በተባለ የጦር ወንጀል በዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በጎርጎሮሳዊው 2009 እና 2010 የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸዋል። ዛሬ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላም በዚሁ ምክንያት ወደ ሄጉ ፍርድ ቤት  ሊወሰዱ ይችላሉ የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። የወታደራዊው ምክር ቤት ሊቀመንበር አውፍ የ75ቱ አል በሽር ዛሬ በቁጥጥር ስር መዋላቸው እና በአስተማማኝ ስፍራ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት። 

Sudan Proteste gegen Präsident Omar Al-Bashir in Khartoum
ምስል picture-alliance/AP Photo
Sudan Proteste gegen Präsident Omar Al-Bashir in Khartoum
ምስል picture-alliance/AP Photo
Sudan - Alaa Salah - Die Sudanesin führt Proteste gegen Präsident Omar al-Bashir an
ምስል Getty Images/AFP
Sudan Militär und Demonstranten in Khartoum
ምስል Getty Images/AFP

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ