1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አል-አሙዲን ጨምሮ ሳዑዲ አረቢያ 38 ሰዎችን አሰረች

እሑድ፣ ጥቅምት 26 2010

ሳዑዲ አረቢያ በጸረ-ሙስና ዘመቻ 11 ልዑላን፣ አራት በሥልጣን ላይ ያሉ ሚኒስትሮች እና በርካታ የቀድሞ ሹማምንትን አሰረች። ሮይተርስ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የሳዑዲ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው መሐመድ አል-አሙዲ ከታሰሩት መካከል አንዱ ናቸው።

https://p.dw.com/p/2n3dp
König Salman Bin Abdul Aziz Al Saud und Kronprinz Mohammed Bin Salman Al Saud
ምስል picture-alliance/abaca/B. Press

ኪንግደም ሖልዲንግ የተባለው የመዋዕለ-ንዋይ ኩባንያ ባለቤት ልዑል አልዋሊድ ቢን ታላል ከአስራ አንዱ ልዑላን መካከል ይገኙበታል። የሳዑዲ አረቢያ ብሔራዊ ዘብ አዛዥ የነበሩት ልዑል ሚተብ ቢን አብዱላሕ ታስረው ከሥልጣናቸው ሲሻሩ በልዑል ኻሊድ ቢን አያፍ ተተክተዋል። 38 ልዑላን፣ ሚኒሥትሮች እና እውቅ ባለወረቶች ትናንት ቅዳሜ የታሰሩት ንጉስ ሰልማን በልጃቸው ልዑል መሐመድ የሚመራ የጸረ-ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙን ካስታወቁ በኋላ ነው። ኮሚቴው የእስር ማዘዣ የመቁረጥ፣ የተጠርጣሪዎችን ሐብት እንዳይንቀሳቀስ የማገድ እና የጉዞ ማዕቀብን የመጣል ጨምሮ በርካታ ስልጣኖች ተሰጥተውታል። የ32 አመቱ አልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን አልሳዑድ  ሙስናን ለመታገል ቃል ገብተው ነበር። የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት እስካሁን ይፋ ማረጋገጫ አልሰጠም።  ከሳውዲ አረቢያው ዘጋቢያችን ጋር የተደረገ ተጨማሪም መረጃ በድምፅ ከዚህ በታች ያገኛሉ።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ