1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራ ክልል በጦርነቱ የወደሙ ድልድዮችና መንገዶች

ማክሰኞ፣ ኅዳር 6 2015

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በርካታ ድልድዮች ጉዳት ስለደረሰባቸው ከየከተሞቹ ጋር የሚደረገውን ግንኙነት አዳጋች እንዳደረገባቸው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ የአንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎች አማረዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በበኩሉ የድልድዮች ጥገና እየተካሄደ ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/4JXmn
Äthiopien Sanierung einer Brücke
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በድልድዩ መሰበር ምክንያት የመጓጓዣ ዋጋ ጨምሯል

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ድልድይ ጥገናዎችን እያካሄደ እንደሆነ ገለፀ። በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በርካታ ድልድዮች ጉዳት ስለደረሰባቸው ከየከተሞቹ ጋር የሚደረገውን ግንኙነት አዳጋች እንዳደረገባቸው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ የአንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎች አማረዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በበኩሉ የድልድዮች ጥገና እየተካሄደ ነው ብሏል። 

ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ መንግስትና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል በተደረገው ጦርነት በሕይወት ላይ ከደረሰው ከፍተኛ ጉዳት በተጨማሪ በንብረት ላይ ውድመት ደርሷል። ጉዳት ከደረሰባቸው የመሰረተ ልማት ዘርፎች መካከል መንገዶችና ድልድዮች ይጠቀሳሉ። በተለይ ከተሞችን ከከተሞች የሚያገናኙ ድልድዮች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አቶ ጀማል ስጦታው የኮረም ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ሰቆጣንና ኮረም ከተሞችን የሚያገናኘው የጥራሪ ወንዝ ድልድይ በጦርነቱ በመጎዳቱ በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለው የትራንስፖርት ፍሰት በእጅጉ ተጎድቷል ብለዋል። በተለይ ሸቀጦችን ከከተሞች ወደ ከተሞች ለማድረስ ባለመቻሉ ገበያውን ጎድቶታል ነው ያሉት። «ትራንስፖርት ተቋርጧል። ለጊዜው መከላከያ በዶዘር አስተካክሎ በወንዙ እንዲታለፍ አድርጓል። አውቶቡሶችና ታላላቅ ተሸከርካሪዎች ለመንቀሳቀስ አስቸግሯቸዋል። ድልድዩ ከሌለ ማነኛውም ሸቀጥ መተላለፍ አስቸጋሪ ስለሚሆን ይህ ከባድ ያደርገዋል። መከላከያ በቦታው አለ። አሁን እየተሠራ ነው መጠናቀቁን አላውቅም።»
 
አማኑኤል አሰፋ የቆቦ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ወልዲያን ከቆቦና አላማጣ ከተሞች የሚያገናኘው የአለውሀ ወንዝ ድልድይ በጦርነቱ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጠዋል። ተሸከርካሪዎች በወንዝ ውስጥ ለመሻገር በመገደዳቸው የተሸከርካሪዎቹ የውስጥ እቃ እየተጎዳ ነው፤ በዚህ ምክንያትም የትራንስፖርት ታሪፍ ጨምሯል ብለዋል። «በትራንስፖርት የዋጋ ጭማሪ አለ። የሚሄዱበት (በወንዙ ላይ) ጠመዝማዛ ነገር ስለሆነ ተሸከርካሪዎችን ይጎዳል። ድንጋይ፣ ውኃ ስላለው ማለት ነው። ትራንስፖርት (ከቆቦ ወልዲያ) ከ50 ብር ወደ 100 ብር ሆኗል። ጊዜያችንንም በአግባቡ እንዳንጠቀም አድርጎናል። መንገዱ በፊት ከነበረው 12 ኪሎ ሜትር ጨምሯል። አማራጭ መንገድ በመጠቀማችን፣ በተለይ ለከባድ ተሸከርካሪዎች በጣም አስቸጋሪ ነው።»
 
የወልዲያ ከተማ ነዋሪው አቶ ወርቁ ተገኝም በወልዲና በቆቦ መካከል ያለው ድልድይ ባለመጠገኑ ኅብረተሰቡ የጊዜና የኢኮኖሚ ብክነት እንደደረሰበት አስረድተዋል። «ወደ ቆቦ ነዳጅ እየገባ አይደለም (የነዳጅ ቦቴዎች መሻገር ስለማይችሉ)፣ ከወልዲያ አላማጣ 80 የነበረው የትራንስፖርት ታሪፍ 200 ብር ገብቷል በድልድዩ መሰበር ምክንያት። ባለሀብቶችም የመኪናዎቻቸው እቃ እየተጎዳባቸው ነው። ብረት ድልድይ ስለሚሠራ አሁን ብረት ቀርቧል፣ ግን እስካሁን አልተሠራም።» 

Äthiopien Sanierung einer Brücke
የድልድይ ጥገናዎችን የሚያደርጉ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድልድዮችና ስትራክቸር ሥራዎች ዳይሬክተር ኢንጂኔር ጌትነት ዘለቀ በስልክ ተጠይቀው ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት ምላሽ፦ የአለውሀና የጥራሪ ድልድዮች ግንባታ እየተካሄደ ነው። «አለውሀን ጠገንን፣ እንደገና ተመልሶ ተጎዳ። አሁን ሁለተኛ እሱን እየሠራን ነው ያለነው። ድልድዩን ከፈንጁ በተጨማሪ ጎርፍም ጎድቶት ስለነበረ፣ … አሁን ተገጣጣሚ ድልድይ እንሠራለን። የአለውሀውን ማለት ነው። የጥራሪውንም ተሸካሚዎቹ ግራና ቀኝ ያሉት ግንቦች ደህና ስለሆኑ ድልድዩ ከላይ ብቻ ስለሆነ የወደቀው፣ እስንም የመተካት ሥራ እየሠራን ነው። በሚቀጥሉት አምስትና ስድስት ቀናት ውስጥ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል የጥራሪው።»

እንደ ኢንጂኔር ጌትነት ከዚህ በፊት ሁመራን ከሸራሮ ወይም አዲጎሹን ከሽሬ የሚያገናኘው የተከዜ 3፤ አብነትን ከአምደወርቅ የሚያገናኘው የተከዜ 1 ድልድዮች፣ ወልዲያን ከሚሌ የሚያገናኘው የጨረርቲ ድልድይና የጎቦ ድልድይ ግንባታቸው ተጠናቀቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነዋል ብለዋል። አጠቃላይ ከዚህ በፊት ለጥገና እና በጥገና ላይ ለሚገኙት ድልድዮች 160 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉንም ባለሞያው ተናግረዋል። ሌሎች የተጎዱ ድልድዮችም ሪፖርት ሲደረግልን እየተከታተልን እንጠግናለንም ብለዋል። 

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ