1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

አረንጓዴ እና ዘመናዊ የህፃናት መጫወቻ ስፍራ

ዓርብ፣ ሐምሌ 7 2009

ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ይካሄዳል። ከእነዚህ መካከል አዲስ አበባን በምሳሌነት መዉሰድ ይቻላል። ለመሆኑ ቤቶቹ ሲገነቡ ልጆች የሚጫወቱበት ቦታ ምን ያህል ታሳቢ ይሆናል? የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዶቻችን ይህ ጉዳይ አሳስቧቸው ብቻ ሳይሆን፤ መፍትሄ ይሆናል ያሉትንም ሀሳብ ይዘው ቀርበዋል።

https://p.dw.com/p/2gQ52
Äthiopien #youforG20  Children reclaim space
ምስል Children reclaim space

mmt Jugend140717_Kinder brauchen Spielplätze - MP3-Stereo

በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ሦስት ጓደኛሞች ናቸው። መዝገበ ዘርፉ፤ ቶማስ ደረሰ እና እንግዳወርቅ አስራት ይባላሉ። ተገናኝተው ስለ ልጅነት ጊዜያቸው ሲያወጉ እና ታናናሾቻቸዉን ሲመለከቱ ልጆቹ እንደነሱ ውጪ ተጫውተው ማደግ አለባቸው ብለው ብቻ ሳይሆን የሚያምኑት፤ በአግባቡ እና አመቺ ሆኖ ለነሱ የተሠሰራ የመጫወቻ ስፍራም ያስፈልጋቸዋልም ባይ ናቸዉ። ይሁንና በከተማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚታዘቡት ተቃራኒውን ነው። « ህፃናት የሚጫወቱበት በቂ ቦታ አልተዘጋጀላቸውም»ይላል ሲቪል መሀንዲሱ መዝገበ። ጎልማሶቹ ይህንን ችግር እንዴት መቅረፍ እንችላለን በሚለው ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ተወያይተዋል። መፍትሔ የሚሉትንም ሀሳብ የንግድ አስተዳደር ባለሙያዉ እንግዳወርቅ ያብራራል። «ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘ የመጫወቻ ስፍራ ነው መፍጠር የምንፈልገው ።» ይላል  እንግዳወርቅ።

Äthiopien #youforG20 Kinderspielplatz
መዝገበ ዘርፉ በስተ ግራ፤እንግዳወርቅ አስራት (የፀሀይ መነፅር ያደረገው) እና ከእሱ በስተ ግራ በኩል ቶማስ ደረሰ ፤ ከልጆች ጋር ሲጫወቱምስል Children reclaim space

ሀሳቡን ከጀመሩ ሦስት ዓመት የሆናቸው ጓደኛማቾች እስካሁንስ በተግባር ምን አድርገዋል? ከእነሱ አንዱ የሆነው ቶማስ፤ የተለያዩ መጫወቻዎችን ለሙከራ መስራታቸውን ይናገራል። ቶማስ ሜካኒካል መሀንዲስ ነው። ሁሉም በትርፍ ጊዜያቸው ነው ተሰባስበው የጋራ ሀሳባቸው በሆነው አላማ ላይ የሚሰሩት። በተለይ ባለፉት ሳምንታት ደግሞ ይበልጥ በአላማቸው ላይ አተኩረው ሰርተዋል። በአንድ ውድድርም ተካፍለዋል። ውድድሩ ባለፈው ሳምንት በጀርመን ሀምቡርግ ከተማ ከተካሄደው የቡድን 20 አባል ሃገራት ጉባኤ ጋር ይያያዛል። #youforG20 በሚል ርዕስ ስር ለከባቢ አየር ወይም ለማህበረሰቡ እና ለታዳጊው ጠቃሚ መርሀ ግብር ይዘው ቀርበዋል የተባሉ 140 ተወዳዳሪዎች ከመላው ዓለም ተሳትፈዋል። የድምፅ አሰጣጡ የተከናወነዉ በኢንተርኔት ወይም ኦንላይን ሲሆን፤ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙት አምስት ፕሮጀክቶች በዳኛ ተመርጠው አሸናፊው 15 000 ዮሮ ያገኛል። ለአላማቸው ይህንን ድጋፍ ለማግኘት ሦስቱ ጎደኛማቾች ለአመታት በሀሳብ ደረጃ ይዘው የነበረውን እቅድ በወረቀት ላይ አስፍረው ለሀገር እና ለውጭው ማህበረሰብ ሰሞኑን አስተዋውቀዋል። መዝገበ እንደሚለው ከህዝብ ያገኙት ምላሽ የተለያየ ነው። ከደጋፊ አንስቶ እንደ ቅንጦት እስከሚያዩ ገጥሟቸዋል።

በተለይ በውጪው አለም ልጆች የተመቻቸ የመጫወቻ ስፍራ ኖሯቸው ውጪ ወጥተው አይጫወቱም፤ ኮምፒውተር እና ቴሊቪዥን ላይ ነው አብዛኛውን ጊዜ የሚያጠፉት እየተባለ ይተቻል። እኢአ በ 1950 ዓም ጀርመን ሀገር የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች መገንባት የተበራከቱት ከተሽከርካሪዎች መብዛት የተነሳ፣ ከተሞች እያደጉ እና እየተስፋፉ ስለሄዱ ልጆች አደጋ በማይበዛባቸው ፣ አረንጓዴ በሆኑና በታጠሩ ቦታዎች ተጫውተው እንዲያድጉ በሚል ነው። ዛሬ የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች ከጋራ መኖሪያ ቤቶች የማይነጠሉ ናቸው።

ጓደኛሞቹ በ #youforG20 ውድድር አሸናፊ  ሆኑም አልሆኑም አላማቸውን እውን ለማድረግ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆነው እንደሚሠሩ ይገልፃሉ።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ