1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የሊቢያ የፀጥታ ሁኔታ

ዓርብ፣ ኅዳር 5 2007

በሊቢያ የሚታየዉ የፀጥታ ሁኔታ እጅግ አደገኛና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ስጋት ላይ ጥሎአል። ለዘመናት ሊቢያን በደቋሽ ክንዳቸዉ የገዙት የሊቢያዉ መሪ ሞአመር ጋዳፊ ከስልጣና ከተወገዱ ከሶስት ዓመት በኋላ ዛሬ የሚታየዉ የርስ በርስ ጦርነት ሀገሪቱን ወደ መንኮታኮት እያመራት መሆኑ ተመልክቶአል።

https://p.dw.com/p/1DnFX
Gefechte in Bengasi Libyen 22.10.2014
ምስል Abdullah Doma/AFP/Getty Images

በሊቢያ በየዕለቱ የሚታየዉ ዉጥንቅጥ ሀገሪቱን ቀስ በቀስ በማንኮታኮት ላይ መሆኑ ተገልፆአል። በትሪፖሊስ የቦንብ ጥቃት፤ በምስራቅ ሊቢያዊትዋ ቶብሩክ ከተማ የፍንዳታ አደጋ፤ ቤንጋዚ ከተማ የሁለት ተቀናቃኝ ሚሊሽያ ቡድኖች ደም አፋሳሽ ዉግያ የመሳሰሉት የየተለት ርዕሰ ዜናዎች ከሊቢያ የሚሰሙ አሳዛኝ ክስተቶች ናቸዉ። ትናንት ሃሙስ በሊቢያዋ መዲና ትሪፑሊስ ላይ ሁለት መኪና ላይ የተጠመደ ቦንብ ፈንድቶ ከባድ ጉዳትን አስከትሎአል። ከትናንት በስትያ ረቡዕ በምሥራቃዊዉ የሀገሪቱ ክፍል በተጣለዉ ጥቃት ቢያንስ አምስት ወታደሮች ተገድለዋል። በሀገሪቱ በቅርብ ጊዜያት ክስተቶች እንደሚያመላክቱት፤የፀጥታ ሁኔታዉን መቆጣጠር አልተቻለም። በሊቢያ ሁለት ፓርላማ እና ሁለት መንግሥታት ስልጣን ላይ መሆናቸዉ በሀገሪቱ ይህ አይነቱ የየዕለት ቀዉስ ለመከሰቱ እና ለመታየቱ ዋንኛ ምክንያት መሆኑ ተገልፆአል። ከተቀናቃኞቹ መካከል በአንዱ ወገን ጽንፈኛ አክራሪ ሲሆኑ በሌላ ወገን ያለዉ ደግሙ ተቀናቃኝ ቡድኑ ነዉ። የሊቢያን ሃብት በእጃቸዉ ለመቆጣጠር እና በሀገሪቱ ዉስጥ የሚገኘዉን እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉን ሚሊሽያ ለመዘወር የሚዋጉት ሁለቱ የሊቢያ ተቀናቃኝ ቡድኖች በጋራ ለዘመናት ሥልጣን ላይ የነበሩትን የቀድሞዉን የሊቢያ መሪ የሞአመር ጋዳፊመንግሥት ለመጣል ትግል ሲያካሂዱ መቆየታቸዉ ይታወቃል። ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ ግን ሁለቱ ቡድኖች በተናጠል የየራሳቸዉን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚካሂዱት ትግል በሀገሪቱ አስከፊ ገፅታ ያለዉን ወንጀል እየፈፀሙ ይገኛሉ፤ ሲሉ በጀርመን ማይንዝ ከተማ ዩንቨርስቲ በዓረብ ሀገራት ጥናት ተቋም ፕሮፊሰር ጉንተር ማየር ተናግረዋል፤

Explosion einer Autobombe nebst der ägyptischen Botschaft in Tripolis
ምስል M. Turkia/AFP/Getty Images

« ይህ ሁሉ የሚያሳየዉ የዓረቡ ዓለም የርስ በርስ ጦርነት ላይ መሆኑን ነዉ። በአንድ በኩል አክራሪ ፅንፈኞቹ ከደጋፊዎቻቸዉ ካታርና ከቱርክ የጦር መሳርያ እገዛ በሚስራታ በኩል ማስገባታቸዉን የሚያመላክት መረጃ ተገኝቶአል። በሌላ በኩል ደግሞ ግብፅ እና የዓረብ ኤሜሪትስ በጥምር እዉቅና ያገኘዉን የቶብሩክ መንግስት ይደግፋሉ»

በሊቢያ የሚታየዉ የፖለቲካ አሰራር የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ እንዲዳከም እንደዉም በአጠቃላይ ፀጥታዉ እንዲታወክ መዳረጉ ነዉ የተመለከተዉ። ለዚህ ክስተት ዋና ምክንያቱ ደግሞ የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ ሞአመር ጋዳፊ ተጠቃሽ ናቸዉ። የአብዮቱ አራማጅ ብለዉ ራሳቸዉን ይጠሩ የነበሩት የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ ሞአመር ጋዳፊ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በሀገሪቱ የፖለቲካዉ አሰራር እንዳይጎለብት ተፎካካሪዎቻቸዉን በሙሉ ማጥ ዉስጥ እየዘፈቁ ስልጣኑን ተቆናጠዉ ለመቀመጥ ጥረት ማድረጋቸዉ ይታወቃል። ለዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሰዉ ጋዳፊ የቤተ-መንግሥት ልዩ ኃይላት ላሉዋቸዉ ጠባቂዎቻቸዉ የተትረፈረፈ ጥቅምን በመስጠት የሀገሪቱን ወታደሮች እና የፀጥታ ሃይላቶች ንቀዉ መተዋቸዉ ነበር ። ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ የተያዘዉ እቅድ፤ ሚሊሽያዉን በሀገሪቱ የፀጥታ ኃይል ዉስጥ ማዋቀር ነበር። ግን ይህ ዕቅድ እንደታሰበዉ አልተሳካም። ሚሊሽያዎቹ ከመንግሥት ደምወዝን ቢያገኙም እንደ ፀጥታ አስከባሪ ፖሊስ ወይም ወታደር ሃገሪቱን ለማገልገል ሳይሆን የሚታገሉት የራሳቸዉን ጥቅም ለማስጠበቅ ሆነ፤

ብሔራዊ ጥምረትን በመስረት ያልቻለችዉ ሊቢያ በመንኮታኮት ላይ መሆንዋን አንዳንድ ታዛቢዎች ይናገራሉ። ራስ-ገዝ የነበሩት ትሪፖሊናታ ፤ ሳይሪናካ እና ፋሳና ግዙፍ የሊቢያ ግዛቶች ከጎርጎረሳዉያኑ 1963 ዓ,ም በኋላ ማዕከላዊ መንግሥትን በማቋቋም መጣመራቸዉ ይታወቃል። ይህ ጥምረት በአሁኑ ግዜ ባለዉ የፀጥታ ሁኔታ አደጋ ላይ መዉደቁ ነዉ የሚነገረዉ። የሙስሊም ፓርቲ በሀገሪቱ በነበረዉ ምርጫ ሽንፈቱን አልተቀበለም። ባለፈዉ ነሃሴ ወር ሚስራታ በሚገኙት አክራሪ ሚሊሽያዎች በመታገዝ መዲና ትሪፖሊስን ተቆጣጥሮአል። በቅርቡ የተካሄደዉን የፓርላማ ምርጫ የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህገ-ወጥ ሲል ምርጫዉን ዉድቅ አድርጎ ፤ በዚህ ምትክ አክራሪዎቹ የራሳቸዉን ፓርላማ መሥርተዋል። በማይንዝ ዩንቨርስቲ የዓረብ ሀገራት ጥናት ተቋም ፕሮፊሰር ጉንተር ማየር የሊቢያዉ መንግሥት እጅግ ደካማ መሆኑ ይገልፃሉ፤

Libyen Stadtansicht von Tripolis
ምስል picture-alliance/dpa

« በይፋ የሚታወቀዉ የሊቢያ መንግሥት እጅግ ደካማ ነዉ። አክራሪ ሚሊሽያዎች የራሳቸዉን መንግሥት መስርተዋል። በሀገሪቱ የሚታየዉ የርስ በርስ ሽኩቻና ትግል፤ በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግ ሳይሆን ፤ በተለያዩ ሚሊሽያ ቡድኖች መካከልና ከሃይማኖት ከማይወግኑ ቡድኖች እንዲሁም ከዘር ሃረግ ጋር ችግር ጋር በተያያዘ ነዉ። »

ሊቢያ ጀሃዲስቶች ያለምንም ችግር የሚኖሩባት ሃገር መሆን ከጀመረች ዓመታት መቆጠራቸዉ ተመልክአል። በጋዳፊ የሥልጣን ዘመን በምስራቃዊ ሊቢያ አክራሪዎች በብዛት የሚገኙበት «ዴርና» ከተማ አካባቢ ሹራ የወጣቶች ምክር ቤት «እራሱን እስላማዊ መንግሥት » ለተባለዉ ፅንፈኛ ቡድን አጋር መሆኑን አሳይቶአል። እንደ ጀርመናዊዉ ምሁር በአሁኑ ወቅት ሊቢያን የሚቆጣጠር ማዕከላዊ መንግሥት የለም። ባለፉት ሶስት ዓመታት የሊቢያነዋሪዎች የሀገሪቱ ሁኔታ በአስከፊ መልኩ በመቀያየሩ በአንፃራዊ ሁኔታ የተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ የነበረዉን የጋዳፊ ሥርዓት ዳግም በሊቢያ እንዲመጣ ይመኛሉ፤ ምንም እንኳ ጋዳፊ አንባገነን የአገዛዝ ስርዓትን ይዘዉ ሊቢያን ረግጠዉ ቢገዙም።

ማርኮ ሙለር / አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ