1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የቅርስ ጥበቃ በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ ነሐሴ 3 2005

የኢትዮጵያ እድሜ ጠገብ ቅርሶች ላይ በተለያየ አቅጣጫ ጥፋት እየፈጸመ መሆኑን፤ በሕገ ወጥ ቅርስ አቀባዮች የሀገሪቱ የታሪክ ማህደር ወደ ዉጭ እየተጋዘ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተነገረ።

https://p.dw.com/p/19MQd
ምስል picture-alliance/ZB

የሰዉ ልጅ መገኛ የሆነችዉ ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪክ የባህልና የቅርሶችም መገኛ ናት። የታሪክ ማህደር የሆነዉ ቅርስዋ የሚደረግለት ጥበቃ ምን ይመስላል? ህብረተሰቡስ ለቅርስ ያለዉ ግንዛቤ ምን ያህል ይሆን? በዕለቱ ቅንብራችን የምንዳስሰዉ ጉዳይ ነዉ።

Saint Yared Choir aus Äthiopien
ምስል DW/A.Tadesse-Hahn

ቅርስ ትናንት እያሳየ፤ ዛሬን እየኖረ፤ ነገን እያመላከተ ማለትም ሶስት ዘመናትን የሚያገኛኝ ድልድይ መሆኑ ይታመናል። ቅርስ ከጥንት ትዉልድ የሚወረስ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ሃብት መሆኑኑም ይገለጻል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ቅርስ የማንነት መገለጫ መሆኑ አያነጋግርም። ግን ለቅርሶቻችን ምን ያህል ክብካቤ እናደርጋለን? ዕዉቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፊሰር ባሕሩ ዘዉዴ፤ በቂ ክብካቤ እንደማይደረግ ቢሆንም፤ አንዳንድ የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ ገልጸዋል። ፕሮፊሰር ባሕሩ ዘዉዴ በመቀጠል በተለይ በከተማ አካባቢዎች የሚታየዉ የግንባታ ሥራ ቅርስን በሚያገናዝብ መልኩ መፈጸም ይኖርበታል፤ ሲሉ አሳስበዋል። ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ዉስጥ በሚገኙ አብያተ ክርስትያናት ተዘዋዉረዉ ጥናት ያደረጉትና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ክብካቤና ልማት ማሕበር መቋቋሙ በይፋ በተገለፀበት ዕለት ስዕላዊ መግለጫ ያቀረቡት፤ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሥነ-ጥበብ ታሪክ መምህር አቶ አበባዉ አያሌዉ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ቅርሶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆናቸዉን ተናግረዋል። በብሪታንያ ከተቋቋመ 14ኛ ዓመቱን የያዘዉ የኢትዮጵያ ቅርስ ማበልፀግያ ማሕበር፤ መስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ ማህበራቸዉ፤ ከኢትዮጵያ በስርቆት ወደ አዉሮጳ የተለያዩ ሀገሮች የተሻገሩ ቅርሶችን በማሰባሰብ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። በሀገሪቱ የሚገኘዉ ቅርስ እንዲጠበቅ ተንቀሳቃሽ ቅርስም ከሀገር እንዳይወጣ እየሠራን ነዉ ያሉት በኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብና ዓለማቀፍ ግንኙነት ረዳት ሃላፊ አቶ ፋንታ በየነ በበኩላቸዉ፤ መስሪያ ቤታቸዉ እስከ ዛሪ በርግጥ በጥንካሪ አለመስራቱ ነገርግን በቀጣይ ቅርስን በመጠበቅ ሥራ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

Äthiopien - Fossil Lucy
ምስል Getty Images

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት በ UNESCO ስር ኢትዮጵያ ዘጠኝ ታሪካዊ ቅርሶችን በማስገዘብ ከአፍሪቃ የመጀመርያያዋ ሀገር መሆንዋ ይታወቃል። የማንነት መታወቅያ፤ የግል ታሪክ መግለጫ የሆነዉን ቅርስን መጠበቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት ይመስለናል። ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ