1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የኤቦላ ተኀዋሲ ሥርጭት ምዕራብ አፍሪቃ

ሰኞ፣ ነሐሴ 12 2006

የኤቦላ ተኀዋሲ ወይም ቫይረስ» መዛመት እስካሁን ከታሰበዉ በላይ አስከፊ ነዉ ሲል የዓለም የጤና ድርጅት «WHO» ባለፈዉ ሳምንት ማስጠንቀቅያ ማዉጣቱ ይታወቃል። በምዕራብ አፍሪቃ በአሁኑ ወቅት በኤቦላ ቫይረስ የተያዙ አልያም በበሽታዉ የሞቱት ቁጥር በርግጥ ስንት እንደሆን መናገር አዳጋች ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/1CwY0
Ebola West Point Slum Infizierte verlassen Isolierstation
ምስል John Moore/Getty Images

ተኅዋሲዉ በታየባቸዉ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት ሥርጭቱን መቆጣጠር እንዳልተቻለ እየተነገረ ነዉ። በላይቤሪያ መዲና ሞንሮቭያ ዌስት ፖይንት በተሰኘ ትፍግፍግ ባለ የድሆች መንደር፤ አካባቢ ነዉ በሃገሪቱ በኤቦላ ተኀዋሲ የተያዘ ህመምተኛ እንደሞተ የተነገረዉ። ድስቁስ ያሉ የቆርቆሮ ቤቶች ያሉበት ይህ አካባቢ እጅግ ፅዳት የጎደለዉ የቆሳሻ ፍሳሽ በየቦታዉ ታቁሮ የሚገኝበትም ነዉ። የአካባቢዉ መዘጋጃ ቤት በኤቮላ የሞተን ሰዉ አስክሪን ለመዉሰድ ቦታዉ ላይ ሲገኝ፤ የኤቦላ ሥርጭትን ለመግታት፤ ዊስት ፖይንት የተባለዉን አካባቢም መራቅ እንደሚያስፈልግ ነበር በሞንሮቭያ ብዙሃን መገናኛዎች ይፋ የተደረገዉ። ይህን ተከትሎ ትናንት እሁድ አመሻሹ ላይ በኤቦላ የተያዙና የተጠረጠሩ ህመምተኞች ህክምና እንዲከታተሉበት የተደረገዉ ማዕከል፤ ማለትም የቀድሞዉን ትምህርት ቤትን ታጣቂዎች በመዉረር ዘረፋ አካሄዱ፤ በመዓከሉ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ በበሽታዉ የተያዙ ተጠርጣሪዎችና በተኀዋሲዉ የተያዙ ህመምተኞች የህክምና ማዕከሉን አምልጠዉ ወጡ። የህክምና ማዕከል ሆኖ የሚያገለግለዉን የትምህርት ቤት ቅፅር ግቢን ጥሰዉ የገቡት ዘራፊዎች፤ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ሲወስዱ፤ ያዩ የህክምና ማዕከሉ የበጎ ፈቃድ ሰራተኛ፤ በማዕከሉ የነበሩ ታካሚዎች በሙሉ ማምለጣቸዉን ለፈረንሳዩ ዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሪስ አስታዉቀዋል። የማዕከሉ በመንደራቸው መገንባት ያበሳጫቸው ናቸው የተባሉት ታጣቂዎች ባደረሱት በዚህ ጥቃት፤ የማዕከሉ በሽተኞች ይጠቀሙባቸው የነበሩ አንሶላ እና ብርድ ልብሶችን ሁሉ መዘረፋቸው እንዲሁም፤ ታማሚዎቹ ማዕከሉን ጥለዉ ማምለጣቸዉ እና ከሕዝብ ጋር መቀላቀላቸዉን ተከትሎ የበሽታው ስርጭት እጅግ ይባባሳል የሚል ስጋትን አሳድሮአል።
በላይቤሪያ እስካሁን በኤቦላ ቫይረስ ሃኪሞችንና የህሙማን እና ረዳቶችን ጨምሮ 413 ሰዎች ሞተዋል። በላይበሪያ በድንበር አያግዴዉ የሃኪሞች ድርጅት የሚያገለግሉት ሊንዲስ ሁርም በላይቤርያ የኤቦላ ስርጭት ከቁጥጥር ዉጭ መሆኑን ተናግረዋል።
«በሚያሳዝን ሁኔታ በቫይረሱ የተያዙትን ታካሚዎች፤ ከሌላዉ ማህበረሰብ ነጥሎ የህክምና ክትትል እንዲደረግላቸዉ ለማድረግ ሁለቱም የህክምና ማዕከል በቂ አይደለም። በአሁኑ ወቅት የሚታየዉ ኤቦላ ተኅዋሲ መዛመት ከቁጥጥር ዉጭ ሆንዋል። በዚህም ምክንያት አንድ አዲስ እቅድ ያስፈልገናል»
በምዕራብ አፍሪቃ በሚገኙት ሶስት ሃገራት፤ ማለትም በላይቤሪያ በሴራልዮን እንዲሁም በጊኒ የኤቦላ ቫይረስ ስርጭት በስፋት ታይቶአል። የአካባቢዉ አራተኛ ሀገር በናይጀርያም በኤቮላ ተኅዋሲ 12 ሰዎች ሞተዋል። በናይጀርያ የሚገኙ የጤና ባለሞያዎች በሥራ ገበታቸዉ በኤቦላ እንዳይያዙ በመስጋት ወደ ሥራ ገበታቸዉ መሄድ ማቆማቸዉም እየተነገረ ነዉ። እንዲያም ሆኑ 500 ናይጀርያዉያን በተኀዋሲዉ የተያዙ ታማሚዎችን ለመርዳት የህክምና አሰጣጥ ትምህርት መዉሰዳቸዉ ተገልፆአል። ኬንያ በበኩልዋ ለላይቤሪያ፤ ለጊኒ እና ለሴራልዩን ተጓዦች ድንበርዋን እንደምትዘጋ ትናንት አስታዉቃለች። «የህዝቡ ጤንነት ስጋት ላይ በመዉደቁ» ሳብያ ከነዚህ ሶስት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የሚመጡ ተጓዦች ከፊታችን ማክስኞ እኩለ ለሊት ጀምሮ ወደ ሃገሪቱ እንዳይገቡ መከልከሉን የኬንያ መንግሥት አስታዉቆአል። እንዲያም ሆኖ ኬንያ ዉስጥ እስካሁን በኤቦላ በሽታ የሞተ ሰዉ አለመኖሩ ነዉ የተዘገበዉ። የኬንያ መንግስት የጉዞ እገዳዉን ይፋ ያደረገዉ የዓለም የጤና ድርጅት የ«WHO»ን ማስጠንቀቅያ ተከትሎ መሆኑም ተያይዞ ተጠቅሷል። በቅርቡ የዓለም የጤና ድርጅት፤ በኬንያ የኤቦላ ተኅዋሲ መዛመት ሊጠነክር ይችላል ሲል መግለጫ ማዉጣቱ ይታወቃል። ኬንያ መዲና የሚገኘዉ ዓለማቀፍ የአዉሮፕላን ጣብያ፤ የአካባቢዉ ሃገራት መንገደኞች የሚዘዋወሩበት ማዕከላዊ ቦታ መሆኑ ይታወቃል።

Symbolbild - Ebola in Liberia
ምስል picture-alliance/dpa
Ebola Seuche Liberia Nigeria Krankheit Epidemie
ምስል John Moore/Getty Images


አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ