1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የየመን ሁኔታ

ሐሙስ፣ የካቲት 10 2008

የየመንን ጦርነት ለመግታት ተቀናቃኝ ኃይላትን የሰላም ድርድሩ ወደ ሚካሄድበት ጠረቤዛ ዙርያ ለማምጣት ምንም ዓይነት ተስፋ የሌለዉ መሆኑን የተመድ ገለፀ። በተመድ የየመን የሰላም መልክተኛ ኢስማኢል ኦልድ ቼክ ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ በየመን ተቀናቃኞች መካከል ያለዉ ልዩነት የሰፋ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1HxXq
Jemen Aden Präsidentschaftspalast Autobombe
ምስል picture-alliance/dpa

[No title]

ዳግም ለሰላም ለድርድሩ ለመቀመጥ ተስፋ አይታይም፤ በየመን በአየርና በምድር የሚደረገዉ ጦርነት ተባብሶ ቀጥሎአል። በሌላ በኩል የየመኑን ጦርነት አልፈዉ ወደ ስዑድ አረብያ የሚገቡት ኢትዮጵያዉያን ቁጥር ጥቂት እዳልሆነ ፤ በጅዳ የሚገኘዉ ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ገልፆልናል። ባሳለፍነዉ ታህሳስ ወር የመጨረሻዉ የየመን የሰላም ድርድር በሃገሪቷ ባየለዉ ጦርነት ከተቋረጠ በኋላ ድርድሩን ዳግም ለመቀጠል ለጥር ወር ቀጠሮ ተይዞ እንደነበር ይታወቃል።

በዓረቡ ዓለም ደኃዋ መሆንዋ የሚነገርላት የመን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እዉቅና ያገኘዉ መንግሥስቷ በስዑድ አረቢያ መራሹ ጦር በመታገዝ በየመን ዉስጥ ከሚንቀሳቀሱትና በኢራን እንደሚደገፍ ከሚነገርላቸዉ ሁቲ አማፅያን ጋር ዉግያዉን አፋፍሞ እንደቀጠለ ነዉ። በተመድ የየመን የሰላም መልክተኛ ኡልድ ቼክ አህመድ በየመን በአየርም ሆነ በመሪት ለመሪት ዉግያዉ ተጠናክሮ መቀጠሉን ትናንት በሰጡት መግለጫ አዉግዘዋል። እንደ ኡልድ ቼክ አህመድ ከሁለቱም የየመን ተቀናቃኝ ኃይሎች በኩል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ምንም ዓይነት ጥረትም ሆነ ፍንጭ አይታይም። ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ እንደገለፀዉም የየመን ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶአል።

Jemen bei Taez Transport Hilfsgüter
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Alseddik

በሌላ በኩል ይላል ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ፤ በሌላ በኩል በየመን የሁቲን አማፅያን ለመደብደብ ኅብረትን ያሳባሰብችዉ ስዑድ አረብያ፤ አካባቢዉ ሃገራት ላይ «IS»ን በመዉጋት ወደ ሶርያ አቅንታለች።

በየመን የየርስ በርሱን ጦርነት አልፈዉ ወደ ርያድ የሚገቡ የኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ቁጥርም ከፍተኛ መሆኑን ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ገልጾልናል።

የየመንን ቀዉስ እየተባባሰ ነው ሲሉ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ተጠሪ ስቴፈን ብሪይን በሳምንቱ መጀመርያ ላይ አስጠንቅቀዋል። ብሬይን በመግለጫቸዉ እንዳስታወቁት የመን ዉስጥ በሚካሄደው ጦርነት ከጎርጎረሳዉያኑ 2015 ዓ,ም መጋቢት ወር ጀምሮ 6000 ሰዎች ተገድለዋል ፣35 ሺህ ሰዎች ቆስለዋል 7,6 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል 3, 4 ሚሊዮን ሕጻናት ደግሞ ት/ቤት መሄድ አልቻሉም።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ