1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢ የሆነው የባካሲ ሁኔታ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 10 2004

ናይጀሪያ በነዳጅ ዘይት፡ በጋዝ እና በአሣ ሀብት የታደለውን የባካሲን ግዛት በይፋ ለካሜሩን ከአራት ዓመታት በፊት ባስረከበችበት ድርጊት በሁለቱ ሀገራት መካከል ወደ ሀምሣ ዓመት ገደማ የቆየውን ውዝግብ አብቅታለች። የዓለም አቀፉ ድንበር ውዝግብ ተመልካች ፍርድ ቤት ግዛቱ ለካሜሩን እንዲሰጥ ብይን ያሳለፈው እአአ በ 2002 ዓም ነበር።

https://p.dw.com/p/15qVi
This picture released on November 3, 2008 shows an aerial view taken on August 2008 of a campsite located near Akwa, in bakassi's province in Cameroon where the Bakassi Freedom Fighters (BFF) had seized 10 oil workers -- seven French, two Cameroon nationals and a Tunisian -- on a French oil vessel off the Cameroon coast on October 31. The BFF's leader complained on November 3 that the Cameroon government had still not made contact over the hostages. AFP PHOTO/ CLEMENT YANGO (Photo credit should read Clement Yango/AFP/Getty Images)
ምስል AFP/Getty Images

ይሁንና፡ ራሱን እንደ ናይጀሪያዊ የሚመለከተውና ብይኑን ትክክለኛ አይደለም በሚል የተቃወመው ብዙው የግዛቱ ሕዝብ ከጥቂት ቀናት በፊት በዚሁ የባካሲ ግዛት ውስጥ የራሱን ነፃ መንግሥት አውጆዋል።

ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የቀድሞዎቹ ቅኝ ገዢዎች ብሪታንያና ጀርመን እአአ በ 1913 ዓም የደረሱትን ስምምነት መሠረት በማድረግ ነበር ከዓለም የነዳጅ ዘይትና ጋዝ ንጣፍ መካከል አሥር ከመቶው የሚገኝበትን በጊኒ ባህረ ሠላጤ ያለው የባካሲ ልሳነ ምድር ለካሜሩን እንዲሰጥ የወሰነው። ይሁንና፡ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በባካሲ ግዛት ላይ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት፡ በዚሁ ግዛት የሚኖረው የኦጎኒ ሕዝብ ምን ይፈልጋል ብሎ የሕዝቡን አስተያየት ሳይጠይቅ፡ ግዛቱ ለካሜሩን እንዲሰጥ መወሰኑ ዛሬም ከሕዝቡ ዘንድ በፍፁም ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን የግዛቱ መሪ ግርማዊ ዶክተር ኤቱሙኩኔ ዴት ገልጸዋል።
«ግዛቱ በቀድሞው ፕሬዚደንት ለካሜሩን ከተመለሰ ወዲህ ውሳኔው እንዳሳመመን ይገኛል።»

ፍርድ ቤቱ ብይኑን በ 2002 ዓም ባሳለፈበት ጊዜ ናይጀሪያ በውሳኔው ላይ ጥያቄ ማንሳት ካሰበች የአሥር ዓመት ጊዜ መስጠቱ ይታወሳል። ይኸው የጊዜ ገደብ ሊያልፍ ሦስት ወራት ቀርተውታል። በዚህም የተነሳ የናይጀሪያ ምክር ቤት የባካሲ ግዛት ለካሜሩን እንዲመለስ ውሳኔ የደረሰበትን ሂደት እንደገና መመልከት እንዲጀምር ሰሞኑን ለሀገሩ መንግሥት ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ኤቱሙኩኔ ዴት ይህን ርምጃ አሞግሰዋል።
« የናይጀሪያ መንግሥት የባካሲ ጉዳይ ገና አልተዘጋም ሲል በድፍረት ሲናገር ተሰምቶዋል። እርግጥ ይህ አነጋገር ካሁን ቀደምም በተደጋጋሚ ሰምተነዋል፤ ግን አሁን ለጉዳዩ ትኩረት እንደሰጡ ነው የተረዳነው። እኛ ካሜሩን ግዛታችንን በሕገ ወጥ መንገድ እንደያዘች ነው የሚሰማን። እና ይህንን ግዛታችን በሕገወጥ መንገድ የተያዘበትን ርምጃ ለማብቃት ሕጉ በሚፈቅድልን ዘዴ በመጠቀም የሚቻለንን ሁሉ ለማድረግ እየሞከርን ነው። »
ሁኔታዎች ይህን በመሰሉበት ጊዜ ነበር በባካሲ ግዛት የሚኖረው ጥንታዊው የኦጎኒ ሕዝብ እንደሚወክል የሚናገረው ራሱን የባካሲ ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ግንባር ብሎ የሚጠራው ቡድን የግዛቱን ነፃነት እአአ ነሀሴ ሁለት፡ 2012 ዓም ያወጀው። ብይኑ በተላለፈበትና ግዛቱ ለካሜሩን ከተመለሰ በኋላ በተከተሉት ዓመታት ናይጀሪያ በብይኑ አንፃር ርምጃ ካልወሰደች በስተቀር ነፃነቱን እንደሚያወጅ በዛተው መሠረት አሁን በአባና አካባቢ መንግሥት አቋቁሞዋል፤ ይህንኑ ርምጃውንም እስከመጨረሻ ለማስከበር እንደሚታገል ካስታወቀ ወዲህ የካሜሩን መንግሥት ባካባቢው ሁከት እንዳይነሳ በመስጋት በስፍራው ጦሩን አከማችቶዋል። የቡድኑ የነፃነት እወጃ ውሳኔ ባካባቢው የሚታየውን ውጥረት እንዳካረረው የገለጹት የግዛቱ መሪ ግርማዊ ዶክተር ኤቱሙኩኔ በወቅቱ በዚሁ አካባቢ የተፈጠረው አሳሳቢ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ተፅዕኖ ለማሳረፍ በመሞከር ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፤ ግን፡ ይህ ጥረታቸው መሳካቱን ይጠራጠሩታል። ምክንያቱም፡
« ያካባቢው ወጣቶቹ አወዛጋቢውን ግዛት እንደማይለቁ አስጠንቅቀዋል። ምንም ያስቡ ምን እኔ ዕቅዳቸውን ተግባራዊ እንዳያደርጉ ማዘች አልችልም። ማንንም አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ላዝ አልችልም። »
ነፃነቱን ያወጀው ቡድን አባላት እንደሚሉት፡ የባካሲ ሕዝብ መብት አሁንም እየተረገጠ ነው።
« ግዛቱ ለካሜሩን ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮ በናይጀሪያ እና በካሜሩን መንግሥታት በደል እየተፈፀመብን ነው። በካሜሩን ለምሳሌ አንዳንዶች መክፈል የሌለባቸውን ቀረጥ በግድ እንዲከፍሉ መደረጉንም ሰምተናል። እና ኑሮ እጅግ ከብዷቸዋል። »
በናይጀሪያ እና በካሜሩን መካከል በባካሲ የግዛት ባለቤትነት ጥያቄ ሰበብ ወደ ሀምሣ ዓመት ገደማ ያህል በቀጠለው ውዝግብ በርካቶች ተገድለዋል።

An unidentified Nigerian soldier walks along a street in Archibong, a disputed area of the southern Bakassi Peninsula, Nigeria, Sunday, Aug. 13, 2006. Nigeria has begun withdrawing thousands of troops from a disputed border region with Cameroon in line with a U.N. ruling, officials said Saturday. (AP Photo/George Osodi)
ምስል AP
A Nigerian police officer walk pass a poster of Governor Umaru Yar'Adua's who is a leading presidential candidate at the venue of the People's Democratic Party (PDP) primary elections in Abuja, Nigeria, Saturday, Dec. 16, 2006. Nigeria's ruling party was voting Saturday to choose its presidential candidate for April elections, with the governor of a northern state emerging a front-runner in a dozen-strong field.
ምስል AP

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ