1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አስተያየት ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጽደቅ

ዓርብ፣ የካቲት 23 2010

ዶቼቬለ አስተያየቱን የጠየቀው በኦሮምያ ተቃውሞ ከሚያካሂዱት ቄሮዎች ወይም ወጣቶች አንዱ ይህን መሰሉ ድንጋጌ በይፋ ሳይታወጅ በፊትም ሀገሪቱ በመሰል አስተዳደር ስር ነበር የቆየችው አዲስ ነገር የለም ብሏል። ወጣቱ እንደሚለው ምንም እንኳን ክልከላ እና ገደቡ ተቃውሞን የማስቀረት ዓላማ ቢኖረውም ተቃውሞውን ግን ሊያስቀር አይችልም።

https://p.dw.com/p/2tbIM
Äthiopien Tote bei Anti-Regierungs-Protesten in Bishoftu
ምስል DW/Y. Gegziabher

አስተያየት ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጽደቅ


የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማጽደቁ አስፈላጊ አልነበረም ሲሉ ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ተናገሩ። አስተያየት ሰጭዎቹ አዋጁ ሊያመጣ የሚችለው በጎ ለውጥ እንደማይኖር ይልቁንም ቀውሱን ያባባሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። እሥካሁን የሚደረገውን ተቃውሞ ለተወሰነ ጊዜ ጋብ እንዲል ቢያደርግ እንጂ ሊገታው እንደማይችልም ገልጸዋል። 
ከዛሬ ሁለት ሳምንት በፊት ለ6 ወራት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብዙ ሲያነጋግር ቆይቷል። አዋጁ ዛሬ ከእረፍት በተጠራው በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላም ማወዛገቡ ቀጥሏል። ዛሬ ምክር ቤቱ አዋጁን ያጸደቀበት ቁጥር በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የተለያየ አሀዝ ተስጥቶታል። ምክር ቤቱ በፌስቡክ ገጹ መጀመሪያ ላይ ረቂቁ በ346 የድጋፍ በ88 ተቃውሞ እና በ7 ድምጸ ተአቅቦ መጽደቁን ዘግቦ ነበር። ይህንኑ ቁጥር የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የምክር ቤቱ ውሳኔ አድርገው ዘግበዋል። ኃላ ላይ ግን ምክር ቤቱ ባወጣው ሌላ ዘገባ ደንቡ በ395 ድጋፍ በ88 ተቃውሞ እና በ7 ድምጸ ተአቅቦ መጽደቁን አስታውቋል። ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ ላካሄዱት የምክርቤት አባላት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ አዋጁ የተደነገገው ሕገ መንግሥቱን እና ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል መሆኑን ይገልጻል። ተቃዋሚው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ በምህጻሩ ኦፌኮ እንደሚለው አዋጁ ህገ መንግሥቱን ከማስከበር ይልቅ በተቃራኒው ሀገሪቱን አለመረጋጋት ውስጥ የሚከት ነው ይላል። የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ 
«በእውነቱ ህገ መንግሥትን የሚያደናቅፍ፣ለዚህ የሚያበቃ ምክንያትም የለም፤ሆን ተብሎ የተደረገ ነው። እና ስለዚህየሀገሪቷን ሰላም ለማደፍረስ የተደረገ ነውና ትክክል አይደለም ብለናል። አሁንም ምልክት አይተናል። ለወደፊትም ሰላም አያመጣም።መረጋጋትን የሚያመጣ አይደለም።»
ዶቼቬለ አስተያየቱን የጠየቀው በኦሮምያ ተቃውሞ ከሚያካሂዱት ቄሮዎች ወይም ወጣቶች አንዱ ይህን መሰሉ ድንጋጌ በይፋ ሳይታወጅ በፊትም ሀገሪቱ በመሰል አስተዳደር ስር ነበር የቆየችው፤ አዲስ ነገር የለም ብሏል። ወጣቱ እንደሚለው ምንም እንኳን ክልከላ እና ገደቡ ተቃውሞን የማስቀረት ዓላማ ቢኖረውም ተቃውሞውን ግን ሊያስቀር አይችልም። 
«ህዝቡ መፍራት ትቷል ። በተፈጥሮ ያለሽ ነጻነት የምትነፈጊ ከሆነ የህይወት ትርጉሙ ምንድነው? ብንሞት ነው የምንመርጠው። ስለዚህ ብንሞትም ተቃውሞውን ወደ ኃላ የሚመልሰው ዓይነት አይደለም። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጸደቀ አልጸደቀ ምንም አዲስ ነገር የለም። ከትናንትናው የተለየ ነገር የለም። እና ተቃውሞው ይቀጥላል። ትንሽ ለጊዜው ለአንድ ሁለት ሳምንት ወይ ለአንድ ወር ያህል ጋብ ሊል ይችላል፤ ህዝቡ አቅሙን እስኪያደራጅ ድረስ ማለት ነው። ከዚያ ውጭ ግን ተቃውሞው ይቆማል የሚል ግምት የለኝም። 
የሰሜን ወሎ ነዋሪ የሆነው ሌላ ወጣት ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከህዝቡ የለውጥ ጥያቄ ጋር አይሄድም ይላል። በርሱ አስተያየት አዋጁ ተጨማሪ ጥፋት ከማስከተል በስተቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። 
«አገሪቱ አሁን አንድ አካባቢ ወይም አንድ ቦታ ላይ አይደለም ረብሻ እየተነሳ ያለው፤ ተቃውሞ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ የሚካሄደው። መላው ህዝቡ ተነስቶ አሁን አመራሩ ይበቃናል ሌላ አዲስ ለውጥ እንፈልጋለን፤ እያለ ነው ያለው። በዚህ ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ምን ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ህዝቡ በቃን ብሎ ከተነሳ አስቸኳይ ጊዜ ቢታወጅ ምንም ለውጥ እኮ አያመጣም። ከማስገደል እና ከማለቅ ውጭ ምንም ሌላ መፍትሄ የለውም። መሮታል ህዝቡ አሁን በቅቶታል።
የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ የሰዎችን መብት የሚገድብ ያሉትን አዋጅ ያጸደቁትን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በታሪክ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም ብለዋል። 
« አዋጁ የሰብዓዊ መብትን የሚደፍር ነው። የሰዎችን ከቦታ ቦታ መዘዋወርንም የመሰብሰብን የመናገርን በጠቅላላ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን መበት የሚገድብ ዓይነት ነገር ነው። እና ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን የህዝብ ተወካይ ነኝ ብለው ይህንን አዋጅ ያጸደቁት ሰዎች ታሪክ ይጠይቃቸዋል። አሁንም እየፈሰሰ ያለው ደም ያገሬው ሰው ነው። በሀገር ሀብት የተገዛ ጥይት ነው። እና የህዝብ መተላለቁ በጣም የሚያሳዝን ነው። ገዳዩም ኢትዮጵያዊ ነው። የሚሞተውም  ኢትዮጵያ ነው።»
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስቀመጣቸውን ክልከላዎች እና ገደቦችን በሚጥሱ ሰዎች ላይ ላይ የህግ አስከባሪ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንደሚችሉ ተደንግጓል። ይህ ማስጠንቀቂያ ግን የኦሮምያው ወጣት  እንደሚለው ወጣቱን ከተቃውሞ እንዲያፈገፍግ አያደርገውም።  
«ቄሮ አደባባይ ሲወጣ አደጋ አይመጣም በሰላም ወጥቼ እመለሳለሁ ብሎ አይደለም። ለሚመጣው ትውልድ ነጻነቱን ለማውረስ ነጻነት ለማምጣት ብሎ ነው። ህይወቱን እየሰዋ ያለው እንጂ ወጣቱ ህይወቱን እንደሚያጣ ጠፍቶት አይደለም።»
ኂሩት መለሰ

Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV
ምስል picture alliance/AP Photo/ltomlinson
Äthiopien Proteste | Mulatu Gamachu
ምስል DW/M. Yonas Bula

ነጋሽ መሐመድ