1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሽከርካሪ አልባ መኪኖች

Eshete Bekeleረቡዕ፣ መስከረም 12 2008

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ዓለም ከተመለከተቻቸው አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች አሽከርካሪ አልባ መኪኖች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ምንም እንኳ መኪኖቹ ከሙከራ ተሻግረው ግልጋሎት መስጠት ባይጀምሩም ግዙፍ የተሽከርካሪ አምራቾችና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን እሽቅድድም ውስጥ ከትተዋል።

https://p.dw.com/p/1Gbyj
IAA 2015 Daimler Auto ohne Fahrer
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Probst

አሽከርካሪ አልባ መኪኖች

ሜርሴዲስ፤ቢኤምደብሊውና ቴስላን የመሳሰሉ ኩባንያዎች በውስብስብ ቴክኖሎጂ ራሳቸውን የሚዘውሩ ተሽከርካሪዎችን ይፋ አድርገዋል። መኪኖቹ አዳዲስ ማሻሻያዎችና ማስተካከያዎች እየተደረገላቸዉ በጎዳናዎች ላይ ለሙከራ እየተሽከረከሩ ነው።

አሽከርካሪ አልባ መኪኖችን ለማምረት ደፋ ቀና የሚሉት ግን የተሽከርካሪ አምራች ኩባንያዎች ብቻ አይደሉም። እሽቅድድሙን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከተቀላቀሉት ሰነባበቱ። የአሜሪካው ጉግል ኩባንያ በዚህ አመት በካሊፎርኒያ ጎዳናዎች አሽከርካሪ አልባ መኪኖችን ሊፈትሽ አቅዷል። አፕል ‘ቲታን’ሲል የሰየማቸውን ቅንጡ መኪኖች ከሶስት አመታት በኋላ ለገበያ ለማቅረብ አስቧል።

ግዙፎቹ ኩባንያዎች በጋራም ይሁን በጥምረት ሊያመርቷቸው ያቀዷቸው አሽከርካሪ አልባ መኪኖች በተሽከርካሪ ምርትና ቴክኖሎጂ ላይ አብዮት እንደሚያስነሱ እየተተነበየላቸው ነው። አዳዲሶቹ መኪኖች የሰው ልጅ ከመሪ፤ፍሬን፤የጎን እና የውስጥ መስታወት ጋር ያለውን ግንኙነት ይቀይራሉ። በሚንቀሳቀሱባቸው ጎዳናዎች የሌሎች ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ፣ እግረኞችና የመንገድ መብራቶችን ይቆጣጠራሉ። የሃይል ፍጆታቸውም በኤሌክትሪክ ይቀየራል። አንዲት አነስተኛ ቁልፍ በመጫን ሞተራቸው የሚነሳ ሲሆን በጉዟቸው ወቅት እንደ አስፈላጊነቱና በተፈቀደው አግባብ ፍጥነታቸውን ይቀንሳሉ፤ይጨምራሉ። ሜርሴዲስ ኤፍ ኦ 15 (Mercedes-Benz F 015) በኤሌክትሪክ የሚሰራ፤ከካርቦን ፋይበር፤ፕላስቲክና አልሙኒየም የተበጀ ቅንጡ ተሽከርካሪ ነው። መኪናው የሙከራ ጊዜው ተጠናቅቆ ለገበያ ባይቀርብም ገና ካሁኑ አድናቆት ጎርፎለታል። በጀርመኑ የመኪና አምራች ዳይምለር ኩባንያ ተመራማሪ የሆኑት አሌክሳንደር ማንኮቭስኪ ተሽከርካሪውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ኢንጂኔር ናቸው።

Google self-driving car
ምስል Getty Images

«ይህ የወደፊት ርዕያችንን ጠንቅቀው ከሚያመለክቱ መኪናዎች አንዱ ነው። የከተማ ህይወት፣የራሳችን ህይወት ምን እንደሚመስል ጥቆማ ይሰጣል። ይህ የመፃዒው ዘመን የማዕዘን ድንጋይ ነው።»

ሜርሴዲስ ኤፍ ኦ 15 እውነትም የማዕዘን ድንጋይ -ከትናንት ይልቅ የነገ መኪና ። መቶ ሰማኒያ ዲግሪ የሚሽከረከሩ ወንበሮችና ሰፋፊ ስክሪኖች የተገጠሙለት መኪና ደፍረው ለሚገዙት እንደ ቢሮና መዝናኛ ያገለግላል ተብሎለታል።ከመጓጓዣ ይልቅ ተንቀሳቃሽ መኖሪያ የተባለለት ሜርሴዲስ ኤፍ ኦ 15 ከእግረኞች ጋር መነጋገር ሁሉ ይችላል።

«ይህ መኪና ከፊትና ከኋላ ፍላጎቱን የሚያሳውቅባቸው የመብራት ምልክቶች አሉት። ከእግረኛው ጋር መግባባት ይችላል። በመንገዱ ላይ እግረኛ ከመጣ ለማለፍ ምቹ መሆኑን ያሳውቃል። አሊያም ለእግረኛው ለማቋረጥ ምቹ ካልሆነ አታቋርጥ ወይም አደገኛ ነው የሚል መልዕት ይሰጣል።»

አሽከርካሪ አልባ መኪኖች በባለሙያዎቹ ዘንድ የሮቦት መኪና (ሮቦ ካርስ) እየተባሉ ይጠራሉ። መኪኖቹ ለገበያ ቀርበው በትልልቅ ከተሞች ሽር ብትን ከማለታቸው በፊት ግን የብቃት ማረጋገጫ ማግኘት ይኖርባቸዋል። የብቃት ማረጋገጫውን የማግኘቱ ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ የሚሆን አይመስልም። ለዚህም ይመስላል መኪናዎቹን ለገበያ ለማቅረብ ደፋ ቀና የሚሉት ኩባንያዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎች ማሻሻያዎችና ለውጦች የሚያደርጉት። የዳይምለር ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዲተር ሴትሸ

«ከሰላሳ አመታት በፊት የእነዚህን መኪኖች ንድፍ እየተመለከትን እናልም ነበር። አሁን ልናሳካው ተቃርበናል። ቢሆንም መኪናውን የፈጠረው ኩባንያ የእኛ ነው። ስለዚህ ከዚህ የበለጠ ልናሳድገው ይገባል።»

በአሽከርካሪ አልባዎቹ መኪኖች በጉዞ ወቅት እርስ በርስና ከእግረኞች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ከመንገድ አጠቃቀም መመሪያዎችና ከመንገደኛና ተሳፋሪ ደህንነት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶታል። ማርቲና ማራ በመጪው ዘመን ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ባደረገው አርስ ኤሌክትሮኒካ ፊውቸርላብ (Ars Electronica Futurelab) የተሰኘ ኩባንያ የሰውና ኮምፒውተር ግንኙነትን ያጠናሉ።

«የወደፊቱ አሽከርካሪ አልባ መኪና በመንገድ ላይ በአካባቢው ላሉ ሰዎች ራሱን እያሽከረከረ ይሁን አሊያም በሾፌር እየተነዳ ሊያሳውቅ ይገባል። ህጻን ልጅ እንኳ ቢሆን ተመልክቶት የሮቦት መኪና እንዳየውና እንዳላየው በአጭር ጊዜ ማወቅ መቻል አለበት።»

DW Shift Mobilität der Zukunft
ምስል DW

መጪው ጊዜ የሰው ልጅ በጎበዝ አሽከርካሪነቱ የሚወደስበት ላይሆን ይችላል። በቴክኖሎጂ ፍቅር የተለከፉትና የሮቦት መኪኖችን አገልግሎት መጀመር የሚጠባበቁ ባለሙያዎች ሰዎች አስቀያሚ አሽከርካሪዎች ናቸው ሲሉ ይደመጣል። መጠጥ፤እየነዱ ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም፤ድካምና ዝንጉነት የሰዎች መገለጫዎች ናቸው።ለማሽከርከርም ቢሆን የተለየ ክህሎት አይጠይቅም።

በሙከራና ምርምር ላይ የሚገኙት መኪኖች ሁሉ ራሳቸውን የሚያሽከረክሩ አይደሉም። አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ መንገደኛው ተሽከርካሪውን የሚቆጣጠርበት ማቆም፤አቅጣጫ ማስቀየር፤ማፍጠን እና በዝግታ መንዳት የሚችልባቸው ቴክኖሎጂዎች አሉ። የሙከራ ጊዜያቸው ተጠናቆ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ሲያሟሉ ከ10 ሚሊዮን በላይ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች ግልጋሎት ላይ ይውላሉ ተብሎ ይጠበቃል። መኪናዎቹ ለአገልግሎት የሚበቁበት የህግ አግባብና የመድን ጉዳይ ግን አሁንም መፍትሄ አላገኘም። ለሙከራ ጉዞ እንኳ ፈቃድ የከለከሉ የአውሮጳና አሜሪካ ከተሞች አልጠፉም።

አሽከርካሪ አልባዎቹ መኪኖች የሙከራ ሂደት ግን ያለምንም እንከን የተካሄደ አይደለም። የጉግል ኩባንያ ለሚሞክራቸው ተሽከርካሪዎች የሶፍትዌር ስራዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን ቀሪ የመኪና አካል ስራዎች ውል ከገባላቸው 35 ኩባንያዎች ይቀበላል። ከእነዚህ መካከል የጃፓኑ ቶታል ፒረስና የጀርመኑ አውዲ ቲቲ ይጠቀሳሉ። ኩባንያው የአሽከርካሪ አልባ መኪኖችን የሙከራ ጉዞ ከጀመረበት ከ2012-2015 ዓ.ም. ባሉት አመታት በ23 ተሽከርካሪዎቹ ላይ 14 አነስተኛ አደጋዎች ገጥመውታል። ጉግል አደጋዎቹ የተከሰቱት መኪኖቹን ሰው በሚያሽከረክርበት ወቅት አሊያም ሌላ ተሽከርካሪ ስህተት በመፈጸሙ መሆኑን አስታውቋል። ለመሆኑ በኮምፒውተር የሚነዱት መኪኖች ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው? ፍሎሪያን ሌነርት በዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት ባደረገ የጥናት ማዕከል ተመራማሪ ናቸው።

«ራሳቸውን ማሽከርከር የሚችሉት መኪኖች የሰዎችን ደህንነት ማሳደግ እንደሚችሉ አምናለሁ። ሰዎች ጥሩ አሽከርካሪዎች አይደሉም። ብዙ አደጋዎች የሚከሰቱት በሾፌሮች ስህተት ነው። በኮምፒውተር የሚታገዙት መኪኖች ያለምንም ጣልቃ ገብነት በጉዞው ላይ ብቻ በማተኮር የደህንነትን ጉዳይ ማሳደግ ይችላሉ።»

በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ የትዕይንት መድረኮች ራሳቸውን ማሽከርከር የሚችሉት መኪኖች ከፍተኛ ትኩረት እያገኙ ነው። የመኪኖቹ ፍላጎትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሆነ ይነገራል። በሙከራ ላይ የሚገኙት የአውዲ መኪኖች ስራ ላይ ሲውሉ መንገደኞች የሚፈልጓቸውን መረጃዎች በቀላሉ ማግኘት የሚችሉባቸው የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ተጭነውለታል። የቢኤምደብሊው መኪና ራሱ ከአገልግሎት በፊትና በኋላ የመቆሚያ ቦታውን ይመርጣል። ያመቻቻል። ያቆማል። አስፈላጊ ሲሆን ከባለቤቱ በተጨማሪ በራሱ ጊዜ ተንቀሳቅሶ ለሌሎች ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል።ኡልሪሽ ሐከንበርግ የአውዲ የምርምር ኃላፊ ናቸው።

«አሁን አሁን ደንበኞቻችን በመኪናዎቻቸው ውስጥም ሆነው እርስ በርስ መገናኘት ይፈልጋሉ። በመኪናዎቻቸው ውስጥ ሆነው የሚፈልጉትን መረጃ ሁሉ ማግኘት ይፈልጋሉ። ያንን ለማቅረብ እየተጋን ነው።»

Bildergalerie - fahrerlose Autos
ምስል picture-alliance/dpa/Google

በኮምፒውተርና ውስብስብ ሶፍትዌሮች የሚንቀሳቀሱትና ከቀሪው ዓለምና እርስ በርስ በኢንተርኔት የተሳሰሩት አሽከርካሪ አልባ መኪኖች በሶስተኛ ወገን ጥቃት ቢደርስባቸውስ? መኪኖቹን የሚቆጣጠሩት ፕሮግራሞች በሰርሳሪዎች ጥቃት ደርሶባቸው ከቁጥጥር ውጪ ቢሆኑ? የጉዞ አቅጣጫ ቢቀየር አሊያም መቆም ባይችል? እነዚህ በበይነ-መረብ ደህንነት ባለሙያዎች የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው። መኪኖቹን ለማምረት ደፋ ቀና የሚሉት ኩባንያዎችም ይሁኑ ባለሙያዎች ለእነዚህ ስጋቶች ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ቢያደርጉም ተጠራጣሪዎች አልጠፉም። ተመራማሪው ፍሎሪያን ሌነርት አሽከርካሪ አልባ መኪኖች ላይ የሚነሳው ጥያቄ ትኩረት እንደሚያሻው ይስማማሉ። ነገር ግን ለችግሮቹ መፍትሄ በስጠት በርካታ ጠቀሜታ እንደሚገኝ ያምናሉ።

«ብዙ ሰዎች መኪና በማሽከርከር ይደሰታሉ። አዲሱ ቴክኖሎጂ ስጋቶችም አላጡትም። ይሁንና ለችግሮቹ መፍትሄ አይጠፋም። እነዚህ መኪኖች የመንጃ ፈቃዳቸውን ላልያዙ፤ለሸመገሉ ወይም የአካል ጉዳት ላለባቸው ሰዎች ትልቅ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል። ስራ ለሚበዛባቸው እና ለደከማቸውም እንዲሁ። የከተሞችን የመንገድ አጠቃቀምም መሰረታዊ በሆነ መንገድ ይቀይራሉ።»

ለጊዜው የጉግልና፤አፕል፤ቢኤም ደብሊው፤ ሜርሴዲስ ቤንዝ፤አውዲንና ቴስላ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች እውን ሆነዋል። መኪኖቹ አስፈላጊውን ቅድመ-ሁኔታና የጥራት ማረጋገጫ አሟልተው ለገበያ ባይቀርቡም ለመግዛት የተዘጋጁት ግን በርካታ ናቸው። የተንደላቀቁት የአዲሱ ዘመን መኪኖች ዋጋ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚቀመስ አይመስልም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ