1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አብይ ለኢትዮጵያ ቀውስ መፍትሔ ያገኙ ይሆን?

ሐሙስ፣ መጋቢት 20 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቺዎች ዶክተር አብይ አሕመድ ጠቅላይ ምኒስትር ሆነው ሲሾሙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲሽሩ ይሻሉ። ሊቀ-መንበር አድርጎ የመረጣቸው ኢሕአዴግ በአንጻሩ አዋጁ የተደነገገበትን ጊዜ ያክል ይቆያል ብሏል። ይኸ ዶክተር አብይ ከሚፈተኑባቸው በርካታ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አንዱ ነው።

https://p.dw.com/p/2vDU1
Äthiopien Abiy Ahmed OPDO
ምስል Abdulbasit Abdulsemed

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጉዳይ ከፈተናዎቻቸው ቀዳሚው ነው

በመጪው ሰኞ የጠቅላይ ምኒስትርነት ቦታውን ከአቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ይረከባሉ ተብለው የሚጠበቁት ዶክተር አብይ አሕመድ ሁለት ፅንፎች ይጠብቋቸዋል። በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት የኢሕአዴግ ጥብቅ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር እና ገፍቶ የመጣ የሕዝብ ጥያቄ።

ጥያቄዎቹ የከረሙ ቢሆኑም እንኳ ታዛቢዎች እንደሚያምኑት ኢሕአዴግ ሲያድበሰብሳቸው ከርሞ አገሪቱን ዛሬ ወዳለችበት ቀውስ አድርሰዋታል። የአማራ ተቃውሞን በማስተባበር እና ሥርዓቱን በመተቸት የሚታወቁት አቶ አቻምየለህ ታምሩ ገዢው ግንባር "ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሕአዴግ ነው ይላል፤ በምርጫ ተወዳድሮ አሸንፎ ይቺን አገር የመምራት ኃላፊነት የተረከበው ኢሕአዴግ ነው፤ ተወዳድሮ ያሸነፈው የኢሕአዴግ ፕሮግራም ነው" በመግለጫ ማለቱን ጠቅሰው ከዶ/ር አብይ ግለሰባዊ አመራር ለውጥ መጠበቅ ፈታኝ መሆኑን ይናገራሉ።

"አንድ ግለሰብ ከፊት ቢመጣም እስካሁን ድረስ ስንጨቆንበት፣ ስንጎዳበት፣ ስንሞትበት፣ ስንገደልበት የነበረው ኢሕአዴግ የሚባለው ድርጅት ፕሮግራም ነው" የሚሉት አቶ አቻምየለሕ ሊቀ-መንበሩን የግንባሩ "ፕሮግራም አስፈፃሚ" ይሏቸዋል። "ሥርዓቱ የተዋቀረበትን ርዕዮተ-ዓለም እስካልቀየረ ድረስ የትኛውም ሰው ቢመጣ ሐይለማርያም ከነበራቸው የአሻንጉሊት ሚና ወይንም ከዚህ በፊት በመጣንበት መንገድ እየሔድን የተለየ ውጤት እናመጣለን ብዬ አልጠብቅም" ሲሉ አቋማቸውን ያስረዳሉ።

EPRDF Logo

ዶ/ር አብይ "የሚመረጡበት ቦታ እና የሚረከቡት ሥልጣን በሕግ አንፃር ሲታይ ትልቅ ነው" የሚሉት የሕግ ባለሙያው ዶ/ር ጸጋዬ አራርሳ ናቸው። የሕሊና ነፃነት፣ ጥሩ የአመራር ብቃት፣ የተሟል ተክለ-ስብዕና፣ የራሱ ርዕይ ያለው ሰው ከሆነ መጠነኛ የሆነ የኢሕአዴግን ፕሮግራም ይዞ በራሱ ሕልም እና ቅኝት ለመሔድ የሚችል ሰው ከመጣ ለውጡን ለማምጣት ብቁ ርቀት ለመሔድ ይችላል" ሲሉ ይናገራሉ። ያ ሰው ዶ/ር አብይ አሕመድ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተስፋ አላቸው።

የሖርን አፌርስ አምደ መረብ መስራቹ ዳንኤል ብርሐነ በአንፃሩ ዶክተር አብይ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሔ ማበጀት የሚችሉት የሚመሩት ግንባር ባስቀመጠው አቅጣጫ ከተጓዙ  ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። "እንሰማ እንደነበረው ኢሕአዴግ የነበሩ ችግሮችን ገምግሞ እነዛ ላይ መስማማት ላይ እንደደረሰ ነው። በበቂ ጥልቀት አይቷቸው ከሆነ እና እነዛን ማስተካከልን እንደ አቅጣጫ ይዘው ከሆነ አዲሱ ሊቀ-መንበር የሚቀጥሉት የማስተካከል እድል ሊኖራቸው ይችላል" የሚሉት የአምደ-መረብ ጸሐፊው የከረረ ትችትም አላቸው።

"በኦሮሚያ ውስጥ ቢያንስ ባለፉት ስምንት ወራት እሳቸው እራሳቸው የኦሕዴድ ፅህፈት ቤት ኃላፊ በነበሩበት ጊዜ ትግራዮችን ጨምሮ በተለያዩ ብሔሮች ላይ ጥቃት ሲደርስ እንደነበረ እና ያም የአመራሩ ሽፋን እንደነበረው እናቃለን። ስለዚህ እኔ ቁርጠኝነቱ እና ፍላጎቱ አላቸው የሚለው ያጠራጥረኛል" ይላሉ አቶ ዳንኤል። 

የሕግ ባለሙያው ዶክተር ጸጋዬ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ፋታ ያሻታል። "አገሪቱ ባስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ትገኛለች፤ ሰላም የለም፤ የድንበር ጦርነት አለ፤ መፈናቀል አለ፤ መደበኛው የሲቪል አስተዳደር በተለያዩ ቦታዎች በተለያየ ደረጃ ተገድቧል" የሚሉት የሕግ ባለሙያው ሰላም ማስፈን እና መረጋጋትን መፍጠር ቀዳሚው ሥራ ሊሆን ይገባል የሚል እምነት አላቸው።  በአገሪቱ የረበበውን ሥጋት ለመቅረፍ የሕግ ባለሙያው "ሕገ-መንግሥታዊ ያልሆነ፣ ምንም ሕጋዊ መሰረት የሌለው" የሚሉትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማንሳት አሊያም በመሻር ሊጀመር ይገባል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳቱ ነገር ሰኞ ጠቅላይ ምኒስትር ለሚሆኑት ለዶክተር አብይ ፈታኝ የቤት ሥራ ይመስላል። በተለያዩ ከተሞች ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች እና እንደ ዶ/ር ጸጋዬ ያሉ የኢሕአዴግ ተቺዎች እንዲነሳ መሻታቸውን በግልፅ ተናግረዋል። የኢሕአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ግን አዋጁ የተደነገገበትን ጊዜ ያክል ኢትዮጵያ እንደምትተዳደርበት ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ