1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቴንስ-የግሪክ መንግሥት እርምጃ እና አበዳሪዎች

ማክሰኞ፣ መስከረም 9 2004

የግሪክ መንግሥት ለመንግሥት አገልግሎት የሚያወጣዉን ገንዘብ መጠን ይበልጥ ለመቀነስ ዛሬ ቃል ገባ።ምጣኔ ሐብቷ ለከሰረዉ ለግሪክ ርዳታ የሚሰጡ መንግሥታትና ተቋማት የግሪክ መንግሥት ወጪዉን እንዲቀነስና የመዋቅር ለዉጥ እንዲያደርግ ከፍተኛ ግፊት እያደረጉበት ነዉ።

https://p.dw.com/p/RmqL
የግሪክ ጠ/ሚምስል dapd

የሐገሪቱ የገንዘብ ሚንስቴር ዛሬ እንዳስታወቀዉ መንግሥት የሚቆጣጠራቸዉ አንዳድ መስሪያ ቤቶች ይዘጋሉ።የግሪክ መንግሥት ወጪዉን ካልቀነሰና በቀረጥ ክፍያ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ካላደረገ ተጨማሪ ብድር እንደማይሰጡት «ሰወስትዮሽ» የሚባሉት አበዳሪዎች የአዉሮጳ ሕብረት፥ የአዉሮጳ ማዕከላዊ ባንክና የአለም ገንዘብ ድርጅት በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።በግሪክ የአለም ገንዘብ ድርጅት ተጠሪ ቦብ ትራእ ትናንት እንዳሉት የግሪክ መንግሥት ቀረጥ ከመጨመር ይልቅ ቀረጥ አጭበርባሪዎችን መቆጣጠር አለበት።«በኛ አመለካከት በተወሰኑ ግብር ከፋዮች ላይ ግብር በየጊዜዉ መጨመር የለበትም።ይሕ በኢኮኖሚዉን ሆነ በፖለቲካዉ ዘላቂነት አይኖረዉም።ይሕንን ለማስወገድ በኛ እምነት በሁለት መንገድ ሊተኮርበት የሚገባ ሌላ ጉዳይ አለ።የመጀመሪያዉ የግብር ቁጥጥርን ለማጠናከር የተደረገዉ ጥረት እስካሁን ጥሩ ዉጤት ያመጣል የሚል ተስፋ አልፈጠረም።(ሁለተኛዉ) ግሪክ ታክስ አጭበርባሪዎችን ለመቆጣጠር ሁነኛ እርምጃ ሳትወስድ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለዉ ምጣኔ ሐብታዊ እርምጃ ልትወስድ አትችልም የሚል እምነት አለን።»የግሪክ የገንዘብ ሚንስትር ኢቫንጌሎስ ቬኒዜሎስ ዛሬ ማምሻቸዉን መንግሥታቸዉ ለመዉሰድ ቃል ሥለ ገባዉ እርምጃ ከአዉሮጳ ሕብረትና ከአለም ገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ጋር ይነጋገራሉ።አበዳሪ ሐገራትና ተቋማት ለግሪክ መንግሥት ስምንት ቢሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ብድር ለመስጠት ቃል ገብተዋል።ብድሩን የሚሰጡት ግን የግሪክ መንግሥት ወጪዉን ለመቀነስና ለመቆጣጠር እርምጃ መዉሰዱን አበዳሪዎች ሲያረጋግጡ ነዉ።

ነጋሽ መሃመድ
አዜብ ታደሰ