1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የኦፌኮ አመራር አባላት ታሰሩ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 15 2008

ፓርቲው በኦሮሚያ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የታሰሩት ሰዎች ቁጥር 3500 መድረሱንም አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1HTqd
Äthiopien Polizei
ምስል imago/Xinhua

የአዲስ አበባን ከተማ ከአጎራባች የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ጋር ለማስተሳሰር በሚል በመንግስት የቀረበው እቅድ ላይ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከ3500 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቋል። «ኦሮሚያ ውስጥ ባለው የህዝብ ተቃውሞ ምክንያት ብዙ አባላቶቻችንና ደጋፊዎቻችን እየተለቀሙ እየታሰሩ ነው።» ያሉት የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ነጋ አመራሮችም መታሰራቸውን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።የድርጅቱ ምክትል ዋናጸ ሓፊ አቶደ ጀኔ ጣፋ እና ቀዳሚ ምክትል ሊቀ-መንበሩን አቶ በቀለ ገርባ በተጨማሪ አምስት የወጣት አመራሮች መታሰራቸውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሓፊ አቶ በቀለ ነጋ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የ8 ዓመት ከሰባት ወራት እሥር ተበይኖባቸው በይግባኝ ለአምስት አመት ከሦስት ወራት የታሰሩትና ከጥቂት ወራት በፊት የተፈቱት አቶ በቀለ ገርባ የተያዙት ከአዳማ መኖሪያ ቤታቸው መሆኑን እና በአሁኑ ወቅት ወደ ማዕከላዊ ምርመራ መወሰዳቸውን አቶ በቀለ ነጋ ተናግረዋል። የድርጅቱ ምክትል ዋና ጸሓፊ አቶ ደጀኔ ጣፋ ደግሞ አዲስ አበባ ከመንገድ ላይ በጸጥታ ኃይሎች መወሰዳቸውን ዋና ጸሓፊው አረጋግጠዋል።አቶ በቀለ ነጋ ፓርቲውም ሆነ የፖለቲከኞቹ ቤተሰቦች ለእስሩ ምክንያት እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።

የአውሮጳ ህብረት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሰዎች መሞታቸውን ገልጦ ሁሉም ወገኖች ለልዩነቶቻቸው ሰላማዊ እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልጉ አሳስቧል። የአውሮጳ ሕብረት በመንግስት እቅድ ስጋት የገባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ማማከር እንደሚገባም ጠቁሟል።

እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ