1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንድነት ወይስ ሁለት ነት?

ሰኞ፣ ጥቅምት 17 2007

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሐገር የመምራት ሥልጣን የያዙ ይሁኑ-ለመምራት በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱ አንድነታቸዉን በነገሩን ማግስት-ሁለትነታቸዉ ፈጥጦ ሲወጣ ማየት፤ጥብቅ ወዳጅነታቸዉን አሳይተዉን ሳያበቁ ጠላትነታቸዉን ሲያረጋግጡልን መስማት በርግጥ አዲስ አይደለም።---አንድነት ተረኛ መሆኑ ይሆን?

https://p.dw.com/p/1Dcub
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የኢትዮጵያ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ-(አንድነት ባጭሩ) አንድና ሁለትነት።የተቃዋሚዉ ፓርቲ የአንድነት መሪዎች ወይም መሪነን የሚሉ ወገኖች ዉዝግብ የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሐገር የመምራት ሥልጣን የያዙ ይሁኑ-ለመምራት በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱ አንድነታቸዉን በነገሩን ማግስት-ሁለትነታቸዉ ፈጥጦ ሲወጣ ማየት፤ጥብቅ ወዳጅነታቸዉን አሳይተዉን ሳያበቁ ጠላትነታቸዉን ሲያረጋግጡልን መስማት በርግጥ አዲስ አይደለም።

UDJ PK
ምስል DW

አንድ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፖለቲከኛ «የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሁለት ሆነዉ ሰወስት የፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት ይሻሉ።» እስከማለት መድረሳቸዉን አንብበናልም።በቅርብ ዓመታት ከሕወሐት እስከ ኦነግ፤ ከቅንጅት እስከ ኦብኮ---ከሌሎችም ያየን የሰማነዉ ሌላ አይደለም።አንድነት ተረኛ መሆኑ ይሆን? የፓርቲዉ ምክትል ፕሬዝዳንትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቸኛዉ የተቃዋሚ ፓርቲ እንደራሴ አቶ ግርማ ሠይፉ አጭር መልስ አላቸዉ።«ምኞት» የሚል-ከምፀት ፈገግታ ጋር።

ቶ ግርማን በምክትል ፕሬዝዳንትነት የያዘዉን አመራር እንቃወማለን ያሉት እና ከፓርቲዉ ሰባት ዞኖች መወከላቸዉን ያስታወቁት ፖለቲከኞች ግን ሕግ ተጥሷል ባይ ናቸዉ።የምዕራብ ኢትዮጵያ የፓርቲዉ የድርጅት ጉዳይ ሐላፊ ነኝ ያሉት አቶ ብርሐኑ ፈካና

Demonstration der UDJ- Unity for Democracy and Justice Party Party in Addis Abeba, Äthiopien
ምስል DW

የቀድሞዉን የፓርቲዉን ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ግዛቸዉ ሽፈራዉን ለማነገር ሥልክ ደዉለን «እያስተማርኩ ሥለ ሆነ---» በሚል ምክንያት ቀጠሮ ሰጡን።በቀጠሩኝ ሰዓት ደወልኩ፤ ሥልካቸዉ ተይዟል።መልሼ ደወልኩ።አይመልሱም።እንደገና ደወልኩ ተይዟል፤ ደግሜም፤ አሠልሼም ደወልኩ አያነሱም----ማሽኗ----አይሰለቻትም።አኔ ግን ጊዜዬ ባከነ።በቃኝ።

የሆነዉ ግን እንዲሕ ነዉ።አምና ታሕሳስ የተሰየመዉ የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ መሪ መረጠ።ኢንጂነር ግዛቸዉ ሺፈራዉን።አዲሱ መሪ አዲስ ካቢኔ ሰየሙ።በስድስተኛ ወሩ ግን ከአዲሱ ካቢኔ አምስቱ ሥልጣን ለቀቁ።ምክንያት፤-ያኔ ሥልጣን ለቀዉ ከነበሩት አንዱ አቶ ዳንኤል ተፈራ---ይናገራሉ።

አቶ ዳንኤል አሁን የፓርቲዉ የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ናቸዉ።ከነሐሴ ጀምሮ የአንድነት፤ አንድነት-«በጥግን ግን» የቀጠለ ዓይነት ነበር።አቶ ግርማ ሰይፉ እንደሚሉት እሳቸዉን ጨምሮ የፓርቲዉ አመራር አባላት ኢንጂነር ግዛቸዉ አንድም የአብዛኛዉን አመራርና አባላት ፍላጎትና ስሜት አክብረዉ እንዲመሩ አለያም ሥልጣን እንዲለቁ ግፊት ማድረጋቸዉን ቀጠሉ።

ግፊቱ ወይም አለመግባባቱ አጉዞ አጉዞ ኢንጀነር ግዛቸዉን በፈቃዳቸዉ ሥልጣን ለቀቁ።ሌላ ተመረጠ።የኢንጂነሩን ሥልጣን መልቀቅ የተቃወሙት ፖለቲከኞች ግን ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ኢንጂነር ግዛቸዉ ሥልጣን የለቀቁት ከሐገር ዉጪ ባሉ አባላትና ደጋፊዎች በተደረገባቸዉ «ተፅዕኖ» እና «ደባ» ነዉ። አቶ ብርሐኑ ፈካና።አቶ ግርማ ግን የዉጪ ግፊት የምትለዋን አረፍተ-ነገር ኢሕአዲግ የሚወዳት ይሏታል።

አቶ ዳንኤል ደግሞ በኢንጂነር ግዛቸዉ መልቀቅ ሰበብ አዲሱን የአንድነት አመራርን ከሚወቅሱት ወገኖች አብዛኞቹን የፓርቲዉ አባላት እንኳ አይደሉም ባይ ናቸዉ።ከጀርባቸዉ ደግሞ ገዢዉ ፓርቲ አለበት።

የአቶ ግርማ አስተያየትም ተመሳሳይ ነዉ።አቶ ብርሐኑ ፈካና ግን ፕሬዝዳንት መምረጥ ያለበት ጠቅላላ ጉባኤዉ መሆን ነበረበት ባይ ናቸዉ።

አቶ ግርማ መልስ አላቸዉ።አቶ ዳንኤልም።ዉዝግቡ ከመገናኛ ዘዴዎች እንኪያ ሠላንቲያ አልፎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደርሷል።የቦርዱ ምክትል ሐላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ እንዳስታወቁት ቦርዱ ከሁለቱም ወገኖች ደብዳቤ ደርሶታል።

UDJ Presse Konferenz
ምስል DW/G. Tedla

ልዩነቱ ወይም ዉዝግቡ የተሠማዉ ተቃዋሚዉ ፓርቲ ለምርጫ በሚዘጋጅበት፤ ከሌላዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ከመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጋር ለመወሐድ የጀመረዉ ድርድር ለዉጤት መብቃት አለመብቃቱ በሚያነጋግርበት ወቅት ነዉ።አቶ ግርማ ሰይፉ እንደሚሉት ዉዝግቡ ቢኖርም ፓርቲያቸዉ ለምርጫዉም ለዉሕደቱም መዘጋጀቱ አልተቋረጠም።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ