1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንጋፋዉ የጀርመን ት/ቤትና የመጀመርያዉ ተመራቂ

ሐሙስ፣ ግንቦት 13 2007

«ኢትዮጵያዉያኖች ጀርመን ትምህርት ቤት ገብተዉ እንዲማሩ ፈቃድ አልነበረም። እንደማስበዉ መራሔ መንግሥት ሽሮደር ኢትዮጵያ በነበሩበት ጊዜ ይመስለኛል፤ ይህ ችግር አለበሚል ከኛ ከቀድሞ ተማሪዎች ተጠይቀዉ ይህ ችግር ተፈትዋል። አሁን ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ልጁን እዝያ ማስተማር ይችላል»

https://p.dw.com/p/1FTUg
Äthiopien Deutsche Schule
ለት/ቤቱ 60ኛዉ ዓመት ክብረ በዓል የቀድሞዎቹ ተማሪዎችና የአሁኖቹ በአንድ ላይምስል Conny Prehl

አንጋፋዉ የጀርመን ት/ቤትና የመጀመርያዉ ተመራቂ

የዛሬ 60 ዓመት አዲስ አበባ ከተማ ላይ የጀርመን ትምህርት ቤት በተቋቋመ በሁለተኛ ዓመቱ ከአራተኛ ክፍል ትምህርታቸዉን ጀምረዉ እዝያዉ የሁለተኛ ደረጃ ትምርታቸዉን ካጠናቀቁት የመጀመርያዎቹ ብቸኛ ሁለት ኢትዮጵያዉያን ተማሪዎች መካከል ዶክተር ካሳይ ወልደ ጊዮርጊስ የሰጡን አስተያየት ነበር። በኬሚስትሪ ትምህርት በጀርመን ሃገር የዶክትሪት ማዕረግን ያገኙት አቶ ካሳይ ወልደጊዮርጊስ ዛሬ በኢትዮጵያና በጀርመን ሃገር መካከል ድልድይን ዘርግተዉ የቀድሞዎቹን ተማሪዎች በማገናኘት በሃገራቱ መካከል ያለዉን የቆየ የባህል፣የእዉቀት ብሎም የኤኮኖሚ ትስስር ይበልጥ እንዲጠነክር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

Äthiopien Deutsche Schule
ዶክተር ካሳይ ወልደ ጊዮርጊስ-በጎርጎረሳዉያኑ 1957 ዓ,ም ትምህርታቸዉን ጀምረዉ 1968 ዓ,ም በመጀመርያነት ከትምህርት ቤቱ ተመርቀዋልምስል Conny Prehl

የአዲስ አበባዉ የጀርመን ትምህርት ቤት ከዛሬ ከስድሳ ዓመት በኋላ በምን ደረጃ ላይ ይገኝ ይሆን?በርግጥ በኢትዮጵያ ዉስጥ የጀርመንኛ ቋንቋን የሚናገር ማኅበረሰብ በርከት ብሎስይሆን?! የጀርመንን እዉቀት ቀስመዉ ኢትዮጵያዉያ ዉስጥ በማገልገል ላይ ያሉ ዜጎችስ ቁጥር ምን ያህል ይሆን። በለቱ ዝግጅታችን ስድሳ ዓመት የሆነዉን የጀርመን ትምህርት ቤት ይዘን የመጀመርያዉን የትምህርት ቤቱን ተመራቂ በእንግድነት ጋብዘናል።

«ለሕይወታችን ደስታ ሰጭዉ አሁንም ሆነ ለሚመጣዉ ልባችንን በኩራትና ደስታ የሚያስፈነድቀዉ አሁን ዛሬ ቀኑ ምንጊዜም ዘላለማዊ ነዉ ። » ስለኛ ከፍ ይበል ይላል፤

በጎርጎረሳዉያኑን 2014 ዓ,ም በተካሄደዉ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ በተለይ የጀርመንን የብዙኃን መገናኛ ያደመቀዉ « Auf uns» የተሰኘዉ የጀርመንኛ ሙዚቃ። 60 ኛ ዓመቱን ለአከበረዉ አዲስ አበባ ለሚገኘዉ የጀርመን ትምህርት ቤት መርጠነዋል፤ እዝያ ትህርታቸዉን ለጨረሱም ሆነ ለሚከታተሉት ለመምህራኑም ጭምር። የአዲስ አበባዉ የጀርመን ትምህርት ቤት ከተቋቋመበት ዓመታት ጀምሮ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ከተከታተሉት ተማሪዎች መካከል በዚሁ ትምህርት ቤት እንደ ኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር በ1960 ዓ,ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በትክክል አጠናቀዉ የተመረቁት የመጀመርያ ተማሪዎች ቁጥር አምስት ብቻ ነበር። ሁለት ኢትዮጵያዉያንና ሶስት ጀርመናዉያን። በዚያን ጊዜ ከተመረቁት ሁለት ኢትዮጵያዉያን ተማሪዎች መካከል፤ ዶክተር ካሳይ ወልደ ጊዮርጊስ አንደኛዉ ናቸዉ።

Äthiopien Deutsche Schule
የቀድሞዎቹ ተማሪዎች ለ60ኛዉ ዓመት ክብረ በዓል ት/ቤት ዉስጥ የተነሱት ፎቶምስል Conny Prehl

« እኔ አዲስ አበባ በሚገኘዉ የጀርመን ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ያጠናቀኩት በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ1968 ዓ,ም ነዉ። የዝያን ጊዜትምህርታችንን ስንጨርስ ሁለት ኢትዮጵያዉያን ብቻ ነበር የተቀሩት ሶስቱ ጀርመናዉያን ነበሩ። ከኔ ጋር ትምህርቱን የጨረሰዉ ደግሞ አስፋ ወሰን አስራተ ነበር። እና በጣም ብዙ ገንዘብ ተከፍሎ ነበር የተማርነዉ ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም አስተማሪዎቹ በሙሉ የመጡት ከዉጭ ነዉ»

ከስድሳ ዓመት በፊት አዲስ አበባ ዉስጥ ኒትዛ በሚባል ሆቴል ዉስጥ የጀመረዉ የጀርመናዉያኑ ትምርት ቤት እኛ የመጀመርያዎቹ ተማሪዎች ኩችና ዉስጥ ነበር ትህርታችን የምንከታተለዉ ሲሉ ዶክተር ካሳይ ወልደ ጊዮርጊስ ያስታዉሳሉ ።

ጀርመናዉያኑ ይህን ትምህርት ቤት አዲስ አበባ ላይ ሲያቋቁሙ በጀርመናዉያን የትምህርት ደረጃ ነዉያሉትየመጀመርያዉ የጀርመን ትምህርት ቤት ተማሪና ተመራቂ ዶክተር ካሳይ በመቀጠል «አዎ ኒዛ የሚባል ሆቴል ዉስጥ ነበር ትምህርቱ የጀመረዉ፤ መንግሥትም ጥሩ ሁኔታን አመቻችቶላቸዉ የጀርመንም መንግስት መርዳት ጀመረ፤ ትምህርቱ በኒዛ ሆቴል ቀጠለ። አስታዉሳለሁ ትምህርት እንደ ጀመርን የመማርያ ክፍላችን ኩችና ዉስጥ ነበር። እኔ መጀመርያ በፈረንሳይ ትምህርት ቤት ሕጻናት መዋያ ትምህርቴን ጀመርኩ ከዝያ የእንግሊዘኛ ቋንቋ እየጠነከረ ሲመጣ አባቴ ከእህቶቼ ጋር ናዝሪት ትምህርት ቤት አስገባን፤ ናዝሪት ትምህርት ቤት የሴቶች ተማሪ ቤት ነዉ ሲባል አባቴ እኔን ከዝያ አስወጥቶ፤ ካቴድራል በሚባል ትምህርት ቤት አስገባኝ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የምንኖርበት የቤተሰቦቼ ቤት ጀርመን ትምህርት ቤት አቅራብያ ስለነበር፤ በአባቴ አማክኝነት በአጋጣሚ ወደዚህ ትምህርት ቤት ለመግባት በቅቻለሁ።»

Äthiopien Deutsche Schule
በጎርጎረሳዉያኑ 2005 ዓ,ም ፕሬዚዳንት ሆርስት ኮለር ከባለቤታቸዉ ጋር በት/ቤቱ በእንግድነትምስል Conny Prehl

ጀርመናዉያኑ ይህን ትምህርት ቤት አዲስ አበባ ላይ ሲያቋቁሙ በጀርመን የትምህርት ደረጃ ነዉ ያሉት የመጀመርያዉ የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪና ተመራቂ ዶክተር ካሳይ ትምህርታቸዉን ሲጀምሩ ከ20 በላይ ተማሪዎች እንደነበሩምያስታዉሳሉ።

«ከአስራ አንድ ዓመት በኃላ ትምህርታችንን ስንጨርስ የቀረነዉ ሁለት ኢትዮጵያዉያን ብቻ ነበር። ብዙ ተማሪዎች ትምህርቱን ሳያጠናቅቁ የወጡ አሉ። ይህ የሆነዉ ደግሞ በቋንቋ ችግር ምክንያት ነበር። የሚገርመዉ ነገር እዝያ ትምህርት ቤት ተምረዉ ጥሩ ደረጃ የደረሱ ብዙ ተማሪዎች አሉ። ትምህርቱ በጀርመን ሃገር ካለዉ ትምህርት ቤት ጋር የተስተካከለ ነዉ። ለምሳሌ አስረኛ ክፍል ፈተና ስንፈተን ከጀርመን ሃገር አስተማሪዎች እየመጡ ነበር የሚፈትኑን። ከዝያ አይተዉ አይተዉ ይህ ትምህርት ቤት እንደ ጀርመን ሃገር ደረጃ ያለዉ ነዉ ሲሉ እዉቅና ሰጡት መሰከሩም። ታድያ በዝያን ወቅት ጀርመንኛ በአዲስ አበባም ሆነ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የሚታወቅ አልነበረም በዝያ ምክንያት ለብዙዎች ተማሪዎች ቋንቋዉ እጅግ ከብዶአቸዉ ነበር።»

Äthiopien Deutsche Schule
የመጀመርያዉ የጀርመን ትምህርት ቤት በሆቴል ኒዛምስል Conny Prehl

ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በፊት ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ ጀርመናዉያን እንደነበሩና የዛሬዉ የጀርመን ትምህርት ቤት ከመቋቋሙ ከ 28 ዓመት በፊት 1928 ዓ,ም 50 የሚሆኑ የመጀመርያዉን ሚሲዮንን መመሥረታቸዉ ዘገባዎች ያሳያሉ። ስለዚህ ጉዳይ በእዉነት ጠለቅ ብዬ የማዉቀዉ ነገር የለኝም ያሉት ዶክተር ካሳይ፤

« በእዉነቱ ጠለቅ ብዬ የማዉቀዉ ነገር የለኝም፤ግን ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በፊት ሰፋ ያለ የጀርመን የፕሮቴስታንት ማኅበረብ ነበር፤ ትምህርት ቤትም ነበራቸዉ። ጣልያንኖች ከመጡ በኃላ የራሳቸዉን የካቶሊክ ሐይማኖት ማስፋፋት ስለፈለጉ እንደዉም እንዳነበብኩት ጀርመናዉያኑ ኃብታቸዉን ሸጠዉ እንዲወጡ ነዉ ያደረጉዋቸዉ፤ ካሳም እየከፈሉም ነዉ ያስዋጡዋቸዉ። አዎ ከጦርነቱ በፊት ሰፊ የጀርመን ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነበር።»

Äthiopien Deutsche Schule
ከጎርጎረሳዊዉ 1994-1999 ዓ,ም ጀርመንን ያስተዳደሩት ሰባተኛዉ የጀርመን ፕሬዚዳንት ሮማን ሄርዞግ ት/ቤቱን ሲጎበኙምስል Conny Prehl

ጀርመናዉያን ይህን ትምህርት ቤት ሲያቋቁሙ ለልጆቻቸዉ ሲሉ ቢሆንም በመጀመርያዎቹ ዓመታት ኢትዮጵያዉያን ገብተዉ የመማር ፈቃድ ነበራቸዉ ያሉት ዶክተር ካሳይ፤ ዋናዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሥራ ጉዳይ የሚመጡ ኢትዮጵያዉያን ልጆቻቸዉን የሚያስተምሩበት ቦታ ስለሚያስፈልጋቸዉ ለነሱም ታስቦ ነዉ። ቀደም ሲል ግን በኛ ጊዜ ለጀርመናዉያኑም ለኢትዮጵያዉያኑም ለሁሉም ተማሪዎች ታስቦ ነዉ።

« ትምህርት ቤቱ ሥራዉን እንደጀመረ ብዙም ተማሪዎች አልነበሩትም፤ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ባገኘ ቁጥር ደስታዉ ነበር። ቆይቶ ቆይቶ ግን የተገነዘቡት ነገር ተማሪዎቹ ትምህርታቸዉን በጥሩ ሁኔታ እንዲያጠናቅቁ፤ ቋንቋዉንም በደንብ እንዲችሉ በትምህርት ቤቱ ህጻናት መዋያ ትምህርትና ቋንቋዉን መማር መጀመር አለባቸዉ የሚል አቅዋም ወስደዉ እንደሚመስለኝ ከጎርጎረሳዉያኑ 1972ዓ,ም ጀምሮ ተማሪዎችን ከህጻንነታቸዉ ማለት ለአንደኛ ክፍል መዘጋጃ ከሚሰጠዉ ትምህርት ክፍል መቀበል ጀመሩ። እናም ከኛ በኋላ የመጡ ተማሪዎች ከመጀመርያዉ ጀምሮ ቋንቋዉን ስለተማሩ እንደኛ የቋንቋ ችግር አልገጠማቸዉም።»

ጀርመናዉያን ይህን ትምህርት ቤት ሲያቋቁሙ ለልጆቻቸዉ መማርያ ቦታ ለማበጀት ቢሆንም ይህ ትምህርት ቤት የኢትዮጵያዉያንና የጀርመንን ግንኙነት በማጠናከር ላይ ያለ ተቋም መሆኑ እሙን ነዉ። እንድያም ሆኖ ከጀርመን ትምህርታቸዉን ጨርሰዉ ወደ ሃገር ቤት የገቡ ኢትዮጵያዉያን ወላጆችም ሆኑ በሥራ ጉዳይ ለጥቂት ዓመታትና ወራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ ወላጆች የአዲስ አበባዉ የጀርመን ትምህርት ቤት ክፍያዉ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ሲናገሩ ይሰማል። ምንም እንኳ በጀርመን ሃገር ትምህርት ነፃ ቢሆንም ቅሉ።

Äthiopien Deutsche Schule
የትምህርት ቤቱ አርማምስል Conny Prehl

በዲሲፕሊን ማለት በሥነ-ስርዓት በጠንካራ ሰራተኝነትና ሰዓት በማክበር የሚታወቁት ጀርመናዉያን፤ የዛሬ ስድሳ ዓመት አዲስ አበባ ላይ በአቋቋሙት ትምህርት ቤት በርካታ ኢትዮጵያዉያን በትምህርት አንፀዉ አስመርቀዋል። የዚሁ ትምርት ቤት የመጀመርያ ተመራቂ የሆኑት ዶክተር ካሳይ ወልደ ጊዮርጊስ ለሰጡን ቃለ ምልልሥ በማመስገን ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫዉን ማዕቀፍ በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ