አንፃራዊው የህፃናት ድህነት በጀርመን
ማክሰኞ፣ መስከረም 9 2004ማስታወቂያ
ምንም እንኳን ጀርመን ህፃናትን ተንከባክቦ በማሳደግ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣት ሀገር ብትሆንም በሃገሪቱ የኑሮ ደረጃ መመዘኛ መሰረት የድህነት ህይወት ውስጥ የሚገኙ ህፃናት ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም ። በጀርመን ፌደራል ስታስቲክስ ፅህፈት ቤት ዘገባ መሠረት ከጀርመን ህፃናት 15 በመቶ ያህሉ ማለትም ከ 6 ልጆች አንዱ በጀርመን ህብረተሰብ የኑሮ ደረጃ በአንፃራዊነት የተጎሳቆለ ኑሮ ውስጥ ይገኛል ። ለዚህ ዓይነቱ ህይወት በይበልጥ ከሚጋለጡት ህፃናት ውስጥ በተለይ በአንድ ወላጅ ማለትም በእናት ወይም በአባት ብቻ የሚያድጉ ህፃናት ይገኙበታል ። ከነዚህ ውስጥ ወደ 37 በመቶ የሚሆኑት በሀገሪቱ ለድህነት ከተቀመጠው ደረጃ በታች በሆነ ኑሮ ውስጥ እንደሚገኙ ይኽው መረጃ ያመለክታል ። በጀርመን የህፃናት ድህነት ሲባል ግር ማሰኘቱ አይቀርም ። በተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት በእንግሊዘኛው ምህፃር ዩኒሴፍ የጀርመን ቅርንጫፍ ቃል አቀባይ ሩዲ ታርኔደን ለዶቼቬለ የአማርኛው ክፍል በሰጡት ማብራሪያ በጀርመን የህፃናት ድህነት ሲባል በሶስተኛው ዓለም ከሚታወቀው ድህነት የተለየ መሆኑን አስረድተዋል ።
ሒሩት መለሠ
ተክሌ የኋላ