1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አኢቺ፤ የጃፓን ኤኮኖሚ መንኮራኩር

ሐሙስ፣ መጋቢት 15 1997

ጃፓን ማዕከላዊት ክፍለ-ሐገር አኢቺ ዋና ከተማ ናጎያ ላይ ነገ የኤክስፖ ትዕይንት ይከፈታል። ከተማይቱ በውጭው ዓለም እስካሁን ብዙም አትታወቅም።

https://p.dw.com/p/E0er

ስለ ጃፓን አስደናቂ የኤኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና የማያውቅ፤ አኩሪ ዕርምጃዋን በአርአያነት ለመውሰድ ያልከጀለም አዳጊ አገር የለም። እርግጥ ስለ ጃፓን ሲወራ ብዙዎቻችን የምናስታውሰው ምናልባት ዓለምአቀፍ የፊናንስ ማዕከል የሆነችውን ዋና ከተማይቱን ቶኪዮን ወይም ዮኮሃማን፤ አለበለዚያም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአቶም ቦምብ የወደሙትን ሂሮሺማንና ናጋሣኪን ነው።
ግን ጃፓን ሃያል የኤኮኖሚ ዕድገት መሠረት የሆኑ ዓለም እምብዛም የማያውቃቸው ሌሎች አካባቢዎችም አሏት። ከነዚሁ አንዷ ለምሳሌ የሣሙራዮች ምንጭ የሆነችውና በኢንዱስትሪ ምርቷ አቻ የሌላት ማዕከላዊቱ አኢቺ ክፍለ-ሐገር ናት። ነገ አርብ በዚህችው ክፍለ-ሐገር ዋና ከተማ ናጎያ ዓለምአቀፉ የኤክስፖ ትዕይንት ይከፈታል። ለዚህ ትኩረታችን መንስዔ የሆነንም ይሄው ዝግጅት ነው።

በትዕይንቱ ከ 120 የሚበልጡ ሃገራት አምራቾች አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና ግኝቶችን የሚያስተዋውቁ ሲሆን 15 ሚሊዮን ጎብኚዎች እንደሚገኙም ነው የሚጠበቀው። ይህ ደግሞ “የጃፓን ኤኮኖሚ አንቀሳቃሽ መንኮራኩር” የሚል ቅጽል የተሰጠውን አካባቢ በሰፊው ለዓለም እንደሚያስተዋውቅ አንድና ሁለት የለውም።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት የጨርቃ-ጨርቅ እንዱስትሪ ማዕከል የነበረችው አኢቺ ከዚያን ወዲህ ታላቁ የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ ቶዮታና ሌሎች ዋና ዋና ኩባንያዎች የሰፈሩባት ማዕከል ናት። በቶኪዮና በኦሣካ መካከል ለምትገኘው ክፍለ-ሐገር ብልጽግና ዓቢይ ምክንያቱ በአካባቢው ዘመን ያስቆጠረው ጥንቃቄ የተመላበትና ወግ ያጠበቀ የአስተዳደር ዘይቤ ሣይሆን አልቀረም።

የአኢቺ ዓመታዊ አጠቃላይ ምርት 270 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል። ይህም ከታይዋን ወይም ከግዙፏ ሩሢያ የሚመጣጠን መሆኑ ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ የአካባቢው የንግድ ትርፍ በ 2003 ዓ.ም. 7,6 ትሪሊየን የን፤ ወይም 72 ቢሊዮን ዶላር በመድረስ ከጠቅላላው የአገሪቱ ትርፍ 60 በመቶውን ድርሻ የያዘው ነበር። አኢቺ ለ 27 ተከታታይ ዓመታት ቀደምቷ የጃፓን ኢንዱስትሪ ማዕከል ሆና ነው የቆየችው።
ቢሆንም ዛሬ ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ሂደት በተለወጠበት በዘመነ-ግሎባላይዜሺን አኢቺ በቶኪዮና ሌሎች ከተሞች ጥላ ሥር ተሸፍና ዕድገቷን ልትጠብቅ አትችልም። ለውጭው ዓለም ራሷን መክፈት ግድ ነው የሚሆንባት። የወቅቱ ኤክስፖ ለዚህ አመቺ ጥርጊያ እንደሚከፍት የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ጽኑ ዕምነት ነው። ትዕይንቱ 21 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል። መዋዕለ-ነዋይን ለመሳብ እንደሚበጅም ነው የሚታመነው። አኢቺ የአመራረት ስልቷን ሁል-ገብ ማድረግ እንደሚኖርባትም አስተዳዳሪዎቿ እየተረዱት መጥተዋል። አለበለዚያ አንድ ቀደምት የኢንዱስትሪ መሪ እንደተናገሩት “ምርጫው በወቅቱ ታላቁ ከሆነው የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ ከቶዮታ ጋር ማበብ ወይም መውቀቅ ነው የሚሆነው።