1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አከራካሪው የአቶም ኃይል እቅድ በደቡብ አፍሪቃ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 30 2009

በደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ሰሞኑን የካቢኔ ሹም ሽር ያደረጉበትን ሁኔታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የመብት ተሟጋች ቡድኖች አሁንም በጥብቅ እንደተቃወሙት ይገኛል። ሀገሪቱ አከራካሪ የአቶም ኃይል ማመንጫ ተቋም ለመገንባት በማሰላሰል ላይ ሳትሆን እንዳልቀረ መሰማቱ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም።

https://p.dw.com/p/2ati5
Südafrika Atomkraftwerk Koeberg nahe Kapstadt
ምስል picture-alliance/dpa/EPA/N. Bothma

Fokus Afrika A 08.04.2017 - MP3-Stereo

በትናንቱ ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪቃውያን በሙስና በሚተቹት በፕሬዚደንት ዙማ እና ለሀገሪቱ ኤኮኖሚ ችግር ተጠያቂ ነው በሚሉት መንግሥታቸው አንፃር በሀገሪቱ ዓበይት ከተሞች አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ አሰምተዋል፣ ዙማም ስልጣናቸውን እንዲለቁ ጠይቀዋል። 

 የሰሞኑ ሹም ሽር ከዚሁ አከራካሪ የአቶም ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተቋም እቅዷ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው «ኧርዝ ላይፍ» የተባለው ያካባቢ ጥበቃ ተሟጋች እና ፀረ አቶም ድርጅት ባልደረባ  ማኮማ ሌካላካላ ግምታቸውን ገልጸዋል። 

« በካቢኔው ውስጥ ሹም ሽር ማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያት፣  «ሮዛቶም» ከተባለው የሩስያ የመንግሥት አቶም ኃይል ተቋም ጋር አንድ ስምምነት ሳይፈረም አልቀረም መባሉ ነው። እንደተሰማው፣ ይኸው ስምምነት በድብቅ ነበር የተፈረመው።»

በውሉ ስምምነት ላይ አዲሱ የፕሬዚደንት ዙማ ካቢኔ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። የገዢው ፓርቲ፣ የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች ኮንግረስ፣ በምህፃሩ «ኤኤንሲ» አባል ሲቡሲሲዌ ምንጋዲ ባለፈው እሁድ በድረ ገፃቸው በተነበበው ዜና መሰረት፣ የአቶሙ ስምምነት ፍረማ እስካለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጠናቀቅ እንደነበረበት እና አዲሱ የገንዘብ ሚንስትር ማሉዚ ጊጋባ ስምምነቱን እንደፈረሙ ተመልክቶዋል። ይሁንና፣ በዚያን ወቅት ስልጣን ከያዙ ገና ሁለት ቀናት የሆናቸው የገንዘብ ሚንስትር ጊጋባ እንኳንስ የአቶሙን ስምምነት ቀርቶ የራሳቸውን የአድራሻ ካርድ እንኳን አላወጡም ሲል ሚንስቴሩ የ«ኤኤንሲ» አባል ያወጡትን ዘገባ አስተባብለዋል።

Malusi Gigaba neuer Finanzminister Südafrika
ማሉዚ ጊጋባምስል Getty Images/AFP/G. Guercia

ይሁን እንጂ፣ ይኸው የሚንስቴሩ ማስተባበያ ሕዝቡን የሚያረጋጋ አልሆነም። «ሮዛቱም» ከተባለው የሩስያውያኑ የአቶም ኃይል ማመንጫ ተቋም ጋር  ተፈርሟል ስለሚባለው የአቶም ኃይል ማመንጫ ተቋም ግንባታ ስምምነት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ክርክሩ  ቀጥሏል። የደቡብ አፍሪቃ ሀያስያንም ቢሆኑ ጉዳዩን በጥርጣሬ እየተከታተሉት ነው። እንደሚታወቀው፣ ባለፈው ሀሙስ ከስልጣናቸው የተነሱት የደቡብ አፍሪቃ የገንዘብ ሚንስትር ፕራቪን ጎርደን ገዢው ፓርቲ የአቶም ኃይል ማመንጫ ተቋምለመገንባት የያዘውን እቅድ በጥብቅ ነበር የተቃወሙት። ጎርደን የግንባታው ፕሮዤ ሊጠይቅ የሚችለውን ወጪ በተደጋጋሚ ለመንግሥት በመግለጽ፣ ይህ ሀገሪቱን የግዙፍ የውጭ እዳ ተሸካሚ ሊያደርጋት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። በፕሮዤው አንፃር አቋም የያዙት የኃይል ምንጭ ሚንስትር፣ የሕዝባዊ ተቋማት ሚንስትር እና ምክትል ሚንስትርም በሰሞኑ ሹም ሽር ከስልጣናቸው ተባረዋል።
የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ሊያስገነባው ይፈልጋል የሚባለው የአቶም ኃይል ማመንጫ ተቋም ወደ አንድ ትሪልየን የደቡብ አፍሪቃ ገንዘብ «ራንድ» ወይም ወደ 70 ቢልዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል። 

Südafrika Proteste gegen Präsident Zuma
ምስል Reuters/M. Hutchings

«ኧርዝ ላይፍ» የተባለው ያካባቢ ጥበቃ ተሟጋች እና ፀረ አቶም ድርጅት ባልደረባ  ማኮማ ሌካላካላ እንደሚሉት፣ ብዙ ገንዘብ ሊንቀሳቀስበት የሚችለው ይህንኑ ፕሮዤ የተመለከተው ስምምነት እንዲፈረም ሙስና ዋነኛው አነሳሽ ምክንያት ሳይሆን አልቀረም።

ፕሬዚደንት ዙማ የገንዘብ ሚንስትር ፕራቪን ጎርደንን እና የኃይል ምንጭ ሚንስትሯን ቲና የማት ፔተርሰን ከስልጣናቸው ያነሱት በእቅዳቸው አንፃር ተቃውሞ ያላሰሙትን ማሉዚ ጊጋባን አዲሱ የገንዘብ ሚንስትር አድርገው ለመሾም በማሰባቸው እንደሆን በጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሀርትሙት ቪንክለር ገልጸዋል።  
« ምንም እንኳን ከፀሐይ የሚገኘው ኃይል ዋጋ በጉልህ ቢቀንስም፣ አንዳንድ ሀገራት ይህን ፕሮዤ ወደፊት ለማራመድ እየሞከሩ ያሉበት ብቸኛው ምክንያት ሕገ ወጥ ጨዋታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቋሚ ይመስለኛል።»

እጎአ በ2014 ዓም  የደቡብ አፍሪቃ  ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ሩስያን በጎበኙበት ጊዜ የሩስያውያኑ ተቋም «ሮዛቶም» ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ስልታዊ አጋርነት መጀመሩን አስታውቋል። «ሮዝቶም» በዚያን ጊዜ እጎአ እስከ 2030 ዓምም ስምንት የተለያዩ ክፍሎች የሚኖሩት 9,6 ጊጋዋታ ኮሬንቲ የሚያመርት የአቶም ማመንጫ ተቋም ሰርቶ እንደሚያስረክብ ገልጾ ነበር። ይሁንና፣ ይኸው ዜና በደቡብ አፍሪቃ ትልቅ ተቃውሞ ካስነሳ በኋላ የሀገሪቱ የአቶም ኃይል ድርጅት፣ በምህፃሩ «ኔክሳ» እቅዱን መሰረዙ አይዘነጋም። ከዚሁ እቅድ ተግባራዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑት ፕሬዚደንት ዙማ እና ደጋፊዎቻቸው ብቻ ናቸው በሚል ፕሮፌሰር ቪንክለር ወቀሳ ሰንዝረዋል።

አንዳንድ፣ የሩስያውያኑ «ሮዛቶም»ን የመሳሰሉ ተቋማት የአቶም ኃይል ማመንጫውን ፕሮዤ ማነቃቃት የሚችሉበትን ኮንትራት ካገኙ፣ ይህ ብዙ ገንዘብ ያስገኝላቸዋል ማለት ነው። ኮንትራቱን ለማግኘትም ሲሉ የሚቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ። ሕዝቡ እንደሚያምነውም፣ የአቶም ኃይል ማመንጫውን ተቋም የመገንባቱን ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ይረዷቸውም ዘንድ ለፖለቲከኞች ጉቦ ከፍለዋል።

 በአቶሙ ኃይል ማመንጨት እቅድ ዙርያ በተለይ   ጆሀንስበርግ አቅራቢያ የሚገኘው የ«ሺቫ» ዩሬንየም ማዕድን ባለቤት የሆነው የጉብታ ቤተሰብ  ትልቅ ሚና መጫወቱን አስታውቀዋል። እስከቅርብ ጊዜ በፊት ድረስ የፕሬዚደንት ዙማ ልጅ ዱዱዛኔ በ«ሺቫ»ማዕድን ይሰሩ ነበር። የማዕድኑ ስራ አስኪያጆች ኤጄይ፣ አቱል እና ራጄሽ ጉፕታ ከፕሬዚደንት ዙማ አድርገዋቸዋል በተባሉ ፕሬዚደንቱን እጎአ  በ2016 ዓም ስልጣናቸውን ሊያሳጡዋቸው ቃጥተው በነበሩ ብዙ ውሎች ሰበብ ትልቅ ቅሌት ገጥሟቸው እነደነበር ተገልጿል። 
የአቶም ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫውን ተቋም ጉዳይ የሚከታተለው በሕዝባዊ ተቋማት ሚንስቴር ስር የሚገኘው የመንግሥቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ድርጅት፣ «ኤስኮም»  ነው።  የዚሁ ድርጅት ባለስልጣናት በሩስያ እና በደቡብ አፍሪቃ መካካል የአቶም ኃይል ማመንጫውን ተቋም ግንባታ ስምምነት ስለመፈረሙ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ  በማስታወቅ፣ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ደቡብ አፍሪቃ እስከ ሚያዝያ 28፣ 2017 ዓም ድረስ ማመልከቻዎችን በማሰባሰብ ላይ መሆኗን ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። እስካሁን በኑክልየር ቴክኒክ ስመ ጥር የሆኑ የፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩስያ እና ደቡብ ኮርያ ተቋማት ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ለመስራት እንደሚፈልጉ ያስታወቁ ሲሆን፣ «ኤስኮም» ሀሳቦቹን ለገንዘብ ሚንስቴር እና ለካቢኔው እንደሚያቀርብ እና የተያዘው 2017 ዓም ሳያበቃ በፊት አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋውን ገልጿል።

Südafrika LOGO Energiekonzern Eskom
ምስል Getty Images/AFP/G. Guercia

የሩስያውያኑ የመንግሥት ተቋም «ሮዛቶም» እጎአ ከ2012 ዓም ጀምሮ በደቡብ አፍሪቃ ጽሕፈት ቤት ያለው ሲሆን፣ በድረ ገጹ እንደተነበበው፣ የኑክልየር ኃይል ስነ ቴክኒክን በአፍሪቃ ለማነቃቃት ይፈልጋል። የሩስያ ዜና ወኪል «ታስ» እንዳስታወቁት፣ ሩስያ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር የአቶሙን ኃይል ምርት በተመለከተ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር የመስራት ፍላጎት አላት። በዚህም መሰረት «ሮዛቶም» ፍላጎቱን ባለፈው ጥር 2017 ዓም ለደቡብ አፍሪቃ በጽሁፍ አቅርቧል።  ዶይቸ ቬለ የአቶም ኃይል ማመንጫውን ተቋም ግንባታ እና አመልካቾችን ጉዳይ አስመልክቶ ባደረገው የመረጃ መሰባሰብ ስራ መሰረት፣ ከሁሉም አመልካቾች መካከል «ሮዛቶም»  የተሻለ እድል አለው። ይሁን እንጂ፣ «ኔክሳ» እና «ኤስኮም» ከጥቂት ጊዜ በፊት ያወጡት ዘገባ ሩስያ ከእድለኞች ሊሆኑ ይችላሉ ከሚባሉት አመልካቾች መካከል አትቆጠረም።

«ኔስኮም» እና «ኤስኮም» ይህን ይበሉ እንጂ፣ «ኧርዝ ላይፍ» የተባለው ያካባቢ ጥበቃ ተሟጋች እና ፀረ አቶም ድርጅት ባልደረባ  ማኮማ ሌካላካላ ሩስያ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር በድብቅ ስምምነቱን እንደተፈራረመች ያምናሉ። በመሆኑም፣ የአቶም ኃይል ማመንጫ ተቋም ግንባታን በተመለከተ መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው በማስታ,ወቅ፣ ግንባታው  እንዲቆም በፍርድ ቤት ክስ  መስርተዋል። 

«በአቶም ኃይል ማመንጨቱ ጉዳይ ዙርያ የተደረጉት ውይይቶች ሁሉ በድብቅ ነበር የተካሄዱት። ይህ አሰራርም በሕገ መንግሥታችን የሰፈሩትን የኛን እሴቶች የሚያጎሉትን አንቀጾች የሚጥስ ነው። ግልጽነት እና ዴሞክራሲያዊው ምክክር የሚሉት ሀሳቦች በአቶም ኃይል ማመንጨቱ ጉዳይ ዙርያ በተደረጉት ውይይቶች ወቅት ተጓድለዋል።»   
እርግጥ፣ ደቡብ አፍሪቃ ቻይናን ከመሳሰሉ ሌሎች የአቶም ኃይል ስነ ቴክኒክ አቅራቢዎችም ጋር ብትወያይም፣ እንደ ሌካላካላ አባባል፣ ከሩስያ ጋር የተካሄደው ውይይት ጠለቅ ያለ ነበር።

አዲሱ ውል ይኸው ከሩስያ ጋር የተደረሰው ነው። ውሉ ለምሳሌ፣ ከኮርያ እና ከዩኤስ አሜሪካ ጋር ከተፈረሙት ውሎች በተለየ፣ ብዙ ዝርዝር ሀሳቦችን የያዘ ነው።»
ደቡብ አፍሪቃ ልትገነባው አስባለች የሚባለው የአቶም ኃይል ማመንጫ ተቋም ሀገሪቱን እጅግ ብዙ ገንዘብ እንደሚያስወጣ ይገመታል። በዚሁ ሰበብ ፕሮዤው ብርቱ ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ ፕሬዚደንቱ ባደረጉት የካቢኔ ሹም ሽር እቅዱ ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ አመቻችተዋል።

Windrad Windräder Erneuerbare Energien Windpark Südafrika Flash-Galerie
ምስል AP

«ብዙዎች እንደሚገምቱት፣ ውሉ ከብዙ ጊዜ በፊት ነው የተፈረመው፣ ሆኖም ግን ፕሬዚደንት ዙማ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል በገጠማቸው ተቃውሞ የተነሳ ሊገፉበት አልቻሉም። »

በደቡብ አፍሪቃ ኃይል የማመንጨት እቅድ መሰረት፣ ሀገሪቱ ለየሚያዋጡ አማራጮች ቅድሚያ እንድትሰጥ ያሳስባል። ደቡብ አፍሪቃ ኃይልን ከፀሐይ፣ ነፋስ እና ከባዮጋዝ ማምረት የምትችልበት አማራጭ አላት። አዳዲሶች መርሀግብሮች በጥሩ ሁኔታ ተመካሄዳቸው ተሰምቶ ነበር። ባለፈው ዓመት  «ኤስኮም» በወጪ ምክንያት ከነፃ የኮሬንቲ አምራጮች ጋር ሌላ ኮንትራት እንደማይገባ ማስታወቁ ይታወሳል፣ እና አሁን የአቶሙ ኤሌክትሪክ ኃይል ውል ከመጣ በሕዝቡ ላይ ተጨማሪ ወጪ ይጨምርበታል። ግን፣ በሀገሪቱ የኃይል ፍጆታ ያን ያህል ፈጥኖ ባለመቸመሩ በርግጥ የአቶም ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ማስፈለጉ ጉዳይ ሊጤንበት ይገባል። በ2012 ዓም የተጀመረው  አረንጓዴ የኃይል ማመንጫ መርሀግብር  ስኬት እያሳየ በመሆኑ ፣ ቪንክለር እንደሚሉት፣ ደቡብ አፍሪቃ ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት የአቶሙ ኤሌክትሪክ ኃይል  አያስፈልጋትም። 

ማርቲና ሺቭኮቭስኪ/አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ