1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አክራ፥ የጋናው ፕሬዚዳንት ስርዓተ-ቀብር

ዓርብ፣ ነሐሴ 4 2004

ጋና የሟች ፕሬዚዳንቷ ጆን አታ ሚልስን የቀብር ስነ ሥርዓት አርብ ነሐሴ 4 ቀን 2004 ዓ ም በክብር ፈፀመች። በቀብር ስርዓቱ ላይ የ16 ሐገራት ርዕሳነ-ብሔር እና የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂላሪ ክሊንተንን ጨምሮ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል።

https://p.dw.com/p/15nsn
የጋናው ፕሬዚዳንት ስርዓተ-ቀብር
የጋናው ፕሬዚዳንት ስርዓተ-ቀብርምስል picture-alliance/dpa

ጋና የሟች ፕሬዚዳንቷ ጆን አታ ሚልስን የቀብር ስነ ሥርዓት አርብ ነሐሴ 4 ቀን 2004 ዓ ም በክብር ፈፀመች። በቀብር ስርዓቱ ላይ የ16 ሐገራት ርዕሳነ-ብሔር እና የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂላሪ ክሊንተንን ጨምሮ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል። ቀያይ ልብሶችን የለበሱ እና በፈረሶች ላይ የተፈናጠጡ የክብር ዘቦች እንዲሁም ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ለቀስተኞች የሟቹን ፕሬዚዳንት የሬሳ ሳጥን የተሸከመውን ጥቁር ሊሞዚን መኪና አጅበው የአክራ ጎዳናዎችን ማጨናነቃቸው ተዘግቧል።

Ghana Beerdigung von John Atta Mills
ምስል Reuters

በርካታ ወታደሮች በስርዓተ-ቀብሩ ላይ የተሳተፉ ሲሆን፤ ወታደራዊ ማርሽም አሰምተዋል። የነፃነት አደባባይ ላይ ለተሰበሰበው ሐዘንተኛ መጪው ምርጫ የሰላም እንዲሆን የሚገልፁ በራሪ ወረቀቶች ከሂሊኮፕተር ተበትነዋል። ጆን አታ ሚልስን የተኩት የጋናው ምክትል ፕሬዚዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ጋናውያን አንድ እንዲሆኑ አሳስበዋል፥

«ከግባችን ለመድረስ የተለያየ አስተሳሰብ እና ዕቅድ ቢኖረንም፤ ጉዳዮቹ አንገብጋቢ በሚሆኑበት ወቅት፤ ግባችንን ለማሳካት፥ መፈለግ ብቻ አይደለም በአንድነት ለመነሳት እንደምንችልም እያሳየን ነው።»


ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆን አታ ሚልስ ቅርብ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአይቮሪኮስቱ መሪ አላሳን ካታራ ደግሞ በግላቸው ለሟቹ ቤተሰቦች የገንዘብ እና የላሞች ርዳታ መለገሳቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ጠቅሷል። ፕሬዚዳንት አታ ሚልስ የጋና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ በድጋሚ ለመሳተፍ አምስት ወራት ይቀራቸው ነበር። ሚልስ የጉሮሮ ነቀርሳ ሲያሰቃያቸው ቆይቶ ነበር የዛሬ አስራ አምስት ቀን ድንገት ማረፋቸው ይፋ የሆነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ