1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው መግለጫ በአዲስ አበባ

ዓርብ፣ ሰኔ 23 2009

የዛሬ ሁለት ወር ግድም ሠነዱ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ባፈተለከበት ወቅት የበርካቶችን ቀልብ ስቦ ነበር። ከያኔው ሠነድ ይዘት ጋር እጅግ ተቀራራቢ የሆነ መግለጫ ደግሞ ሰሞኑን ይፋ ኾኗል። መግለጫው ገና ካሁኑ አወዛጋቢ ከመሆንም ባሻገር አንዳንድ ትኩረት የሚያሻቸው ርእሰ ጉዳዮች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንዲደበዝዙ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/2ffAN
Äthiopien - Addis Abeba - City Churchill Road
ምስል DW/Y. Geberegziabehr

«የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ የቀረበ መግለጫ» የሚል ርእስ ይዟል፤ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ማክሰኞ ከሰአት በአምደ መረቡ ያወጣው መግለጫ።  ይህን መግለጫ  በተመለከተ የመንግሥት መገናኛ አውታሮችም ደጋግመው ዘግበውታል።  ከዚህ መግለጫ ጋር ተቀራራቢነት ያለው ሰነድ የዛሬ ሁለት ወር ግድምም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲሰራጭ ሰነዱ ያካተታቸው አንዳንድ ጠጣር ጉዳዮች ብዙዎችን አሳስቦ ነበር።

ከሰሞኑ ይፋ የሆነው መግለጫ ግን «ጠጣር» የተባሉት አንዳንድ ጉዳዮችን ሲያስቀር አብዛኛ ይዘቱ ከቀድሞው ሰነድ ጋር ተቀራራቢ ነው። የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የትኩረት አቅጣጫን በፍጥነት ያስቀየረው ይኽ መግለጫ የኦሮሞ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ነቀፌታ ገጥሞታል።

ብዙዎች ረቂቅ አዋጁ እንዲህ በጥድፊያ ለህዝብ ይፋ የተደረገው የሰውን ልብ ትርታ ለመለካት ነው እንጂ እንደተባለው ነዋሪዎች ውይይት አያደርጉበትም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የምክር ቤቱ ዓመታዊ የሥራ ማጠናቀቂያ  የቀረው ከ10 ቀን በታች መሆኑን ይጠቅሳሉ።

Äthiopien Parlament Hailemariam Desalegn
ምስል DW/Y. G. Egziabher

ረቂቅ አዋጁ በጥድፊያ በመገናኛ አውታሮች የተነገረው በኦሮሚያ እና በጎንደር በርትቶ በነበረው ተቃውሞ «ሥጋት የገባው» መንግሥት ሌላ የመወዛገቢያ አጀንዳ በመስጠት ፋታ ለማግኘት በማሰብ ያደረገው «ተንኮል» ነው ያሉም አሉ። አንዳንዶች ደግሞ ረቂቅ አዋጁ የኦሮሞን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚል ሰበብ በኦሮሞዎች ዘንድ ብርቱ ተቃውሞ ያስነሱ ጉዳዮችን «በጓሮ በር ለማስፈጸም» የተደረገ ነው ብለውታል።

ግርማ ጉተማ በፌስቡክ ገጹ፦ «የኦሮሚያን ጥቅም ለማስከበር በሚል የወጣው አዲስ ሕግ፣ ፊንፊኔ ከተማ ኦሮሚያ ላይ ተጠንተው በሚገነቡ ቦታዎች ላይ ቆሻሻ መጣያዎችን ትገነባለች በሳይንሳዊ መንገድ እንዲተዳደርም ይደረጋል ይላል። የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ይሄ ነው እንግዴ¡¡¡» ሲል ጽፏል።

ገረሱ ቱፋ ደግሞ «የፊንፊኔ ልዩ ጥቅም ተብዬው» በማለት ይንደረደር እና ለይስሙላ መግለጫው በርካታ ጉዳዮች የቀሩት እንደሆነ ይገልጣል። «ወሳኝ የተባሉ የድምፅ መስጠት ኃይል ወይንም የጋር አስተዳደር፣ በከተሞች መሀከል ያለ የወሰን ጉዳይ እና  የሐብት ክፍፍል ሙሉ ለሙሉ ሳይነሳ ቀርቷል» በማለትም መግለጫውን በጥቅሉ «ባዶ ኳኳታ» ሲል ሰይሞታል።

ከዚህ ቀደም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የተሰራጨው ሰነድ እና አሁን በመግለጫ መልክ ይፋ የተደረገው ረቂቅ አዋጅ በህዝቦች መካከል «ቅራኔ» እንዲፈጠር ሰበብ ሊሆን ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን የገለጡም አሉ።

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

በየጊዜው ወደ ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የሚወረወሩ ሐሳቦች በተደጋጋሚ ብዙዎችን ሲያነታርኩ ተስተውለዋል። የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን አባል የሆነው አጥናፍ ብርሃኔ በትዊተር ገጹ ያስነበበው ጽሑፍ ንትርኩ ያሳሰበው ይመስላል። አጥናፍ፦ «ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ስለሚኖረው ልዩ ጥቅም በሚያትተው ረቂቅ ሰነድ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰነዘሩ አጸፌታዎችን» ለማየት መቸኮሉን ገልጧል።

«ኧረ ለመሆኑ፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ አይደለችም እንዴ ሲል ያጠየቀው ደግሞ መምሕርና የአምደ መረብ ጸሐፊው ሥዩም ተሾመ ነው። ሥዩም «'ኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ለማስከበር' እያሉ በነፃ አሳልፎ መስጠት አለ እንዴ?» በሚል ርእስ ድረ-ገጽ ላይ ያሰፈረው ጽሑፍ፦ «በሺህዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች በከፈሉት መስዕዋት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኖሩ የክልሉ መንግሥት ሠራተኛ የኮንደሚኒዬም ቤት ሲጠይቁበት ማየት ያሳፍራል» ሲል በማጠቃለያ ጽሑፉ ላይ አስነብቧል።

ሥዩም «የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ አራት ግዜ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል 'እምብርት ላይ የምትገኝ በመሆኗ' ይላል። የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 (5) ግን አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል “መሃል” የሚገኝ መሆኑን የሚጠቅሰው» ሲልም ድረ-ገጽ ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ አትቷል።

ከሥዩም አመለካከት ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ ደግሞ ሊያና ተፈሪ በትዊተር ገጿ አዲስ አበባ ሸዋ ላይ የምትገኝ ከተማ እንደሆነች ስያሜዋን የመቀየር ርእስም ፈጽሞ ሊነሳ የማይገባ መሆኑን ታሪካዊ ሰነዶችን በማጣቀስ ታብራራለች። ሊያና በኢትዮጵያ ታሪክ ዝነኛው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እና በቅድመ-ታሪክ ሊቁ ሐርትቪግ  ብሬተርኒትስ በጋራ ያወጡት ጥናታዊ ጽሑፍ የሚገንበት ድረ-ገጽ ማገናኛ አያይዛለች።

Professor für Geschichte Richard Pankhurst gestorben
ምስል Alula Pankhurst

ሊያና ያያዘችው በውጭ ሀገር የታሪክ ሊቃውንት የተጻፈው ሰነድ፦ በደቡብ ሸዋ ከአዲስ አበባ ከተማ አቅራቢያ ከ500 ዓመታት በፊት ማለትም በ15ኛው እና 16ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ በወቅቱ «የአቢሲኒያ» መዲና ስለነበረችው እና በብዙዎች ዘንድ ስለማትታወቀው «በረራ» ስለተሰኘችው ጥንታዊ ከተማ ያትታል። ከተማዋ በወጨጫ አካባቢ እና በየረር ተራሮች መሀከል፤ የአቃቂ ወንዝን በስተምዕራብ፤ የዝቋላ ተራራን እና የአዋሽ ወንዝን በስተደቡብ ብሎም የሞጆ ወንዝ እና ደብረዘይትን በስተ ምሥራቅ አድርጋ ትገኝ እንደነበር ጥናቱ ይገልጣል።

ከተማዋ በአዳሉ ግራኝ አኅመድ ኢብን ኢብራሒም ወረራ ወቅት መውደሟን ቆየት ብሎም ኦሮሞዎች እንደሰፈሩባት ጥናቱ ይገልጣል። ጥናቱ «በረራ» የሚባል የኢትዮጵያ መዲና እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1464 ዓመት ቬኒስ ከተማ ውስጥ ታትሞ በነበረው በቬኒሱ ካርታ ቀያሽ ፍራ ማውሮ ጥንታዊ ካርታ ላይ እንደሚገኝም ይጠቁማል።  ይኽን ሰነድ ያያዘችው ሊያና «አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል» ስትል በትዊተር ጽፋለች።

ባላምባራስ በሚል የትዊተር ስም የሚነበብ መልእክት ደግሞ «አዲስ አበባን በተመለከተ ስለ ሰሞኑ ዘብራቃ ነገር ለማውራት  እስኪ ትንሽ ወደ ኋላ ወደ ታሪክ እንጓዝ» ይላል። በእንግሊዝኛ የተጻፈው የባላምባራስ መልእክት «የጠፉ የኢትዮጵያ ከተሞች» በሚልም በእንግሊዝኛ የተጻፈ ሰነድ ተያይዞበታል።  ባላምባራስ በትዊተር ገጹ ሊያ ካያያዘችው ጋር ተመሳሳይ እና ሌሎች ጥንታዊ የታሪክ ሰነዶች የተያያዙበት በርካታ መልእክትም አስፍሯል።

«የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ከአማርኛ ጎን ለጎን መነገሩ ችግር የለውም» ያለው ሀብታሙ ሥዩም «የቋንቋውን የበላይነት ለማስረገጥ በማሰብ በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ የሚቃጣ የፊት ለፊትም ሆነ የእጅ አዙር ጫና እስከሌለ ድረስ» ብሏል በፌስቡክ ጽሑፉ። ሀብታሙ አያይዞም  «የአሮሞ ተቃዋሚዎችም ሆነ የመንግስት ሰዎች ከኢትዮጵያዊነት የጋራ ጉዞ ይልቅ "ኦሮሚያ! ኦሮሚያ!" በማለታቸው እንደ ስለት ልጅ እንክብካቤ እንደበዛላቸው የሚሳማቸው ወገኖች- ተመሳሳይ ዘመቻ አራብተው የራሳቸውን ዕድል ለመሞከር አሁን ወኔውን የሚያገኙ ይመስለኛል» ሲል ጽሑፉን ቋጭቷል፡፡ 

Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

ማንኛውም የሸዋ ሰው «ሸገር» ብሎ እንደሚጠራ የገለጠው ኤፍሬም ኤፍሬም «ፊንፊኔ በፖለቲካ ውሳኔ የመጣ ስም ነው» ብሏል በፌስቡክ ገጹ። «አዲስ አበባ  ለእኛ ባዕድ ነው ካሉ ፊንፊኔም የበለጠ ባዕድ ነው። ከባሌ ወይም ከወለጋ መጥተህ እትብቱ የተቀበረበትን ከተማ ያንተ አይደለም ልትለው አትችልም» ይልና ቀጠል አድርጎም «ይኼንን ሁሉ የሸዋ ሰው እንዲህ አዚም ያደረገበት ማነው? ያ ሁሉ ንቃቱ እና ጥንቁቅነቱ፣ ብልጠቱ እና አርቆ አስተዋይነቱ ወዴት ሄደ?» ሲል ያጠቃልላል።  

«ከሸገር ውጪ የሚኖር ኦሮሞ ሸገር መጥቶ መታከም መቻሉ ልዩ ጥቅም ሊባል ነው ማለት ይሆን?!?! ወይ ጉድ» በማለት ልዩ ቀልድ ሲል የገለጠው ደግሞ እሸቱ ሆማ ቄኖ ነው።

ይህንኑ ርእስ አስመልክተን በዶይቸ ቬሌ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ የመወያያ ርእስ አስፍረን ነበር። ከሦስት መቶ በላይ አስተያየቶች ደርሰውናል። የተወሰኑትን ለመመልከት ያኽል፦  ራስ ዳሸን እንዲህ ሲል ጽፏል። «ከብሔር ፖለቲካ በትንሹም ቢሆን መሸሻ መሸሸጊያችን አዲስአበባ ነበረች ከእንግዲህማ ነገሩ ሁሉ እንኳንስ እናቴ ሞታብኝ እንዳውም አልቅስ አልቅስ ይለኛል መሆኑ ነው ።ለማንኛውም የአሁኑዋ እሳት ትንሽ ምላጭ አገር ትላጭ እንዳትሆን ሰግተናል» ብሏል።

ዬሮ ደረሰ በበኩሉ፦ «አንድ ሀገር 2ትና ከዛ በላይ የስራ ቐንቐ አላቸውለምሳሌ ቤልጅየም ሦስት ቐንቐ አለት ህንድም በተመሳሳይ ኦሮምኛ ሆነ ብሎ ማልቀስ ተገቢ አይደለም» ይላል መግለጫው በኦሮሞ እና በጎንደር የተቀሰቀሰውን ብርቱ ተቃውሞ ለማብረድ በመንግሥት የተደረገ የማስቀየሻ  ስልት እንደሆነም ዬሮ ጠቅሷል።

አሸናፊ በቀለ ደግሞ፦ «እኛስ ጥለነው የመጣነው አገር የሌለን ከተማዋን የቆረቆሩትም አባቶቻችን በፈጠሩት አንድነት ፍቅር አብሮነት የኢትዮጵያ ምሳሌ የሆነ ማንነት ይዘን የተወለድን ልጆችስ ምንም አንጠየቅም ይህ ጉዳይ አይመለከንም ማለት ነው?» ሲል ጥያቄ አቅርቧል። «አዲስ አበባ የኦሮሚያ በቻ አይደለችም ሁሉም ኢትዮጵያዊ 125 መት በጋራ የተገነባች አገራችን ነች» ያለው ሚካኤል ወርቁ«ይህ ሆኖ ሳለ ለፖለቲካ ጥቅም ተብሎ የሚሰራ ነገር ተቀምጠው የሰቀሉት....አይነት ውጤት እንዳይኖረው እሰጋለው» ሲል ደምድሟል።

Äthiopische Rückkehrer aus Saudi-Arabien
ምስል DW/S.Shibru

በነገራችን ላይ አድማጮች ይህ «የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም» የሚለው መግለጫ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጥሪ እና ድምፅ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች እንዲደበዝዝ አድርጓል። ሳዑዲ ዓረቢያ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች ከሀገር እንዲወጡ ያስቀመጠችው የምህረት ቀነገደብ በመጠናቀቁ በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በጭንቀት ይገኛሉ።

ከሳዑዲ ዓረቢያ የሪያድ አየር ማረፊያ ውስጥ ከተደረደሩ ሻንጣዎች እና ሰዎች መሀል ሆኖ የሚታይ አጠር ያለ የቪዲዮ ምስል የላኩልን አድማጫችን የድምፅ መልእክትም አክለዋል። መጥፎ ጠረን እና አዋራ ባለበት ሥፍራ በሪያድ አየር መንገድ ለስድስት ቀን ያኽል እንደተጉላሉ የገለጡት አድማጫችን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መጉላላቱን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። «ከሳዑዲ ዓረቢያ አየር መንገድን የቆረጠ ለደቂቃ፣ ለሰከንድ እንኳን አይቀመጥም፤ አይጉላላልም በሰላም ነው ሀገሩ እየገባ ያለው» ሲሉ ምሬታቸውን አሰምተዋል። አድማጫችን መልእክታቸውን የላኩት ማክሰኞ ዕለት ነበር። 

ከሳዑዲ ዓረቢያ በጽሑፍ መልእክቱን ያደረሰን ያሲን የተባለ ተከታታያችን ደግሞ «አሁን ያለንበት ቦታ በጣም አስጊ ከመሆኑ የተነሳ ለአይምሮ ቀዉስ ነወ የተዳረግነው። እዉን ሰሚ መንግስት አለን ይሆን ይሄነን ለናንተዉ ተቸዋለዉ» ሲል እሮሮውን ከሳዑዲ ዓረቢያ አሰምቷል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ