1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የሕወሓት መግለጫ

ዓርብ፣ ሐምሌ 5 2011

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ከአስቸኳይ ጉባኤው በኋላ ያወጣው መግለጫ በማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች አነጋጋሪ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር። ከ3 ቀናት በፊት ሦስት የሲዳማ ፓርቲዎች፣ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የሚካሄድበትን ጊዜ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአምስት ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቅ መጠየቀቸው፣ ሌላው ልዩ ልዩ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት ጉዳይ ነበር።

https://p.dw.com/p/3M0Wf
Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

 ሰሞኑን አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄደው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለሰኔ 15 2011ዱ ግድያ ኃላፊነቱን እንዲወስድ እና ይቅርታም እንዲጠይቅ ያሳሰበበት መግለጫ ብዙዎችን አነጋግሯል። በመግለጫው ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትችት፣ ተቃውሞ እና ቁጣ ያመዘነባቸው አስተያየቶች ተነበዋል።
ሳባ ሀበሻዊት «ህወኃት መጀመሪያ ራሱን ሳያፀዳ መቀሌ መሽጎ አዴፓን የመክሰስ ቀርቶ ስለአዴፖ የማውራት ሞራልም ብቃትም የለውም፡፡» ሲሉ በፌስቡክ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። «የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች» በሚለው ምሳሌያዊ አባባል ሃሳባቸውን የጀመሩት ደግሞ አንተነህ ጎን ናቸው። « ምን ማለት እንደፈለጉ ለነሱ እራሱ ግልፅ አይደለም። አንዴ ይቅርታ ይጠይቅ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጉዳዩ ይጣራ ምን ማለት ነው? ሲሉ ጠይቀዋል። «የኢትዮጵያን ህዝብ ቀድመው እነርሱ ይቅርታ ቢጠይቁት ያምር ነበር። መግለጫ ጠላን» ብለዋል ዮናታን ታምሩ በፌስቡክ ባሰፈሩት አጭር መልዕክት ። እውነቱ ይታወቅ በሚል የፌስ ቡክ ስም አስተያየት የሰጡት ደግሞ «ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል ፤የትርምሱ ሁሉ ጥንስስ ከማን እንደሆነ ግልፅ ሆኖ! ምን ዓይነት ንቀት ነው?» ካሉ በኋላ ፍርዱን ለአምላክ ትተዋል።ጊዜለኩሉኃይሉ ደግሞ«በእሳት የተፈተነ ላመነበት ዓላማ ሟች ድርጅት ማለት ህወሓት ብቻ ነዉ» ሲሉ ድርጅቱን አወድሰዋል።

EPRDF Logo


ሄለን ዳዊት በአጭሩ ፣«አባት ልጅን እንዲህ ይመክራል ይቆጣል» ሲሉ  መሀመድ አሊ ደግሞ «እስኪ ዛሬ እንኳን እፈሩ! እናንተ የዘራችሁትን እያጨድን ነውና፡፡ የህወሓት ጭቆና እና አስተምህሮ የአማራ ብሄርተኝትን ወለደ፣ ብዙ የክልልነት ጥያቄ አስነሳ፣ ዜጎች በየቦታው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆነ፣ በአንድ ሐገር ብዙ መንግሥት ነኝ ባይ በዛ፣ ከሐገር ይልቅ ለክልል መጨነቅ አስከተለ፣ ከራሽናል አስተሳሰብ እንድንወጣ አደረገን፣ በብሔርና በቋንቋ ተቧደንን» በማለት ችግሩ ስር እየሰደደ ሊመጣ የቻለበት ምክንያት ያሉትን አካፍለዋል።
የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ በከትናንት በስተያ መግለጫው፣ አዴፓ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ይጠይቅ ያለው ድርጅቱ አሉበት ያለውን «ውስጣዊ ችግሮች በመሸፋፈን በሦስተኛ አካል ማሳበቡን ትቶ ራሱን በጥልቀት እንዲፈትሽ እና እንዲገመግም» በማሳሰብም ጭምር ነው። ይህን የማያደርግ ከሆነ ደግሞ «ሕወሓት ከአዴፓ ጋር ለመሥራት እንደሚቸገር መታወቅ አለበት» ሲልም አስጠንቅቋል።
አለባቸው ሳበቂ በሪሁን «እውነት ከTPLF ጋር ከመሥራት ቢቀር ይሻላል፡፡ አማራን የሚያነቁ የተሻሉ ግለሰቦችን ለማጥቃት መጠነ ሰፊ ዘመቻ ተከፉቷል፡፡ የሚገርመው በወንጀል ከሆነ ከነአሳምነው በላይ የትግራይ ሹማምንቶች እንደ ጌታቸው ያሉት መች ተያዙ,,,» ,ሲሉ  ጽፈዋል።
በህወሀት መግለጫ ላይ ከተሰጡት አስተያየቶች ማዲ ዮናስ በሚል ስም በትዊተር የቀረበው መልዕክት ለየት ያለ ነው። ማዲ ሁኔታውን ይገልጽልኛል ባሉት የዘፈን ግጥም ነው መልዕክታቸውን ያስለታለፉት «አዴፓ፤ ለድሮ ፍቅረኛው ህወሀት የጋበዛት ዘፈን ፣ ተበድየስ ይቅርታ አልልም የቀረው ይቅር እንጂ፤ ተበድየስ ማሪኝ አልልም የቀረው ይቅር እንጂ፤ እንኳን ልልክ አማላጅ እግሬ አይረግጥም ያንቺን ደጅ» ሲሉ። 
 ሌላው የሰሞኑ መነጋገሪያ ሦስት የሲዳማ ፓርቲዎች ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጡት ማስጠንቀቂያ ነው። የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን)፣ የሲዳማ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሲብዴፓ) እና የሲዳማ ሀድቾ ዴሞክራሲያዊ ደርጅት (ሲሀዴድ)ከሦስት ቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የሚካሔድበትን ጊዜ በሚቀጥሉት አምስት ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቅ ጠይቀዋል። እነዚሁ ፓርቲዎች ጥያቄው መልስ ሳያገኝ ለሚፈጠሩ ፖለቲካዊ እና ሕዝባዊ ጫናዎች፣ የደቡብ ክልል ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል። በዚህ ማስጠንቀቂያ ላይ በማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች ተቃውሞ ድጋፍ እና ምክር አዘል መልዕክቶች ተላልፈዋል።  
ኤክሶደስ ፍሪደም በፌስቡክ «በአምስት ቀን ውስጥ ማለት ምን ማለት ነው? ነገርየው ፖለቲካ መሆኑ ቀርቶ የዕቃቃ ጫወታ ሆነ እንዴ?? እረ ሰከን!! በመመካከር እና በመወያየት ቢሆን!!! ለሚፈጠረው ችግር ደግሞ በየትኛውም ዓለም ቢሆን ተጠያቂ የሚሆነው ይሄንን አይነት ቀስቃሽ መግለጫ እየሰጠ ያለው አካል እና ዞኑን እያስተዳደርኩነኝ የሚለው የዞኑ አመራር እና ካቢኔ ነው፣» ሲሉ አሳስበዋል። 
«ቂል ሲነሳ ቤት ያነሳ አሉ አበው፤ በ5ቀን መልስ ማግኝት መፈለጋችሁ ሞኝነታችሁን ያሳብቅባችኋል» የእዮብ አሻግሬ አስተያየት ነው። ሀስማ ሀስማ በሚል የፌስቡክ ስም አስተያየታቸውን የሰጡ ደግሞ «እኔ የገረመኝ አንድ ኢትዮጵያ ስንት ቦታ ልትቆራርሳት ነው እሪ የመንግሥት ያለ ኡኡኡኡኡኡኡ…» ሲሉ በፌስቡክ ጩሀታቸውን አሰምተዋል።  
«የሲዳማ ብቻ ለምን?» የሚለውን ጥያቄ ያስቀድሙት ሰንደኤ እንዳወቄ፣ «ከ10 በላይ ክልል የመሆን ጥያቄ ያቀረቡ ብሔሮች ከሲዳማ ጋር እኩል መልስ ሊሰጣቸው ይገባል። በሕጋዊነት ሽፋን ሕገ ወጥነት ይቁም»  ሲሉ አሳስበዋል።
አሚር ዜድ መሐመድ «መብታችሁ እንደሆነ ማንም ያውቃል። ግን በዚህ መልኩ አይደለም። በደምብ ታስቦበት እናንተ ወይ ተወካያችሁ ባሉበት ፣ በሰከነ መንፈስ ነው እንጂ እንደው በችኮላ የኋላ የኋላ አያምርም እና ሲዳማዎች አስቡበት እንደባህላችሁ ቁጭ ብላችሁ በደንብ ተወያዩበት።» ሲሉ መክረዋል።
«ምንድን ነዉ እዚህ ሀገር ላይ አዛዡ ፡ አስጠንቃቂዉ በዛ፡ ምን ልትፈጥሩ ነዉ?» አለባቸው ባለህ ናቸው ይህን ያሉት። ጎልዲያስ ዘአቢሲንያ በትዊተር «ችኮላ እና ስሜታዊነተት ዋጋን ሲያስከፍል፤ ትዕግስት እና ማስተዋል ግን ጣፋጭ ፍሬን ታፈራለችና ወገኖች ሆይ አካሄዳችን በማስተዋልና በትዕግስት የተሞላ ይሁን!» ብለዋል። «ለሁሉም ነገር ሕግና ደንብ አለ በሕግ አለመመራት በሕግ ተጠያቅ ያደርጋል እናንተ ግን በጉልበት ክልል እንሆናለን ብላችሁ ትፍጨረጨራላችሁ። ይህ የሚያሳየው ስለሕግ ጥልቅ እውቀት እንደሌላችሁ ነው ። ያለ እውቀት ተንቀሳቅሳችሁ ህዝቡን አዘቀት ውስጥ እንዳትከቱ ተጠንቀቁ ወደፊት ክልል ብትሆኑ እንኳን ሀገር ለመምራት እውቀት ይኑራችሁ።» ሲሉ ኤፍሬም በቀለ ምክራቸውን ለግሰዋል።የጌታቸው ሀብቴ መልዕክት ደግሞ ጥሪ ነው  «እናንተ ለህዝብ ቆመናል የምትሉ ምነው የንጹሐን ደም እንዲፈስ ተንቀዠቀዣቹ?! እረ ተረጋጉ እናንተ ህዝብ እንዲረጋጋ ትልቅ ሚና ይጠበቅባችዋል። እለበለዚያ ለሚፈጠረው ማንኛውም ችግር ቁጥር አንድ ተጠያቂ ናችሁ ምርጫ ቦርድ ምን እንዲያደርግላቹ ነው የምትፈልጉት? ሕግ ማክበርና ማስከበር ይጠበቅባችዋል።» የሚል።
በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ካወዛገቡት መካከል የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ግርግር በፈጠሩ ወጣቶች መቋረጡ ነው። ዜናው ከተሰማ በኋላ አሊወልዲም አቢ በፌስ ቡክ «ዲሞክራሢን ለማሥፈን ቆርጨ ተነሥቻለሁ ከሚል መሪ ሐሣብን በጉልበት መገደብ በጣም ያሣዝናል። ሰዎቹ የለየላቸው አምባ ገነኖች መሆናቸው በጊዜ መፈታት አለበት። አዲስ አበባ የአንድ ብሔር መዲና በጭራሽ ልትሆን አትችልም። ይህ ቅዠት ነው።» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። መስፍን ደጀኔ ደግሞ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ «በምን መስፈርት ነው እሱ ለአዲስ አበባ ህዝብ መብት ታጋይ የሆነው? ፓርቲ መስርቶ የተመዘገቡ ደጋፊዎችን ይዞ ነው? ሌላው በምን ምክንያት ይሆን ለአዲስ እበባ ማኅበረሰብ እታገላለሁ እያለ ለስብሰባ የባሕር ዳርን ህዝብ ሊያወያይ የሄደው?» ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።ሽመለስ ቶሎሳ በበኩላቸው « እስክንድር ያነሳው ጥያቄ የኔም ጥያቄ ነው። መላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ከእስክንድር ጋር መቆም አለበት። የኦነጋውያንን ድብቁን ሴራ ስላጋለጠ እንደዕብድ እያደረጋቸው ነው» ሲሉ፣ ከተማ ቶላ በሚል የፌስቡክ ስም «አረ እፍረት የሚባል ነገር የለም እንዴ? ታከለን ህዝብ አልመረጠውም እውነት ነው፡ ግን ለእራሱ አልተቀመጠም። አገሪቱዋን እየገዛ ያለው ፓርቲ ነው ያስቀመጠው። ታከለ እራሱን መምረጡ ስህተት ከሆነ እስክንድር እራሱን ባለ አደራ ብሎ መምረጡ በምን ሂሳብ ነው ትክክል የሚሆነው? የአገሪቱዋ ችግር ብዙ ሆኖ ሳለ ምነው እሱ ደግሞ ነጋ ጠባ ስለ ታከለ ብቻ የሚቃዠው?» በማለት ቅሬታቸውን አስፍረዋል።

Äthiopien Addis Abeba  Eskinder Nega  PK
ምስል DW/S. Musche
Äthiopien Sidama-Befreiungsbewegung Pressekonferenz in Hawassa
ምስል DW/S. Wogayehu

«እስክንድር  ታላቅ ሰው ነው። በዛሬው መግለጫ በአንድ ድንጋይ ሦስት ወፍ መቶበታል» ያሉት ደግሞ «ፍቅር ላቭ ፍቅር» በሚል ስም የፌስ ቡክ ተጠቃሚ የሆኑ አስተያየት ሰጭ ናቸው። እስክንድር አሳክቶታል ያሉትን ሲዘረዝሩም «አንድ መልእክቱን ቀድሞ ሳይረብሹ አስተላልፏል። ሁለት በኢትዮጵያ ጭንብል ያሉትን መሪዎች ምንነት ግልጽ አርጎ ህዝብ እንዲያውቃቸው አድርጓል። ሦስት የጸጥታ ሀይሉ አሁንም በፖለቲከኞች ትእዛዝ እንጂ ሕግ ማስከበር እንደማይችሉ ግልጽ አርጎ አሳይቶናል» በማለት ሃሳባቸውን አጠናቀዋል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ