1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

“የአህያን ስጋ ለገበያ ማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው”

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 11 2009

ከሦስት ሳምንት በፊት ሥራ የጀመረው እና መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የአህያ ቄራ በአስቸኳይ እንዲዘጋ ተወስኗል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ የተገነባው ቄራ እንዲዘጋ የተወሰነው “ከህዝብ ባህል እና እሴት ጋር የሚጻረር ነው” በሚል ነው፡፡ ውሳኔው መተላለፉን ተከትሎ “መጀመሪያውኑ ፍቃድ እንዴት ሊያገኝ ቻለ?” የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡

https://p.dw.com/p/2bY2Q
Esel
ምስል Colourbox

Ethiopia shutdown donkey export abbatior (Longer Version) - MP3-Stereo

የቢሾፍቱ ነዋሪዎች እና ሻንግ ዶንግ ዶንግ የተሰኘው የቻይና ድርጅት አይን ናጫ ሆነው ነበር የከረሙት፡፡ ነዋሪዎቹ የቻይናውያኑ ድርጅት ልዩ ስሙ ቃጂማ በተባለው ቦታ ሲያከናውን የነበረው ግንባታ ዓላማው ለምን እንደነበር ሰምተው ሲያጉረምርሙ ቆይተዋል፡፡ ቻይናውያኑ እየገነቡት በነበረው ቄራ ለእርድ የሚቀርበው በሀገሬው እንደተለመደው በሬ፣ በግ ወይም ፍየል ሳይሆን አህያ መሆኑን ሲያውቁ ተቆጥተዋል፡፡ ተቆጥተውም አልቀሩ “ባህል እና እሴታችንን የተጻረረ ነው” ያሉትን የቄራ ግንባታ እንዲቆም በተደጋጋሚ ለከተማው አስተዳደር አቤት ብለዋል፡፡

ለጥያቄያቸው አጥጋቢ ምላሽ ያላገኙት ነዋሪዎች በኦሮሚያ ክልል በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት በድርጅቱ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል፡፡ በሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ሁሉም ነገር የረገበ በመሰለበት ጊዜ ግን ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን በድርጊት ጭምር የገለጹበት ድርጅት ስራ መጀመሩ ተሰማ፡፡ ጉዳዩን “ፎርቹን” የተሰኘው ጋዜጣ ይዞት ከወጣ ጀምሮ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰነበተ፡፡ በቀን 200 አህያዎችን አርዶ ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም አለው የተባለው ቄራ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጎተጉትውም በዛ፡፡ ጫናው የበረታባቸው የመሰሉት የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ሰዎች ቄራው በአስቸኳይ እንዲዘጋ ወስነዋል፡፡ 

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ድርቤ ግርማ ስለ እርምጃው ለዶይቸ ቨለ አብራርተዋል፡፡  

“በፊት የነበሩት አመራሮች ህዝቡንም ሳያወያዩ ነው ወደዚህ ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዲገቡ የተደረገው፡፡ ቦታውም የተሰጠው ማለት ነው፡፡ ወደ ስራ ሲገባ ህዘቡ አመጽ ነው ያነሳው፡፡ [ፕሮጀክቱን] እስከማቃጠል ድረስ ደርሶ ነበር፡፡ የከተማው አስተዳደርም ኢንቨስትመንቱ ስራ ነው ተብሎ ህዝቡን ለማሳመንም ብዙ ጥረት ተደርጎ ነበር ግን ‘ከእኛ ባህል ጋር አይሄድም፡፡ ባህላችንን የሚያበላሽ፣ የሚያፋልስ ስለሆነ አያስፈልገንም ’ በሚል ነው በአንድ አቋም ህዝቡ የተቃወመው፡፡”

“ህዝቡ የጠላው ኢንቨስትመንቱን ሳይሆንፕሮጀክቱን ነው፡፡ ወይ ፕሮጀከቱን ቀይረው ሌላ ነገር ይስሩ ካልሆነ አንፈልግም ይቆም ነው የተባለው፡፡ ያው ከተማ አስተዳደሩ ደግሞ ለህዝቡ ነው እዚያ ጋር የተቀመጠው፡፡ የህዝቡን ድምጽ ስለሰማ ነው ውሳኔውን በደብዳቤ የሰጠው፡፡ መጀመሪያ በአካል ጠርቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ከተነገራቸው በኋላ በደብዳቤ መልክ ተሰጣቸው” ይላሉ ኃላፊዋ፡፡  

Golabal Ideas Walnussernte in Kirgistan
ምስል DW/K. Palzer

የቄራው ጉዳይ አሁን እንዲህ ገንኖ ይውጣ እንጂ በቻይናውያን በኩል ፍላጎት ማሳየት የጀመሩት ከዘጠኝ ዓመታት በፊት እንደሆነ በኢትዮጵያ በአህዮች እና በቅሎዎች ደህንነት ላይ የሚሰራ ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶ/ር ቦጄ አንዴቦ ይናገራሉ፡፡ 

“ቄራውን በተመለከተ ስንሰማ ይህ የመጀመሪያችን አይደለም፡፡ [እንደ ጎርጎሮሳዊው] 2008 ቻይናዎቹ ራሳቸው ሁለት ጊዜ መጥተው አነጋግረውን ነበር፡፡ ያኔ አይቻልም፤ አይሆንም ብለን መልሰናቸው ነበር” ይላሉ ዶ/ር ቦጄ፡፡ 

መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው እና በኢትዮጵያ ላለፉት 21 ዓመታት በመስራት ላይ የሚገኘው የአህያ ደህንነት እንክብካቤ ድርጅት በአፍሪካ እየተስፋፋ ስለመጣው የአህያ ስጋ ግብይት ጉዳት ጥናታዊ ዘገባ ማጠናቀሩን ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡ ዘገባው የአህያ ስጋ ንግድ በኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት የዳሰሰ ነበር፡፡ የአህያ ቄራ በሀገራቸው እንዲቋቋም ፈቅደው በስተኋላ ላይ ስላስቆሙ ሀገራት ልምድም አካትቷል፡፡ ከአፍሪካ ቡርኪናፋሶ እና ታንዛንያ ከእስያ ደግሞ ፓኪስታን ለዚህ በምሳሌነት ይቀርባሉ፡፡

የአህያ ስጋ ንግድ እንዲቋረጥ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች አንዱ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደሆነ ዶ/ር ቦጄ ይገልጻሉ፡፡ 

“አሁን ሰው የሚያየው ባህላዊውን ብቻ ነው፡፡ ይሄ ፊት ለፊት ያለውን ማለት ነው፡፡ አሁን ‘እኛ ሀገር አህያ አይታረድም፤ ከሃይማኖትም ከባህልም አንጻር ይሄ አስደንጋጭ ነው፡፡ ለምንድነው ወደዚህ ውስጥ የምንገባው?’ እየተባለ ባህሉ ብቻ ነበር የሚታየው፡፡ በሂደት ግን የኢኮኖሚ ቀውስ ያመጣል፡፡ ሰማንያ ሶስት በመቶ ኢትዮጵያዊ (ወደ ሰማንያ ሶስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ማለት ነው) ገጠር ነው የሚኖረው፡፡ ዕቃውን የሚያመላልሰው በአህያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ገበያ ብታይ ግማሹ ሰው፤ ግማሹ አህያ ነው፡፡ ያ አህያ ለጌጥ አይደለም የሚሄደው፡፡ ዕቃ ተሸክሞ ይሄዳል፤ ሌላ ዕቃ ተሸክሞ ይመለሳል፡፡ ምርት የሚጓጓዘው በአህያ ነው፡፡ አሁን አሁንማ በከተማም የቆሻሻ መጣያ ምሶሶ ናቸው፡፡ ለዚያም ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥሩ የበዛው፡፡ አስቀድሞ መንግስትም ህዝቡን ሰምቶ አቆመ እንጂ በኋላ ወደማይመለስበት ደረጃ ይመለስ ነበር” ሲሉ በቢሾፍቱ አስተዳዳር የተወሰደውን እርምጃ ይደግፋሉ፡፡

ዶ/ር ቦጄ “የማይመለስበት ደረጃ” ሲሉ የአህዮችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መመናመን የሚፈጥረውን ቀውስ ነው፡፡ እንደ ድርጅታቸው ጥናት ከሆነ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 7.4 ሚሊዮን አህዮች ይገኛሉ፡፡ ይህም ኢትዮጵያን በአህዮች ብዛት ከዓለም ቀዳሚ ደረጃ ላይ እንደሚያስቀምጣት ዶ/ር ቦጄ ይናገራሉ፡፡ በጎርጎሮሳዊው 2011 በአስራ አንድ ሚሊዮን አህዮች ከዓለም አንደኛ የነበረችው ቻይና ደረጃውን ለኢትዮጵያ አስረክባ ወደ ሁለተኛነት ተንሸራታለች፡፡ በቻይና አሁን ያለው የአህዮች ብዛት ከኢትዮጵያ በአንድ ሚሊዮን ያነሰ መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር ቦጄ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ነው ይላሉ፡፡ አንድ ለእርድ የቀረበን አህያ በሌላ ለመተካት በትንሹ አራት ዓመት እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ፡፡   

በአህያ ቄራው መዘጋት ዙሪያ በፌስ ቡክ ገጻችን በርካቶች አስተያየታቸውን አስፍረዋል፡፡ በእርምጃው የተደሰቱ እንዳሉ ሁሉ “መጀመሪያውኑ መቀፈቀድ አልነበረበትም” ብለው የተከራከሩም አሉ፡፡ “የኢትዮጵያ መንግስት ኢንቨስትመንት ከተባለ አይኑን ጨፍኖ ከመስጠት ወደ ኋላ አይልም፡፡ የፕሮጀክት ውጫዊ ተጽእኖ አዋጭነት በጭራሽ አያጠናም” ሲሉ ሶዶ ዌራ ኬኛ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ ተችተዋል፡፡ “በየጊዜው በእያንዳንዱ የመንግስት መዋቅር የሚወሰንን ውሳኔ ሁሉ ከፍተኛዎቹ የፖለቲካ ዘዋሪዎች ያውቁታል ማለት አይቻልም፡፡ ጉዳዩን ሲያውቁ አስቆሙት! በቃ! እዚህ ላይ ግን የእነሱ ግፊት ሳይሆን የህዝብ ግፊት ነው፡፡ ህዝብን በመስማታቸው ግን ደስ ብሎናል” ብለዋል ሌላው አስተያት ሰጪ ወንድም በላይ ካሳ፡፡ 

የአህያ ቄራው ከባህል ጋር እንደሚጋጭ እየታወቀ “ቀድሞውኑ እንዴት ፍቃድ ሊያገኝ ቻለ?” ለሚለው ጥያቄ ወይዘሮ ድርቤ እርሳቸው እና አሁን ያለው አስተዳደር በቅርቡ ወደ ቦታው እንደመጡ በመጥቀስ ትክክለኛውን ምክንያት እንደማያውቁት ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ