1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዉሮጳና መፍትሄ ያልተገኘለት የስደተኞች እጣ

ዓርብ፣ ሰኔ 12 2007

ባለፈዉ ማክሰኞች ስብሰባ የተቀመጡት የአዉሮጳ ሕብረት የሃገር አስተዳደር ሚኒስቴሮች የሜዲተራንያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አዉሮጳ የገቡትን ስደተኞች በአዉሮጳ ሕብረት ሃገራት በኮታ ለማከፋፈል በያዙት እቅድ ላይ ስምምነት መድረስ አልቻሉም።

https://p.dw.com/p/1FjN1
Italien italienisch-französische Grenze Flüchtlinge
ምስል Getty Images/AFP/J. C. Magnenet

የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሲዮን በኢጣልያ እና በግሪክ የሚገኙ 40 ሺ ስደተኞች ን ወደ ሌሎች የሕብረቱ ሃገሮች በኮታ እንዲሰፍሩ ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ሃሳቡ በሕብረቱ ሃገራት መካከል ከፍተኛ ልዩነት አስነስቷል።

አዉሮጳዉያኑ ተጎራባች ሃገራት ኢጣልያና ፈረንሳይ አዋስኝ ድንበራቸዉ ላይ በሰፈሩት ስደተኞች ጉዳይ ቅራኔ ዉስጥ መግባታቸዉ አሳሳቢ ሆንዋል። ይኸዉ ችግር በሚታይበት በሉክዘምበርግም ለስደተኞች ጉዳይ መፍትሔ ለማፈላለግ የሕብረቱ መንግሥታት የሃገር አስተዳደር ሚኒስትሮች በየጊዜዉ ስብሰባ ቢያካሂዱም ስምምነት ላይ መድረስ ተስኗቸዋል። የኢጣልያ የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር አልፋኖ እንደሚሉት፣ ስደተኞቹ ሜድትራንያንን አቋርጠዉ መጀመሪያ በሚገቡባት ኢጣልያ ውስጥ መቆየት አይፈልጉም።

« ስደተኞቹ ወደ ኢጣልያ የሚመጡት በኢጣልያ ለመኖር ሳይሆን ወደ ሌሎች የአዉሮጳ ሕብረት ሃገራት ለሚሻገር ነዉ»

ኢጣልያ ወደ ሃገርዋ የገቡትን በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች፣ ወደ ፈለጉበት ሌላ የአዉሮጳ ሃገር ማለትም ወደ ስዊድን ወደ ጀርመን ወይም ደግሞ ወደ ፈረንሳይ መሄድ እንዲችሉ ስትል፣ የደብሊኑ ስምምነት በሚያዘው መሠረት አትመዘግብም። ፈረንሳይ ወደ ሃገርዋ የሚገቡትን ዜጎች ሁሉ ድንበር ላይ ትቆጣጠራለች። በዚህ ድርጊትዋም በሸንጌን ውል ተፈራራሚ ሀገራት መካከል በነፃ የመዘዋወርን ስምምነት ጥሳለች። ፈረንሳይ ይህን የምታደርገዉ ይላሉ፤ የፈረንሳይ የሃገር ዉስጥ አስተዳደር ሚኒስትር ካዘነቭ፤ ፈረንሳይ ማንኛዉንም ስደተኛ መቀበል ስለማትሻ ነዉ።
« በቪንቲሚሊያ ያለዉ ሁኔታ ለኢጣልያም ሆነ ለፈረንሳይ እጅግ ከባድ ሆንዋል »

የጎረቤቶቹ ሀገራት ንትርክ በአሁኑ ወቅት በአዉሮጳ መንግሥታት መካከል ስደተኞች በኮታ በመከፋፈሉ ሀሳብ ላይ ያለመስማማታቸዉን በግልጽ ያሳየ ምልክት ነዉ። በዚህ ጥያቄ ላይ የአዉሮጳ ሃገራት የሃገር አስተዳደር ሚኒስትሮች ምንም ዓይነት ገላጋይ ሀሳብ ላይ አለመድረሳቸዉን የፊደራል ጀርመን የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ቶማስ ዴሚዜር ተናግረዋል።

« እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረሰ ውጤት የለም። ይሁንና፣ በአፋጣኝ አንድ የጋራ መፍትሄ ላይ መድረስ እንዳለብን ተስማምተናል። »
ጀርመን ኢጣልያ እና ፈረንሳይ የጋራ መፍትሄ ለማግኘት የትብብር ስራ ጀምረዋል። የፈረንሳዩ የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ካዘነቭ እንዳስታወቁት፣ ችግሩ ከአውሮጳውያኑ መፍትሔ የሚጠይቅ እንደመሆኑ መጠን፣ አንድ የጋራ ርምጃ ለማግኘት ሙከራ መደረግ አለበት።
ሶስት ትላልቅ ሃገራት ስደተኞቹ ሚዛኑን በጠበቀ ኮታ በአዉሮጳ ሕብረት ሃገራት ዉስጥ እንዲከፋፈሉ ጥረት ያደርጋሉ። የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽንም በስደተኞች መጥለቅለቅ ከፍተኛ ችግር ከደረሰባቸዉ ከኢጣልያና ከግሪክ 40 ሺ ስደተኞች በሌሎች የአዉሮጳ ሕብረት ሃገራት በኮታ እንዲከፋፈል ሃሳብ አቅርቦአል። ስፓኝ እና ፖርቱጋል እንዲሁም አንዳን የምስራቅ አዉሮጳና የባልቲክ ሃገራት ሀሳቡን ተቃዉመዉታል። የጀርመን የሃገር አስተዳደር ሚኒስቴር ቶማስ ዴሚዜየር በበኩላቸዉ ይህን ሃሳብ ይቃወሙ የነበሩ አንዳንድ ተቀናቃኝ ሃገሮች ይላሉ ሃሳባቸዉን በሌላ መንገድ እየቀየሩ ነዉ።

« እነዚህ ሃገራት መሳተፍ የሚፈልጉት በፈቃደኝነት ያለግዴታ ከሆነ ብቻ ነዉ። ይህ ደግሞ ትክክለኛ መንገድ ነዉ»
ጀርመን ኢጣልያና ፈረንሳይ ስደተኞችን ለመቀበል የሚያስችሉ ማዕከላት በተቻለ ፍጥነት እንዲቋቋሙ የሚያስችል ዉሳኔ ላይ እንዲደረስ ይሻሉ። በኢጣልያ ስደተኞች የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱ በፍጥነት የሚወሰንባቸው ቢሮዎች መቋቋም አለባቸውም ነው እየተባለ ያለው።

በሸንገን አባል ሀገራት ድንበር ላይ ቁጥጥር ይደረግ የሚለዉን ሃሳብ የጀርመኑ የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ቶማስ ዴሚዜር አልተቀበሉትም። እንደ ዴሚዜር ከዚህ ይልቅ ሃገራት የአዉሮጳ ሃገራት ስደተኛ መጀመርያ በረገጠበት አዉሮጳ ሃገር እንዲመዘገብ የሚለዉን የደብሊኑን ስምምነት ተግባራዊ እንዲደደርጉ ይፈልጋሉ።

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Treffen EU-Innenministerrat in Luxemburg
ምስል DW/B. Wesel
Italien Frankreich Grenze Flüchtlinge
ምስል Reuters/E. Gaillard
Ventimiglia Grenze Italien Frankreich Flüchtlinge Polizeiaktion
ምስል Getty Images/AFP/C. Magnenet