1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አውሮጳና ጀርመን

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 26 2003

ዛሬው አውሮፓና ጀርመን መሰናዶዋችን ሁለት ርዕሰ-ጉዳዮችን እናስተነትናለን። ጀርመን ውስጥ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የሳምንቱ መጨረሻ ላይ ስለ ተያዙት ተጠርጣሪ አሸባሪዎች የሚያወሳው የመጀመሪያው ጥንቅር ነው። የፋይናንስ ቀውስ በአውሮጳና የፈረንሳይ ገበሬዎች ራስን የማጥፋት ዕጣ የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ርዕሳችን ነው።

https://p.dw.com/p/RLY5
የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትምስል picture-alliance/dpa

ለሁለቱም ርዕሰ-ጉዳዮች ጥንቅር ማንተጋፍቶት ስለሺ። ወደ መጀመሪያው ርዕሳችን ስንሻገር፤ ጀርመን ውስጥ በቁጥጥር ስለዋሉት ተጠርጣሪ አሸባሪዎች የሚያትተውን ዘገባ በማስቀደም ነው። እዚህ ጀርመን ውስጥ በሽብር ተግባር የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦች የፈንጂ ጥቃት ለመፈፀም ሲሰናዱ የተያዙት በሳለፍነው አርብ ነበር። ተጠርጣሪዎቹ ትናንት በዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሀይል ፓኪስታን ውስጥ እንደተገደለ የተነገረለት የኦሳማ ቢንላድን የሽብር መረብ የአልቃኢዳ ቡድን አባላት እንደሆኑም ተጠቅሷል። እድሜያቸው ከ19 እስከ 31 ዓመት ውስጥ ከሚገኘው ከእነዚህ ሶስት የሽብርተኝነት ተጠርጣሪዎች መካከል ሁለቱ የጀርመን ዜግነት ያላቸው በትውልድ ሞሮኮዋዊና ኢራናዊ መሆናቸው ተዘግቧል። ሌላኛው ተጠርጣሪ ደግሞ በትውልድም በዜግነትም ሞሮኮዋዊ መሆኑ ታውቋል። የተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር መዋል አስመልክቶ በጀርመን የፌዴራሉ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ራይነር ግሪስባውም ሲያብራሩ ድምፅ 1 «ተከሳሾቹ በጦር መሳሪያ የታገዘ ጀሀድ ለማካሄድ እንዲያስችላቸው ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ በስፋት ሲንቀሳቀሱ ነበር። ራሳቸውን በፈንጂ አንጉደው ጀርመኖችንና ክርስቲያኖችን በመግደል መንግስተ-ሰማያትን ለመውረስ ነበር ህልማቸው። ያንን ተግባራዊ ለማድረግም ቁርጥራጭ ብረቶች የተቀላቀሉበትና በከፍተኛ ዕመቃ የሚፈነዳውን ፈንጂ ራሳቸው ለመስራት አስፈላጊውን መረጃ ሁሉ ሲያሰባስቡ ነበር» እንደ ጀርመን የደህንነት ሰዎች መረጃ ከሆነ ሶስቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ክትትል ማድረግ የተጀመረው ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ ነበር። የፌዴራሉ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከተለያዩ ምንጮች በርካታ መረጃዎች ይደርሱት እንደነበረም ጠቁሟል። በተለይ ተጠርጣሪዎቹ በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ይለዋወጧቸው እና ኢንተርኔት ውስጥ ይፈልጓቸው የነበሩ መረጃዎች የሽብር ተግባራቸውን ከፍፃሜው ለማድረስ መጠጋታቸውን አመላካች ነበር ተብሏል። ፈንጂ ለመስራት የሚያስችሏቸውን አሴቶን እና ሀይድሮጅን ፐርኦክሳይድ የተሰኙ ንጥረ-ነገሮችን በመኖሪያ ቤታቸው አከማችተው እንደነበረም ተገልጿል። ወደ ተግባር ከመግባታቸው አስቀድሞ ግን ፈንጂውን ለመስራት ንጥረ-ነገሮቹን እንዴት እንደሚብላሉ የሚያብራራ መረጃ ከኢንተርኔት ላይ እንደቀዱም ተደርሶበት ነበር። እነዚህ የሽብር ተግባር ተጠርጣሪዎች ግንኙነታቸው ከነማን ጋር እንደነበር ለማወቅም ወደ 108 የሚጠጉ የጀርመን ፖሊሶች ለአንድ ዓመት ያህል ክትትል ሲያደርጉባቸው ቆይተዋል። እንደ ጀርመን የደህንነት ሰዎች ገለፃ ከሆነ፤ የተጠርጣሪዎቹ ቡድን ውስጥ እስከ ስምንት የሚደርሱ ሌሎች አባላት እንደሚገኙበትም ታውቋል። በርግጥ የሌሎኞቹ ተጠርጣሪዎች ማንነት ገና በይፋ አልተገለፀም። የፌዴራሉ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ሀላፊ ዮርግ ሲርከ ጀርመንን ወደፊት የሽብር ጥቃት ያሰጋት እንደሆን ተጠይቀው እንዳብራሩት፤ ድምፅ 2 «ለብረተሰቡ እንዲህ ነው ብለን ግልጽ በሆነ መልኩ የምናስተላልፈው ነገር የለም። ይህ ድርጊትም ሆነ የከዚህ ቀደሙ እንደሚያሳየው ከሆነ፤ በዓለም አቀፉ የሽብርተኞች ጥቃት ኢላማ ውስጥ እንደሆንን ነን። እናም ጀርመን ውስጥ ወደፊት የሽብርተኞች የጥቃት ዕቅድ ሊኖር እንደሚችል እንገምታለን» በርግጥ መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ትናንት ዋነኛው የአልቃኢዳ አቀናባሪና መሪ ኦሳማ ቢን ላዲን መገደሉ ከተነገረ በኌላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ስጋቱ አሁንም እንዳለ ጠቁመዋል። የቢን ላደን መገደል ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልፀው አሸባሪዎች ላይ አሁንም ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አክለውበታል። እግረ መንገዳቸውንም ኦሳማን ለገደሉት የአሜሪካ ወታደሮች ፕሬዚዳንት ኦባማ ክብር እንዳላቸው ገልጠዋል። ሙዚቃ አድማጮች የምትከታተሉት አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችንን ነው። አሁን ወደ ሁለተኛው ርዕሰ-ጉዳያችን እንሻገራለን። ቀደም ሲል በመግቢያችን ላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው የፋይናንስ ቀውስ በአውሮጳና የፈረንሳይ ገበሬዎች ራስን የማጥፋት ዕጣ ይሰኛል ርዕሱ። በአውሮጳ በተለይም በደቡቡ የአውሮጳ ክፍል የሚገኙ ሀገራት የፋይናንስ ገበያ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ከተነገረ ሰነባብቷል። ቀደም ሲል ግሪክና አየርላንድ አሁን ደግሞ ፖርቱጋል የገንዘብ አቅማቸውን ለማረጋጋት አፋጣኝ ብድር እንደሚያስልጋቸው እየተገለፀ ነው። በአውሮጳ ህብረትና በዩሮ ቀጣና ዩሮን ለማረጋጋት መሰናክል የሆኑ ገና ያልተፈቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ይነገራል። አይርላንድ ለጠየቀችው አፋጣኝ ብድር ወደ ፊት መክፈል ያለባት ወለድ አነስተኛ እንዲሆን ትፈልጋለች። ጣሊያን የሚጠበቅባትን ዕዳ በተመለከተ ለየት ያለ ህግ እንዲወጣ ትሻለች። ጀርመን ስለተትረፈረፈው የውጭ ንግዱ ማንም እንዲያነሳበት የሚፈልግ አይመስልም። ፊንላንድ ዩሮን በማዳኑ ተግባር ብዙ እንዲጠበቅባት አትፈልግም። ሌላም ሌላም። ከወደ ፈረንሳይ የተሰማው ደግሞ እጅግ አስደንጋጭ ነው። ከውጭ ሲመለከቷቸው የፈረነሳይ ገበሬዎች እጅግ የደላቸው ነው የሚመስሉት። ከአውሮጳ የገበሬዎች ዕርዳታ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት እነኚሁ የፈረንሳይ ገበሬዎች ናቸው። እንዲያም ሆኖ ግን በርካታ የፈረንሳይ ገበሬዎች በኑሮዋቸው ከመደበትም ባሻገር ራሳቸውን እያጠፉ እንደሆነ የዶቼቬሌዋ ጄኔቪቭ ገልጣለች። የ35 ዓመቱ ገበሬ ፍራንሲስ ቪቻርድ 200 ሄክታር ወደ ሆነው ማሳው ይዞን ሄደ ስትል ትጀምራለች ጄኔቪቭ። ለዕርድ የሚያደልባቸው 300 ፍሪዳዎች አሉት ቪቻርድ። ጥቂት ለስራ አገልግሎት የሚውሉ ፈረሶችና በጎችም በጋጣውና በጉሮኖው ውስጥ ይገኛሉ። የመፀው ወራት ነው፤እናም ቪቻርድ በምጥ ላይ የሚገኙ ላሞቹ ጥጆች እንዲወልዱለት እርዳታ ለማድረግ እኩለ ሌሊት ላይ ሳይቀር ከእንቅልፉ ይነሳል። ግብርና እጅግ የሚወደው ሙያው ነው። ሆኖም ግን በሙያው ለመቀጠል ነገሮች ሁሉ እንዲህ በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም ባይ ነው። የዛሬ 13 ዓመት ግድም ግብርናውን ከቤተሰቦቹ ሲረከብ እርሻው አትራፊ ነበር። ያኔ ለራሱ 1500 ዩሮ የወር ደሞዝ ለመቁረጥ ይቻለው ነበር። አሁን ይህ እጅግ አሽቆልቁሎ በወር 300 ዩሮ ደርሷል። ቪቻርድ ከሚወደው ሙያ የሚያገኘውን እጅግ አነስተኛ ገቢ እንዲህ ያማርራል። ድምፅ 3 «ለእንደዚህ አይነቱ አሰቃቂ ደሞዝ በሳምንት l70 ሠዓታት አንዳንዴም ከዚያ በላይ ማነው መስራት የሚፈቅደው? ማንም! ገበሬዎች እንደ ስራ አጥነት ዋስትና ያሉ ማህበራዊ ድጋፎችን ለማግኘት አይችሉም። ወይንም ደግሞ ሌላ አይነት ማህበራዊ ዋስትና የላቸውም። እንደዚያ አይነት አሰቃቂ ደሞዝ ሲኖራቸው ሰዎች መቀጠል እንደማይችሉ ይማቸዋል» በነገራችን ላይ በአውሮጳ የኑሮ ውድነት ወጣቱ ፈረንሳዊ ገበሬ ቪቻርድ በወር የሚያገኘው 300 ዩሮ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ 6 ልጆች ይዞ የ150 ብር የወር ደሞዝተኛ መሆን እንደማለት ነው ልትሉት ትችላላችሁ። በርግጥ በንፅፅሩ ወቅት በአውሮጳ ያለውን የመንግስት ድጎማ ሂሳብ ውስጥ ማስገባት የለብንም። ቪቻርድ ሌሎች ገበሬዎችን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው የገቢ ማሽቆልቆል ባለቤቱ ከተማ ውስጥ ነርስ በመሆኗ እንደማገገሚያ ወስዶታል። ጎረቤቶቹ ገበሬዎች ግን ሁለተኛ ደሞዝ የላቸውም። ባለፉት ስድስት ወራት እንኳን ከሚኖርበት መንደር ብዙም ሳይርቅ ይኖሩ የነበሩ 5 ገበሬዎች ራሳቸውን ለማጥፋት ተገደዋል። ድምፅ 4 «አንድ የ52 ዓመት ጎልማሳ ገበሬ ስላጋጠማቸው የገቢ ችግር ከጎረቤታቸው ጋር ከሰአት ላይ ሲያወጉ ቆዩ። ልክ ጎረቤታቸው እንደሄዱም ራሳቸውን ኩሬው ውስጥ ወረወሩ። አንድ ሌላ ሰውዬ ደግሞ ጡረታ ለወጡ ወንድማቸው ግዢ ለማከናወን ብድር ቢጠይቁ ባንክ ከለከላቸው። እናም ወደ ቤታቸው ሄደው ተኩሰው ራሳቸውን ገደሉ» ቪቻርድ የገቢ ምስቅልቅሉ መንስዔው በርካታ ነው ይላል። ገበሬዎች ከብቶቻቸውን የሚሸጡት በርካሽ ዋጋ ነው። ወጪያቸው ግን በአንፃሩ ከፍተኛ ነው። ለአብነት ያህል ከብቶቻቸውን የሚቀልቡት አንድ ቶን ድርቆሽ ከ5 ዓመታት በፊት 180 ዩሮ ነበር። አሁን እጅግ አሻቅቦ 350 ዩሮ ደርሷል። የፈረንሳይ መንግስት ይህን የገበሬዎቹን ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ መደበትና ራስን መጥላት በምክር ለማለዘብ ችግር ውስጥ የገቡ ገበሬዎች የሚወያዩበት የስልክ መስመር ማዘጋጀቱ ታውቌል። በርግጥ ገበሬዎቹን ከገጠማቸው የፋይናንስ ቀውስ አንፃር የስልክ መስመሩ ምን ያህል መፍትሄ እንደሚሆን አይታወቅም። አውሮጳ ላይ በአንዳንድ ሀገራት የተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ የበርካታ አውሮጳውያንን በር እያንኳኳ ነው። በእርግጥ በአንዳንድ ሀገራት መሻሻል ሳይታይ አልቀረም። ለአብነት ያህል የጀርመን ምጣኔ ህብት ቀውሱ ከተከሰተ ወዲህ ቀስ በቀስ እድገት እያሳየ መሆኑ የሚታወቅ ነው። በአጠቃላይ ግን የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የገቡ ሀገራት ሙሉ ለሙሉ ከችግራቸው መች እንደሚላቀቁ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

Faust mit aufgemalter Europa-Flagge
የአውሮጳ ኅብረት ከፊቱ የተጋረጠውምስል fotolia/macky_ch
Puzzlebild Triptychon Afghanistan Terror Osama Bin Laden Dossierbild 1
ተጠርጣሪዎቹ የሟቹ ኦሳማ ቢንላደን አልቃይዳምስል AP

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ