አውሮጳን ለመጠበቅ አፍሪቃን በአግባቡ መርዳት

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:13
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:13 ደቂቃ
26.09.2017

የልማት እርዳታ ለአፍሪቃ እንዴት?

«ለልማት የሚሰጡ የገንዘብ እርዳታዎች በተለይም ገንዘቡ በቀጥታ ለበጀት ድጋፍ የሚዛወር ከሆነ ብዙውን ጊዜ እርዳታው ለሚያስፈልገው ህዝብ አይደርስም። ገንዘቡ የፖለቲካ ሥልጣናቸውን በመጠቀም የሀገርን ሀብት የሚመዘብሩ ባለሥልጣናት እጅ ከገባ ሥልጣናቸውን ለማራዘም ለአስከፊው ሙስና ማመቻቻ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል።»ዶክተር ልጅ አስፋ ወሰን አሥራተ ካሳ

ጀርመን በአንድ በኩል እንግዳ የመቀበል ባህልዋን መጠበቅ ይኖርባታል። በሌላ በኩል ደግሞ የፍልሰት እና የስደት መሠረታዊ ምክንያቶችን እውነታ መጋፈጥ አለባት። በሀገራቸው ደርዝ ያለው ህይወት እንዳይመሩ ለህዝቦቻቸው እድሉን የማይሰጧቸው አምባገነኖች ከሚመሯቸው የአፍሪቃ ሀገራት በርካታ ሰዎች ይሰደዳሉ። ከአፍሪቃ የምሁራን ስደትን ለማስቆም ክፍለ ዓለሙን ከልማት እርዳታ ጥገኝነት አላቆ ህዝቡ በራሱ እንደሚተማመን ማድረግ መፍትሄ ነው ይላሉ ዶክተር ልጅ አስፋ ወሰን አሥራተ ካሣ የአፍሪቃ እና የመካከለኛው ምሥራቅ የንግድ ጉዳዮች አማካሪ ደራሲ እና የፖለቲካ ተንታኝ በቀጣዩ ሀተታቸው። ላለፉት 50 ዓመታት በምዕራባውያን የተለሳለሰ የፖለቲካ መርህ ምክንያት  የአፍሪቃ አምባገነኖች ከአውሮጳውያን ቀረጥ ከፋዮች ኪስ በሚወጣ ገንዘብ ይደገፋሉ ይላሉ ዶክተር ልጅ አስፋወሰን በሀተታቸው። የአፍሪቃ መጻኤ እድል እንዲቃና በመጀመሪያ ደረጃ አውሮጳ ከአውዳሚው የኤኮኖሚ እና የንግድ መርህ መላቀቅ አለባት። ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ትከሻ ለእርሻ ኢንዱስትሪዋ የምትሰጠውን ድጎማ ማቆም አለባት። በስተመጨረሻም በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የመሬት መቀራመት ለማስቀረት ውጤታማ ዓለም አቀፍ እርምጃዎችን ተግባራዊ እንዲሆኑ ግፊት ማድረግ አለበት። መሬት መቀራት የዓለማችንን ደሀ ሀገራት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ካለው የእርሻ

Deutschland G20 Afrika Treffen

መሬታቸው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያግዳል።አፍሪቃ በገጠር እርሻን ማስፋፋት የሚያስችል  መሠረተ- ሰፊ ድጋፍ ትሻለች። የሀገር ውስጥ ምግብ አምራቾችን የሚጎዱ  አፍሪቃ የሚራገፉ ምርቶች መታገድ አለባቸው። ከምንም በላይ የአፍሪቃ ሴቶችን ማበረታታት ያስፈልጋል። ሴቶች ለአፍሪቃ መጻኤ እድል ቁልፍ ሚና አላቸው። አፍሪቃ የህዝብ ቁጥር መጨመር ችግርን በተሳካ መንገድ ለመፍታት በሴቶች ላይ ማተኮር አለበት። ከተሞችን ማዘመን፣ ከሌሎች የተወሰዱ የፍትህ እና የኤኮኖሚ ስርዓቶች፣ አዲሱ መገናኛ ብዙሀን፣ በአፍሪቃ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴት ስርዓቶች ላይ ፈጣን ለውጦች አምጥተዋል  ። በአሁኑ ጊዜ የቀድሞዎቹ እና አዲሶቹ እሴቶች ተዋህደው ማየት የተለመደ ሆኗል። በተለይ በከተሞች አካባቢ በየጊዜው ይለዋወጣሉ። በዛሬዋ አፍሪቃ ሀብት እና ሥልጣን ተጽእኖ የሚያደርጉ እሴቶች የሆኑ ይመስላል። በዚህ ሰበብም ማህበራዊ ቤተሰባዊ እና አስተዳደራዊ ግንኙነቶች ሳይቀሩ በከፍተኛ ደረጃ ከገንዘብ ጋር ተያይዘዋል። ይህ ችግር ግን በአፍሪቃ ብቻ አይደለም ያለው። እርስ በርስ በተሳሰረው ዓለም የስስት እና የስግብግብነት ክፉ መንፈስ ሰፍኗል። ካፒታሊዝም በአሁኑ ቅርጹ፣ትክክለኛም ሆነ ዘላቂ አይደለም። ስለዚህ በ21 ኛው ክፍለ ዘመን ትልቁ ተግዳሮት የገበያ ፍላጎትን ከሰብዓዊነት ጋር ማጣጣም ነው። ምርጥ የሚባሉት እቅዶች ሳይቀሩ ለሞት የሚዳርጉ መዘዞችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። የምዕራባውያን ነጻ

Malawi Schülerinnen und Schüler der Grundschule in Mkundi Region Dedza

የምግብ እርዳታ የአፍሪቃን የሀገር ውስጥ የእርሻ ገበያን ያጠፋል። ለልማት የሚሰጡ የገንዘብ እርዳታዎች በተለይም ገንዘቡ በቀጥታ ለበጀት ድጋፍ የሚዛወር ከሆነ ብዙውን ጊዜ እርዳታው ለሚያስፈልገው ህዝብ አይደርስም። ገንዘቡ የፖለቲካ ሥልጣናቸውን በመጠቀም የሀገርን ሀብት የሚመዘብሩ ባለሥልጣናት እጅ ከገባ ሥልጣናቸውን ለማራዘም ለአስከፊው ሙስና ማመቻቻ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል። የኒውዮርክ ዩኒቨርስቲውን ዊሊያም ኢስተርሊን ወይም ስኮትላንዳዊውን የኖቤል የኤኮኖሚክስ ተሸላሚ አንገስ ዴተንን የመሳሰሉ ምሁራን የጋራ የልማት እርዳታን ጽንሰ ሀሳብ ፈጽሞ የተሳሳተ ነው ሲሉ ይተቻሉ። ለዚህም በአስቸኳይ የተረዳው መንግሥት የቀረጥ ከፋዩን ገንዘብ እንዴት እንደተጠቀመበት በየዓመቱ  የሚመረመር  እንደ ጀርመን ብሔራዊ የኦዲት መሥሪያ ቤት በጀርመንኛው መጠሪያ «ቡንደስሬሽኑንግስሆፍ» ያለ የዓለም አቀፍ የልማት እርዳታ ኦዲት ቢሮ ያስፈልጋል። የልማት እርዳታ በርግጥ ትርጉም የሚሰጠው ህዝቡን ለሥራ የሚያነሳሳ ሲሆን ብቻ ነው። አፍሪቃ ዘላቂ እና በተነሳሽነት ላይ የተመሠረተ የልማት እርዳታ ነው የሚያስፈልጋት። አንድ ነገር ርግጥ ነው፤ አንድም ከውጭ የሆነ ፣ አሜሪካም አውሮጳም ቻይናም አንዳቸውም አፍሪቃን ሊያድኑ አይችሉም። ህዝቧ በራስ ከተማመነነ እና በጥንካሬም እምነት ካለው ክፍለ ዓለሟ ራሷ ማዳን ትችላለች። ይህ ሲሆን የአፍሪቃውያን ምሁራን ፍልሰት ይቆማል። አፍሪቃውያን የራሳቸውን እድል በራሳቸው መወሰን አለባቸው። በተለያየ ችግር የተበተበችው አፍሪቃ ወደፊት የተሻለ ተስፋ ያላት ክፍለ ዓለም እንድትሆን አውሮጳ ሊረዳት ይገባል።  
ዶክተር ልጅ አስፋወሰን አሥራተ ካሣ
ኂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ